የሴቶች ጉዳይ የማይመለከተው ሰው፣ ተቋም፣ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ወይም አገር  የለም። ለዛም ነው የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች ማስፈለጋቸው፤ የለውጥ አስተባባሪና ቀስቃሽ እንዲሆኑ። ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ ከተሰጣቸው መካከል ታዲያ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አንዱና ዋነኛው ነው።

ስለዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥራ አፈጻጸም ላነሳ አይደለም፤ ይልቁንም ከቀናት በፊት በመሥሪያ ቤቱ የተካሄደ አንድ የጥናታዊ ጽሑፍ ጉባኤ ልነግራችሁ ነው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሴቶች ጉዳይ ማካተትና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት የሚባል ክፍል አለ። ከዚህ ክፍል ተግባራት መካከል ደግሞ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት አንዱ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በየሁለት ወሩ የሚካሄድ የስርዓተ ጾታ ምርምር ትምህርታዊ ጉባኤ ያዘጋጃል። ይህ ቀጥሎ ዳሰሳ ያደረግንበት መድረክ ለሰባተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ በተለያዩ ሁለት ባለሙያዎች የቀረቡ  ጥናቶች ያለእድሜ ጋብቻ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ቀዳሚውን ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ጉዳይ እምሬ፤  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊና ባህላዊ አንትሮፖሎጂ ዘርፍ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። ዶክተር ጉዳይ ለጥናታቸው ናሙና የወሰዱት ወይም ጥናት ያደረጉት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ፎገራ ወረዳ የሚገኙ ሁለት ገበሬ ማኅበራትን ነው።

ዶክተሯ የጥናቱ ዓላማ ያሉት ያለ እድሜ ጋብቻ ከአያት ጀምሮ እስከ ልጅ ድረስ ያለውን ሂደት፤ ማለትም በሶስት ትውልዶች ላይ ያለው ልዩነት እንዲታይ ለማስቻል ነው። ታዲያ ያለእድሜ ጋብቻ ህግ አለ፣ የሴቶች ጉዳይ ቢሮም በየቦታው ተከፍቷል እየተባለም ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ዛሬም ድረስ ሊያስቆሙት የሚቻል አልሆነም፤ ለምን የተባለ እንደሆነ ባለሙያዋ እንደገለጹት ጋብቻውን የሚያደርጉት በድብቅ በተለያየ መንገድ ስለሆነ ነው።

ታዲያ ጥናቱ እንደሚያመላክተው በአያቶች ጊዜ ጋብቻው ይካሄድ የነበረው እኩል የኑሮ ደረጃ ባላቸው ሰዎች መካከል ነበር። በእናቶች ዘመን ይህን ለማስቆም ህግ የተሠራ ቢሆንም ነገሩ ግን በህግ ሊገታ የቻለ አልነበረም፤ ዛሬም ድረስ ቀጥሎ ይታያል።

ለምን በድብቅ ይድራሉ? ይህን የሚያደርጉት ህጉን ሽሽት ነው። ህጉን ፈርተው ሰርግ ብለው በይፋ ባይደግሱም የተለያዩ ክብረ በዓላትን አስታከው ልጆቻቸውን ይድራሉ። በተጨማሪም ስለዚሁ ተግባራቸው አመክንዮ ብለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ ባል የሞተባት ደግሞም ወንድ ልጅ የሌላት ሴት መሬቱን የሚወርስና የሚያርስበት ስለማይኖር ሴት ልጇን ትድራለች። ይህ ሰው አንድም ጥበቃ ይሆናል ፤መሬቱንም ያርሳል።

እንደ አያቶች ዘመን፥ የኑሮ ደረጃ አሁን ላይ ትኩረት የሚሰጠው አይደለም።ደሃ የሆኑ እማወራዎች ልጃቸውን ለሀብታም ለመዳር ይጠይቃሉ።ለዚህም ሲሉ ልጆቻቸውን ከትምህርት የሚያስወጡም አሉ። እንደ ዶክተር ጉዳይ ገለጻ በተለይ ትምህርትን በተመለከተ አወዛጋቢ ችግር መሆኑን ነው ጥናቱ ያሳየው። በቁጥር ትንሽ ቢሆኑ እንኳን ትምህርታቸውን ያቋረጡ ልጆች ለማኅበረሰቡ መጥፎ ምሳሌ ሆነው ይቀመጣሉ። እነርሱን እያዩ ልጆቻቸውን ከታች ክፍል እያወጡ ይድሯቸዋል።

ሌላው ጥናቱ ያመላከተው ችግር በማህበራዊ ኑሮ ጾታን መሰረት ያደረገ አስተዳደግ መኖሩ ነው። ሴቶች ታዛዥ እንዲሆኑ ተደርገው ነው የሚያድጉት። ይህም ተካትቶ ባህል፣ አኗኗር፣ በማህበረሰቡ የሚደርሰው ተጽእኖና መገለል በመፍራት ልጆቻቸውን ይድራሉ፤ ልጃቸው ቆሞ ቀር እንዳትባል ሲሉ። በአንድ በኩል ይህን ጠልተው በሌላ በኩል ህጉ ስለሚከለክላቸው ጋብቻውን ደብቀው ያደርጉታል።

የማኅበራዊ ዘርፍ አንትሮፖሎጂስት የሆኑት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ሌላው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ነበሩ። እርሳቸውም በተለይ ያለእድሜ ጋብቻ በተግባር የሚታይበትን ብዙ ምክንያት በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል። በማብራሪያቸው መግቢያ ላይ በታዳጊ አገራት ላይ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑ ልጃገረዶች ከአስራ ስምንት ዓመት በታች እንደሚዳሩ ይጠቅሳሉ። ይህም በወሊድ ጊዜ ሞትን እንዲሁም የፌስቱላ ችግር እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው።

እንደጥናቱ ዝርዝር ዘገባ ያለእድሜ ጋብቻ አንዱ መንስኤ ድህነት ነው። በተጨማሪም የቤተሰብ ሁኔታና የወላጆች ግፊት ይጠቀሳል። በተያያዘም ያለእድሜ ጋብቻ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የቀለም ትምህርት ያላገኙት ይበዛሉ።ሥራና ትምህርትን አንድ ላይ ማስኬድ ስለሚከብዳቸው አንዳንዶች በፍላጎት ከጫና እና ከቁጥጥር እንዲሁም ከቤት ሥራ ማምለጥ ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ አማራጫቸው ጋብቻ ይሆናል።

በእነዚህ ሁለት ጥናቶች ላይ የቀረቡት ዝርዝር ዘገባዎች በርካታ ቢሆኑም ለምልከታ ያህል እኛ ይህንን አነሳን። በጥቅሉም ዛሬ ድረስ በተለያዩ ክልል ከተሞችና በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ያለእድሜ ጋብቻ በስፋት አለ። በአንዳንድ ስፍራዎች ተደብቆ መከናወኑ አልሰወረውም። ነገር ግን ማለፍ የማይኖርብንን አንድ ጉዳይ ላስከትል፤ ጥናታዊ ጽሑፎቹ ላነሱት ጉዳይ ምን መፍትሄ አስቀምጠዋል? በጥቅሉ እንደሚከተለው ነው።

አዎን ያለእድሜ ጋብቻን የሚከለክል ህግ አለ፤ ግን አልተተገበረም፤ ይህም ክፍተት ነው። በተለይ ዶክተር ጉዳይ እንደገለጹት እነዚህን ሰዎች በቀጥታ «ያለእድሜ ጋብቻ ጥሩ አይደለም» ብሎ መንገር የበለጠ ተቀባይነትን ያሳጣል፤መረጃን እንዳይሰጡና ድብቅ እንዲሆኑም ያደርጋል።ደግሞም የሚያደርጉትን ለማድረጋቸው በቂ ምክንያት ይሰጣሉ። ለምሳሌ አንዲት ሴት ትዳርን አማራጭ ማድረጓ አንድም ከጥቃት ለመከላከል ጠባቂ ወንድ ስለሚያስፈልጋት ይሆናል።

ነገር ግን መፍትሄ ማምጣት ከተፈለገ በማኅበረሰቡ ተሰሚና ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉትን መያዝና በእነርሱ ውስጥ መናገር ነው። በዚህም መሰረት ለውጥ ሲያመጡ ሽልማት መስጠት። በቤት ውስጥም በግልጽ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ብሎም የልጅ አስተዳደግ እንዴት መሆን እንዳለበት ማሳየት። ዶክተር ጉዳይ ጨምረው እንደገለጹት የሴቶች ጉዳይ ቢሮውን ማሳደግ እንዲሁም ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግና በጥቅሉ ምን ማድረግ እንደሚቻል መስመር ማበጀት ያስፈልጋል።

በተያያዘም ዶክተር አሉላ የሴት ልጆች በተለይ ለደሃ ቤተሰቦች ነጻ የትምህርት እድልና ተጨማሪ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። የአባቶች መማር ከእናቶች መማር የበለጠ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እንደሚችልም  እምነታቸውንም ገልጸዋል። እንዲህም አሉ፥ ዶክተር አሉላ «ተጨማሪ ህጎችን ማውጣት ጥሩ ነው። ነገር ግን የኅብረተሰቡ አመለካከት እስካልተለወጠ ድረስ ህጎቹን በማጠንከር ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ማመጣት አይቻልም»

አቀንቃኙ «ለታናሿም ልስጋ» እንዳለ ለቀደሙት የተደረሰላቸው ባይሆን እንኳን አሁን ለሚመጡት ሴት ልጆችና ህጻናት ዛሬ ሊደረስላቸው ይገባል። እንዲህ ያሉ ጥናቶችም እውነታውን አመላክተው ተግባራዊ ለውጥን የሚያነቃቁ ናቸውና በዛው ልክ ሊታዩ ይገባል። ግንዛቤ መስጠቱን በማስፋፋት ከዚህ በኋላ ለታናሿ እንዳንሰጋ የሚመለከተው ሁሉ በጋራ እንዲሠራ ጥሪው በዚሁ ይቀርባል፤ ሰላም!

 

ሊድያ ተስፋዬ