ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የእናት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርና የሕግ ባለሙያ

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ተወልደው ያደጉት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉትም በአሶሳ ከተማ ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ወስደዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ  አግኝተዋል፡፡ ከአሶሳ ወጥተው አዲስ አበባ ከተማን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ለመማር ተመድበው በመጡበት ጊዜ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ መጀመሪያ ወደ ሥራው ዓለም የቀላቀሉት ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴርን ከለቀቁ በኋላ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ብዙም ያልገፉበትን የዳኝነት ሥራ ለቀው በሕገ መንግሥት ኮሚሽን ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በተለይ በሕገ መንግሥት ኮሚሽን መሥራታቸው ይበልጥ የሚታወቁበትን የሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርን ለመመሥረት ዕድል ያገኙበት ነበር፡፡ እንደ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ያሉ ድርጅቶችም ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በ11 ሴቶች አደራጅነት የተቋቋመው የእናት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ ዳዊት ታዬ ከሥራቸውና ከግል ሕይወታቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ በሕግ ባለሙያነትዎ በተለይም የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን በመመሥረት ይታወቃሉ፡፡ የሕግ ትምህርት እንዴት ሊመርጡ ቻሉ? በአጋጣሚ ነው በፍላጎት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- መርጬ የገባሁበት ትምህርት ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባትም የመጀመሪያ ምርጫዬ አድርጌ የሞላሁት ሕግን ነው፡፡ ዕድለኛ ሆኜ የመጀመሪያ ምርጫዬን ነው ያገኘሁት፡፡ ቤተሰቦቼ በትምህርት ጥሩ ግንዛቤ ነበራቸው፡፡ ልጆቻቸው መሥራትና ማጥናት እንዳለብን ያውቃሉ፡፡ ሁላችንም ትምህርታችን ላይ ትኩረት እናደርግ ነበር፡፡ በጊዜው እንደነበሩት ልጆች ይህንን ያህል የቤት ውስጥ ሥራ አልነበረብንም፡፡ በተለይ የእኔ ትኩረት የውጭ ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ መላላክ አዘወትር ነበር፡፡ ትምህርት ላይ ጎበዝ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚያን ጊዜ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ እንዴት ነበር? ሴቶችን ለማስተማርስ በወቅቱ የነበረው የኅብረተሰብ አመለካከት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይማራሉ፡፡ አሶሳ ከአዲስ አበባ ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ የራቀ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን አካባቢው ዘመናዊ የሚባል አመለካከት የነበረበት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ በንግድና በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የነበሩበት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ያህል የከበደ የባህል ጫና አልነበረም፡፡ ስለዚህ የሚማሩ ሴቶች ነበሩ፡፡ በመሀል አግብተው የሚያቋርጡ አሉ፡፡ ቁጥራችን ትንሽ ቢሆንም የሚማሩ ሴቶች ነበሩ፡፡ ካልረሳሁት በአንድ ክፍል ከ20 እስከ 30 በመቶ ሴቶች ነበርን፡፡ ይህንን ያህል ጫና የለም፡፡ አሶሳ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ነዋሪዎች ያሉባት ነች፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በፍቅር የኖርንበትም ከተማ ነች፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ከእናቴ ጋር ሄደን ነበር፡፡ ከተማ ውስጥ በእግር ስንጓዝ የሼህ ኦጀሌ አራተኛ ትውልድ የሆነች ሴት አገኘን፡፡ አስታወሰችን፡፡ እኛም አውቀናት ነበር፡፡ እናቴ ላይ ተጠምጥማ አለቀሰች፣ አለቀስን፡፡ ይህ ስሜት የከተማው ነዋሪዎች ፍቅር ምን ያህል እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ትምህርት ለመማር የመረጡበት ምክንያት አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ያገባኛል የሚል ስሜት ነበረኝ፡፡ ይህንን የያገባኛል ስሜቴ ግን በጊዜው ሕግ ነው፡፡ መብት ነው የሚባለውን ነገር አውቄ አልነበረም፡፡ ዝም ብዬ አንድ ያልተገባ ነገር ሳይ ጣልቃ እገባለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙጊዜ እንደ ምሳሌ የማነሳው ከታላቅ ወንድሜ ጋር ትምህርት ቤት ስንገባ እሱ የዋህ ስለሆነ ልጆች ያስቸግሩት ነበር፡፡ ይመቱትና ያስለቅሱትም ነበር፡፡ ወላጆቼ ደግሞ ይህንን ስለተረዱ እሱን እንድጠብቀው አዘውኝ ነበር፡፡ እንደተባለውም ወንድሜ ከእኔ ጋር ሲሆን ማንም ሰው አይደፍረውም፡፡ ሌላው በቤት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ያላግባብ ሰው ሲናገራቸው ወይም አግባብ ያልሆነ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ደስ አይለኝም፡፡ ደስ ያለማለት ብቻ ሳይሆን መሀል ገብቼ ይህ መሆን የለበትም ማለት የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነበር፡፡ አልፈራም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሆነ ነገር ግጭት ከተፈጠረ ደብድቤ የማሸነፍ ወኔው ነበረኝ፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ትልቅ ከሆንን በኋላ ከዚሁ ታላቅ ወንድሜ ጋር እጋጫለሁ፡፡ እሱ 11ኛ ክፍል፣ እኔ ደግሞ 10ኛ ክፍል ነበርን፡፡ ተከታታይ ስለሆንም የምንጋጭበት ጊዜ አለ፡፡ አንድ ቀን ግን የመረረ ግጭት በመካከላችን ተፈጠረ፡፡ አባቴ አልነበረም፣ ሥራ ነበር፡፡ እናቴ ግራ ገብቷት በቀጥታ ከግቢ ወጥታ ያኔ የአብዮት ጥበቃ ከሚባሉት ታጣቂዎች አንዱን ይዛ መጥታ አልቻልኳትም አስወጡልኝ ብላለች፡፡ ሰውዬው ጠመንጃ ይዞ ነበርና አስፈራራኝ፡፡ እኔ ተናድጄ ስለነበር ‹‹እንዳትደርስብኝ፣ ከደረስክብኝ ችግር ይፈጠራል፤›› አልኩት፡፡ ሰውዬውም ሁኔታዬን አየና ‹‹ሆ… እቺ ወደፊት ባልዋንም ትደበድባለች፣ እኔ ምንም ላደርግ አልችልም፤›› ብሎ በመጣበት እግሩ ተመለሰ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ኃይለኛ ነበሩ፣ አሁንም ይህ ባህሪ አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በወቅቱ አዎ፡፡ አሁንማ ብዙም አይደለሁም፡፡ እያደግሁ ስመጣ የተውኩት ይመስለኛል፡፡  ያ ኃይለኝነቴ በሌላ መንገድ የሚታይ ይመስለኛል፡፡ የጀመርኩትን ሥራ በእልህ ወደ መጨረስ የገባሁ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ትክክለኛ የሆነ ሐሳብ አምጣልኝ፣ ይህንን ለማሳካት ወደኋላ አልልም፡፡ ‹ሪስክ› መውሰድ ያለብኝንና የሌለብኝን በሚገባ እለያለሁ፡፡ መሥራት ያለብኝ ነገር ከሆነ ትንሹን ነገር ወደ ትልቅ ማሸጋገር እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዩኒቨርሰቲ ከወጡ በኋላ ወደ ሥራ ዓለም የገቡት እንዴት ነው? መጀመርያ የተቀጠሩስት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ያው እንደምታው ከዩኒቨርሲቲ ከወጣህ በኋላ ሥራ የምታገኘው በምደባ ነው፡፡ እኔም ንግድ ሚኒስቴር ተመደብኩ፡፡ ያኔ ንግድ ሚኒስቴር ፒያሳ አሁን ከስታትስቲክስ ባለሥልጣን ፊት ለፊት ነበር፡፡ ከሥራው ጋር ምንም መጣጣም አልቻልኩም፡፡ ብዙም አልጣመኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የተመደቡበት የሥራ መደብ ምን ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ‹ጁነየር ሊጋል ኤክስፐርት› ተብዬ ነው የተመደብኩት፡፡ በሥራው ላይ ብዙም ደስታ አላገኘሁበትም፡፡ ጠዋት ሥራ እገባና ብዙ ጊዜ ከቢሮ ወጥቼ ፀሐይ እሞቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን አለቃችን ይመጣና ‹ምንድነው ውጭ የምትሠሪው?› ሲለኝ ቢሮ ውስጥ ሰለቸኝ አልኩት፡፡ እሱም ‹እንዲህ ማድረግ አይቻልም፣ ይህ እኮ የመንግሥት ሥራ ነው፣ በሥራ ሰዓት ቢሮ ውስጥ መሆን አለብሽ› ያለኝን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ፀሐይ ላይ የሚቀመጡት የሚሠራ የለም ማለት ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ሥራውማ አለ፡፡ ነገር ግን ይህንን ያህል ትኩረቴን የሚወስድ ሥራ አላገኘሁም፡፡ በዚህ ሁኔታ ንግድ ሚኒስቴር አንድ ሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ ነው የሠራሁት፡፡ ከዚያ ያኔ በደርግ ጊዜ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ብዙ ዳኞች በልምድ ነበር የሚሠሩት፡፡ ዲግሪ ያላቸው ዳኞች ውስን ናቸው፡፡ ከዚያ አዲስ ፖሊሲ ተቀረፀና የሠለጠኑ ዳኞች መሾም አለባቸው የሚል ነገር ሲመጣ እኔና ሌሎች ጓደኞቼ ለዳኝነት ሥራ አመለከትን፡፡ ተቀበሉን፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሾምን፡፡ ዳኛ ሆንን፡፡ ግን ዕድሜያችን ገና ነው፡፡ ዳኝነት ብዙ ልምድ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ዳኛ ለመሆን ዕድሉን አገኘን፡፡ የስድስት ወራት ልምድ ካላቸው ዳኞች ጋር ከሠራን በኋላ ራሳችንን ችለን  ተመደብን፡፡ እኔ ወንጀል ችሎት ተመደብኩኝ፡፡ የክስ መዝገቦችን ለብቻዬ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ሥራዬን ለማገዝ በምመለከታቸው ጉዳዮች ሰዎችን አማክራለሁ፡፡ በዚህ መንገድ እየሠራሁ እያለ አንዳንድ የሚከብዱኝ ሁኔታዎች ተፈጠሩ፡፡ እንዲያውም   ትዝ የሚለኝ የአንድ ጥበቃ ሠራተኛ ጉዳይ ነው፡፡ እኚህ ሰው የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ በጥበቃ ሠራተኝነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ያኔ ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ ይሆናቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ በእርሳቸው የጥበቃ ሰዓት ሌባ ትምህርት ቤት ውስጥ ይገባና ከክፍል ውስጥ ፍሎረሰንትና ሌሎች ዕቃዎች ይሰርቃል፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ንብረት ከጠፋ የሚታይበት ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ነበር፡፡ ከበድ ይላል፡፡ በዚህ ሕግ አነስተኛ ቅጣት ተብሎ የተቀመጠው የአምስት ዓመት እስራት ነው፡፡ ከዚያ እኚህ የጥበቃ ሠራተኛ በተከሰሱበት ክስ ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ እሳቸውም አመኑ፡፡ እኔ ደግሞ የሰውዬውን ሁኔታ ስላየሁ የቅጣት ማቅለያ መንገድ ፈልጌ አንድ ዓመት እንዲቀጡ ፍርዱን ጻፍኩ፡፡ ከፍርዱ በፊት እሳቸው ‹‹ደመወዜ ሰላሳ ብር ነው፡፡ ስምንት ልጆች አሉኝ፡፡ ሚስቴ በቅርቡ ሞታለች፡፡ ስለዚህ እኔ እስር የሚወሰንብኝ ከሆነ ልጆቼም መበተናቸው ነው፤›› ብለው አመልክተውም ነበር፡፡ ግን ቅጣቱን ከዚያ በታች ማድረግ የምችልበት የሕግ አግባብ አልነበረም፡፡ አልችልም፡፡ ፍርዱን ችሎት ላይ አነበብኩ፡፡ በኋላ ግን ቢሮዬ ገብቼ ለቅሶዬን አቀለጥኩት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ማድረግዎ ግን ሙያውን መጋፋት አይሆንብዎትም ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አንዳንድ ጊዜ ሳታስበው ስሜትህ የሚነካበት ጊዜ አለ፡፡ የእሳቸው ሁኔታ ረበሸኝ፡፡ ልጅም ስለሆንኩ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳኛ ሆነው ሲሾሙ ዕድሜዎ ስንት ነበር? ሲያለቅሱስ ሰው አላየዎትም?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ያኔ 26 ዓመት አካባቢ ነኝ፡፡ በነገርህ ላይ ቢሮዬ ቁጭ ብዬ ሳለቅስ ጸሐፊዎቹ መጡና ሳቁብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምንድነው በእርስዎ ለቅሶ የሚስቁት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ዘንድሮ ደግሞ ምን ዓይነት ዳኞች ነው መንግሥት መሾም የጀመረው ብለው ነው፡፡ ነገር ግን ጠጋ ብለው አባበሉኝ፡፡ ‹አይዞሽ መበርታት አለብሽ፣ ዳኛ ነሽና መጠንከርም ይኖርብሻል› ሁሉ አሉኝ፡፡ ግን ከዚያ በኋላ ይህ ሥራ ለጊዜው ለእኔ የሚሆን አይደለም ወደሚለው ሐሳብ እንድገባ አደረገኝ፡፡ የዳኝነቱ ሥራ ለእኔ የሚሆን እንዳልሆነም ይሰማኝ ጀመር፡፡

ሪፖርተር፡- እንዳሰቡት ዳኝነቱን ለቀቁ? በዳኝነቱ ምን ያህል ጊዜ ሠሩ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ወደ ሦስት ዓመት አካባቢ ሳልሠራ አልቀርም፡፡ ከዚያ በኋላ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለሁ ኢሕአዴግ መጣ፡፡ እንዲያውም በዚያ ጊዜ የነበሩ ዳኞች ወደ ክልል ይመደቡ ተባለ፡፡ እኔም ልቤ ተከፍሎ ነበር፡፡ በዚህ መሀል አንድ ስብሰባ ላይ እነ አቶ ክፍሌ ወዳጆና እነ አቶ አብዱል መሐመድን አገኘሁ፡፡ አጋጣሚው በጋራ ለማውራት ዕድል ፈጥሮልኝ ነበር፡፡ እነሱም ምንድነው የምትሠሪው ብለው ሲጠይቁኝ ዳኛ ነኝ አልኳቸው፡፡ ሳቁ፡፡ አሁን ግን ሥራ መለወጥ እፈልጋለሁ አልኳቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የሕገ መንግሥት ኮሚሽን እየተቋቋመ ነበር፡፡ ዳኝነቴን መልቀቅ እንደምፈልግ ገልጫለሁና ለሕገ መንግሥት ኮሚሽኑ ‹ሪሰርቸር› እየተፈለገ ነውና አንቺም ከፈለግሽ ማመልከት ትችያለሽ አሉኝ፡፡ አመለከትኩ፡፡ ሕገ መንግሥት ኮሚሽን ተቀጥሬ ገባሁ፡፡ ይህ የሙያ አቅጣጫ ቀያሪ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለት ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ውስጥ የምሠራው ሥራ ብዙ ትኩረት በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንዳደርግ ዕድል ሰጠኝ፡፡ ይህ ደግሞ ልቤ የሚያስበው ነው፡፡ ሁለተኛ ከአቶ ክፍሌ ወዳጆ ጋር መሥራት ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ምክንያቱም በሕይወት ውስጥ ብዙ ሊያስተምሩህ ከሚችሉ ሰዎች ጋር መሥራት ቀላል አልነበረም፡፡ በዚያ ቆይታዬ ስለሕዝብ ሥራ፣ በራስ ስለመተማመንና ብዙ መልካም ባህሪዎች ከእሳቸው ብዙ ወስጃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥት ኮሚሽን ውስጥ ዋነኛ ሥራዎ ምን ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ሪሰርች አሲስታንት ነው፡፡ በተለይ የሰብዓዊ መብት ፓናል የሚባል አለ፡፡ የሕገ መንግሥት ኮሚሽን አባላት የሆኑ ሃያ ሰባት ኮሚሽነሮች አሉ፡፡ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ሊመንበር ነበሩ፡፡ አቶ ዳዊት ዮሐንስ ደግሞ ጸሐፊ ነበሩ፡፡ ይህ በኮሚሽኑ ሥር ከነበረው ቡድን የሰብዓዊ መብት የሚመለከተውን ድጋፍ አደርጋለሁ፡፡ ‹ሪሰርች› አደርጋለሁ፡፡ ኮንፈረንስ ሲዘጋጅ እናግዛለን፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑን ሥራ በሚደግፉ ተግባራት ላይ እንሳተፋለን፡፡ በሕገ መንግሥት ኮሚሽኑ ውስጥ መሥራቴ ደግሞ ወደ ሌላ ነገር አሸጋገረኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ወዴት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን እንድመሠርት ዕድል የሰጠኝ በኮሚሽኑ ውስጥ መሥራቴ ነው ልል እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንዴት መሰለህ የሆነው እኔና አንድ የኮሚሽኑ አባል (ወ/ሮ አፀደወይን) ለሥልጠና ዘ ሔግ ተላክን፡፡ ሥልጠናው የሦስት ሳምንት ነበር፡፡ በዚህ ሥልጠና ላይ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ሴቶች ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ በዚያ ፕሮግራም ላይ ልምድ ስንለዋወጥ አንድ ከኬንያ የመጣች ወጣት የሕግ ባለሙያ በአገራቸው የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር አቋቁመው እየሠሩ መሆኑን ነገረችን፡፡ ማኅበሩ ስለሚሠራውም ሥራ በሰፊው አብራራችልን፡፡ ማኅበሩ በተለይ የሴቶች ሕግ እንዲሻሻል ስለሚሠራው ሥራ አስረዳችን፡፡ ለሴቶች ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት እየሰጡ እንዳሉና ስለሴቶች መብት እንዴት እያስተማሩ እንደሆኑ ሁሉ ሲነግረን በጣም ገረመን፡፡ ምክንያቱም እኛ በሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ለውጥ ለማምጣት ዜጎች መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አናውቅም፡፡ ምክንያቱም በደርግ ጊዜ ጨለማ ውስጥ ነበርን፡፡ ስለዚህ ይህንን መስማታችን ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ አውሮፕላን ውስጥ ከሕገ መንግሥት ኮሚሽን አባል ከነበረችው ዳኛ ወ/ሮ አፀደወይን ጋር እኛም እንዲህ እናደርጋለን ብለን እያወራን መጣን፡፡ አዲስ አበባ ከደረስን በኋላ ስለሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ስለማቋቋም ማብሰልሰላችንን ቀጠልን፡፡ ይህንን ሐሳብ ይዤ አቶ ክፍሌን አማከርኳቸው፡፡ ‹በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው፣ እኔም እረዳችኋለሁ ግፉበት› አሉን፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ ሕገ መንግሥቱን የማርቀቅ ሥራ እየተገባደደ ነበር፡፡ ማኅበሩን ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮፖዛል ጻፍን፡፡ አቶ ክፍሌም ቃል በገቡልን መሠረት ረዱን፡፡ ማኅበሩን ለማቋቋምና ድጋፍ ለማግኘት መጀመርያ የሄድነው ሲዳ ካናዳና ኔዘርላንድ ኤምባሲ ነው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ጥያቄያችንን ተቀበሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመሪያውን ፕሮፖዛል ስትጽፉ የማኅበሩን ዓላማዎች ከምን አንፃር ቃኛችሁት? ግባችሁስ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በሌሎች አገሮች ካሉ ተመሳሳይ ማኅበራት ብዙ ነገር ወስደናል፡፡ ለማኅበሩ ዋና ዋና ዓላማዎች ብለን ካስቀመጥናቸው ጉዳዮች አንዱ ለሴቶች ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሴቶችና የሕፃናት መብት በጥሩ ሁኔታ ተካትቷል፡፡ ነገር ግን ከሕገ መንግሥቱ ሥር ያሉ የበታች ሕጎች ሴቶች ላይ አድልኦ እንዳደረሱ ነው፡፡ ምክንያቱም የድሮ ሕጎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ለሴቶችና ለሕፃናት የሰጠው መብት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ስለዚህ ከታች ያሉት ሕጎችም ይህንን ሕገ መንግሥት ተንተርሰው መስተካከል አለባቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ሕጎችን ለማሻሻል የውትወታና የጉትጎታ ሥራ መሥራት አለብን የሚለውንም ጉዳይ ማኅበራችን ሊሠራቸው ይገባል ካልናቸው መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ሌላው ማኅበሩ ይዞት የተነሳው ዓላማ ሕዝብን ስለሴቶች መብት ማስተማር ነው፡፡ ሴቶችን ስለመብታቸው ማስተማር የሚለውም ይገኝበታል፡፡ እነዚህን ሦስት ዓላማዎች በዋናነት ለማራመድ የተነሳንባቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ በማኅበራችሁ የሚሰባሰቡ በቂ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ነበሩ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ነበሩ፡፡ ስንጀምር ወደ 50 ነበርን፡፡ በኋላ የዋና የማኅበሩ አባላት ወደ 150 ደርሰው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩን ዓላማዎች እንዳሰባችሁት ማሳካት ችለናል ብላችሁ ታስባላችሁ? በተለይ ሥራ በጀመራችሁበት ወቅት? ለመተግበር አልተቸገራችሁም?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንቅስቃሴያችን ካሰብነው በላይ ሆነ፡፡ ቢሮውን ስንከፍት ሴቶች ስለሥራችን አውቀው እንዴት ይመጣሉ ብለን ተጨንቀን ነበር፡፡ አንድ ሁለት ሳምንት ጭንቅ ነበር፡፡ ነፃ የምክር አገልግሎት እንሰጥበት የነበረውን መስኮት ከፍተን ሰው ነበር የምንጠብቀው፡፡ በኋላ ሺዎች የሕግ ምክር ፈላጊዎች መጡ፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ካሰብነው በላይ የሕግ ምክር አገልግሎት የሚፈልጉ ሴቶችን አስተናገድን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ምክር አገልግሎት ሽተው የሚመጡ ሴቶች የሚጠይቁት ጭብጥ ምን ምን ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የተጠቁ ሴቶች፣ በትዳር ላይ ችግር የገጠማቸው፣ ሥራ ላይ በአለቃዬ ትንኮሳ ተደረገብን የበማለት ጉዳያቸውን ይዘው የመጡ ሁሉ ነበሩ፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ይዘን አስተናገድን፡፡ በምርምር ረገድም ስለቤተሰብ ሕግ፣ በወንጀለኛ መቅጫ በዜግነት ሕግና በመሳሰሉት ጉዳዮች ብዙ ሥራ ሠራን፡፡ ያኔ ትዝ ይለኛል፡፡ ህሊና ታደሰ የምትባል ጎበዝ ልጅ ነበረች፡፡ የታደሰ ታምራት ልጅ ናት፡፡ ጎበዝ ሪሰርቸር ናት፡፡ አሁን አሜሪካ ነው የምትኖረው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ችግሮች በጥናት ተለይቶ እንዲወጣ አድርጋለች፡፡ ያሉትን ክፍተቶች ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው አንፃር ተለይቶ ተሠራ፡፡ የቤተሰብና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ያለውን ክፍተት ዘርዝረን በማውጣት መድረክ አዘጋጅተን ሕዝብ በማወያየት ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርገናል፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ላይ የቤተሰብ ሕግን አስመልክቶ ለዘጠኙም ክልሎች ላክን፡፡ ምን መሻሻል እንዳለበት የሚያመለክቱ ነጥቦችን አካተን ለላክነው ደብዳቤ የተሰጠንንም ምላሽ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ መሠረት መንግሥትም አጀንዳውን ተቀበለው፡፡ ፓርላማው ውስጥ የሴቶች ጉዳዮች እንደ ቋሚ ኮሚቴዎች ትልልቅ መድረኮችን በተያያዘ ሁኔታ ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ንቅናቄው ተቀጣጠለ ማለት ይቻላል፡፡ በሕዝብ ማስተማሩ ተግባር ብዙ አዳዲስ ነገሮች ወደ መድረክ ወጡ፡፡ የተደበቁ ነገሮች ወጡ፡፡

ሪፖርተር፡- የተደበቁ ነገሮች ወጡ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ተደብቀው የወጡትስ ምንድናቸው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ‹የሴቶች ጥቃት› የሚባል ቋንቋ አልነበረም፡፡ የወንጀለኛ መቅጫው የኃይል ተግባር ነው የሚለው፡፡ እኛ ደግሞ ስለጥቃት ስንናገር ወሲባዊ ነው፣ የኃይል ጥቃት ነው፣ ድብደባ አለበት፡፡ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ነው፡፡ ስለዚህ የኃይል ተግባር የሚለው አይገልጸውምና ምን እናምጣ ብለን ብዙ አሰብን፡፡ የሴቶች ጥቃት ተባለ፡፡ ዛሬ ጥቃት የምንለው ነገር ገላጭ ቃል ሆኖ እየተሠራበት ሲሆን፣ ይህንን ለማምጣት ብዙ አስበናል፡፡ ዛሬ በፖሊሲም የሴቶች ጥቃት የሚለው የመሥሪያ ቋንቋ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ አንዳንዴ ሰዎች ሲከራከሩበት እሰማለሁ፡፡ በትንኮሳና በጥቃት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ጥቃት እንግዲሀ አካላዊም፣ ወሲባዊም፣ ሥነ ልቦናዊውም ይሁን በሴቶች ላይ በማንም እንግዳ ደራሽ የሚደርስ ጉዳት ነው፡፡ ነገር ግን በባልና በሚስት መካከል ቢሆንም ጥቃት ልንለው እንችላለን፡፡ ወሲባዊ ትንኮሳ ‹‹ሴክሽዋል ሐራስመንት›› ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ወሲባዊ ትንኮሳ የአማርኛ ቃል አልነበረውም፡፡ አንድ ጊዜ ማርች 8 በተመለከተ የሬዲዮ ፕሮግራም ነበረን፡፡ ከሬዲዮ ፕሮግራሙ በፊት ‹‹ስለሐራስመንት›› ቢነሳ በአማርኛ ምን ብዬ ነው የምናገረው ብዬ አሰብኩ፡፡ ገላጭ ነገር እፈልግ ነበርና በዚህ ረገድ ሊያግዘኝ ይችላል ብዬ ወዳሰብኩት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ (ሶሽዮሎጂስት ናቸው) ‹‹ሴክሽዋል ሐራስመንት›› እንዴት ነው የሚተረጎመው?›› ብዬ በስልክ ጠየቅኩት፡፡ መጀመሪያ ‹‹የወሲብ ክጀላ›› አለኝ፡፡ ይህ አባባል አልሳበኝም ነበርና እንዳልተመቸኝ ስገልጽለት ወዲያው ‹‹የወሲብ ትንኮሳ›› አለኝ፡፡ ይህ ገላጭ ነበርና እኔም ይህንን ተጠቀምኩ፡፡ በዚሁ ፀና፡፡ ታሪኩን ግን ብዙ ሰው የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ የወሲብ ትንኮሳ ግን ከሥራ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከአለቃና ከበታች ሠራተኛ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ሰው ሥልጣኑን ተጠቅሞ የሚፈጸመው ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ አስተማሪና ተማሪ፣ አለቃና ሠራተኛ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በሴቶች ላይ የሚያደርሱት የወሲብ ጫና ነው፡፡ የወሲብ ትንኮሳ ወይም ‹‹ሴክሽዋል ሐራስመንት›› ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ልመልስዎ፡፡ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ይዛችሁ ከተነሳችሁ በኋላ የሠራችሁት ሥራ ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ ሕጎች ተለውጠዋል፡፡ ይኼ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ታሪካዊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሕግ ሲለወጥ የአምስትና የአሥር ሺሕ ሰዎች ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የሴቶች ቁጥር ወደ 50 ሚሊዮን ነው፡፡ ስለዚህ የሕጉ መለወጥ እነኝህን ሴቶች ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች በማኅበሩ መፈጠር ሰፊ ግንዛቤ ፈጥሮላቸዋል፡፡ እኔ ከእንዲህ ዓይነት ሥራ ከወጣሁ ወደ አሥር ዓመት ሊሆነኝ ነው፡፡ ነገር ግን የትም የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤት ስሄድ ሰዎች የሚሰጡህ ምሥጋና የማኅበሩ ሥራ አንድ ምዕራፍ የፈጠረው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን ከማኅበሩ እንቅስቃሴ ራቁ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ስምንት ዓመት ሠራሁ፡፡ እንዲያውም ጓደኞቼ ለምን አትቀጥይም ይሉኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ በፍቅር የምትሠራው ነገር ጭልጥ አድርጎ ይወስድሃል፡፡ በማኅበሩ ሥራዬ ጠዋትና ማታ ሳላውቅ ሠርቻለሁ፡፡ በዓል መቼ እንደሆነ እንኳን አላውቅም፡፡ አራት ዓመት እንዲህ ሠርቻለሁ፡፡ ልጆችም ከወለድኩ በኋላ ልጆቼን በቅርጫት ውስጥ ቢሮ ነበር አጠባቸው የነበረው፡፡ ያለኝን አቅም ሁሉ የሰጠሁበት ሥራ ስለነበር ነገሮች መስመር ከያዙ በኋላ፣ አንድ ቦታ ላይ አሁን ደግሞ ሌላ ነገር ማሰብ አለብኝ ወደሚል ነገር የገባሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ወቅት በወንዶች ‹ለከፋ› የሚባለው ዓይነት ነገር ገጥሞዎት ያውቃል? ጉንተላም ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ክጀላ፡፡ ለሴቶች መብት ጥበቃ የገቡት እርስዎ በግል የገጠመዎት ነገር ስለነበር ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ክጀላ ያለ ነው፡፡ በግሌ ብዙ ልምድ አላደረግኩም፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ብዙ ሰው ይጠይቀኛል፡፡ ለምሳሌ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ ገባሽ? ለሴቶች ለመከራከር ያነሳሳሽ በአንቺ ላይ የደረሰ ነገር ስለነበር ነው ወይ? ይሉኛል፡፡ በቤተሰቦቼ የማየው አለ፡፡ እንደ ማንኛውም እናት ሴት ብዙ በደል ደርሶባት አይቼ ነው ያደግኩት፡፡ በአካባቢዬም የማየው ነገር ነበር፡፡ ይህ ውስጤ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህ ጥያቄ የለውም፡፡ ስለዚህ በከፊል ለዚህ ጉዳይ ጊዜዬን የሰጠሁት ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ላይ ግን በቀጥታ የገጠመኝ ነገር አለ አልልም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ስማር ከ50 ተማሪዎች ውስጥ ሴት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በኋላ ሁለት ዓመት ከተማርኩ በኋላ የእኔ ‹ሲኒየር› የነበሩ ኮርስ ያልጨረሱ ከእኔ ጋር ሦስት ሴቶች መጥተዋል፡፡  አንዳንድ ጊዜ የእኔም አመለካከት ሊሆን ይችላል አላውቅም፣ የማስታውሰውና በወንዶች የተደረገብኝ ግፊት ብዙም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- መቼም ሰው ያፈቅራል፣ ትዳር ይመሠርታል፣ ይወልዳል፣ እርስዎስ ይህንን የሕይወት መስመር እንዴት እንደተቀላቀሉ ያስታውሳሉ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ ለብቻዬ ሆኜ ብዙ ኖሬያለሁ፡፡ ቶሎ አላገባሁም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ከሕገ መንግሥት ኮሚሽን ከወጣሁና የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን ከመሠረትን ከአራት ዓመት በኋላ ቆይቼ ነው ያገባሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን ዘግይተው ለማግባት ፈለጉ? ለጋብቻ መዘግየትዎ ምክንያት ነበረው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- መዘገየት ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ነገር የጊዜ ገደብ የምትይዝለት አይደለም፡፡ አጋጣሚና የተለያዩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት ያላገባንና ነፃ ሴቶች በራሳችን ነው የምንኖረው፡፡ ጓደኛ ይዘህ መውጣት መግባት ግን ይኖራል፡፡ ትዳር ጊዜውን ጠብቆ ነው የሚመጣው፡፡ ባለቤቴ ዶ/ር አርዓያ አስፋው ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር የተዋወቅነውና የተገናኘነው አንድ ሪሴፕሼን ላይ በአጋጣሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተዋወቃችሁ በአጭር ጊዜ ወደ ጋብቻ የገባችሁት እንዴት ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አዎ ብዙ የሚያስማማን ነገር ስለነበረን ነው፡፡ ያኔ የማኅበሩ ጓደኞቼን ባል ላገባ ነው ስላቸው፣ ‹‹እንዴት! አንቺም ባል ታገቢያለሽ እንዴ?›› ያለችን ጓደኛ ነበረች፡፡ ‹‹አንቺን የሚያገባ ሁለት ሱሪ የታጠቀ ነው›› ብላ ቀልዳብኛለች፡፡ ትዳር እንደገና መፈጠር ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ባለቤቴ መልካም ሰው ነው፡፡ የምሠራውን በጣም ይደግፋል፡፡ ለዚህ ብዙ ምሳሌ ማቅረብ እችላለሁ፡፡ እንዲያውም የመጀመሪያ ልጃችን ሰናይት ተወልዳ አራት ወሯ ነበር፡፡ ኒውዮርክ የሚካሄድ ትልቅ ጉባዔ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ መሳተፍ ነበረብኝና ልሂድ አልሂድ በሚል ሐሳቤ ተከፈለ፡፡ ከዚያ ባለቤቴ ልጆች ወለድሽ ማለት የጀመርሽውን ዓላማ ትተያለሽ ማለት አይደለም፣ መሄድ አለብሽ ብሎ ሁሉ ያበረታታኝ እሱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ድጋፍ ያደርግለኛል፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ማንኛውንም ሥራ አንዱ ከሌላው ጋር መደጋገፍ አለበት፣ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በትዳር ዓለም 18 ዓመት ቆይተዋል፡፡ ግን ወደ ትዳር ለመግባት መጀመሪያ ጥያቄውን ማን አቀረበ? እርስዎ ወይስ ባለቤትዎ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በጥያቄ ነው ብለህ ነው? ‹‹ኮንሰንስስ›› [መግባባት] ብንለው ይሻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎና እርስዎን መሰል ሴቶች ብዙ ጊዜ ከቤት ውጭ በሥራ ታሳልፋላችሁ፡፡ ለቤት ጉዳይ ብዙ ጊዜ እንደሌላችሁ መገመት ይቻላል፡፡ እንዲያው ቤት ውስጥ በተለይ ማዕድ ቤት ጎራ ብሎ ማበሳሰል ይሞክራሉ? የሙያው ነገር እንዴት ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ዶሮ መበለት ከሆነ በደንብ እችላለሁ፡፡ እሠራለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር በጣም ባለሙያ የሆኑ ሴቶች በጣም ደስ ይሉኛል፡፡ ምክንያቱም ‹አርት› ነው፡፡ ምግብ በመሥራት ሰው ማስረዳት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ይህንንም ብዙ ጊዜ አደርጋለሁ፡፡ ግን በማዕድ ቤት ሥራ ላይ ይኼንን ያህል ባለሙያ ነኝ ብዬ ደፍሬ ለመናገር አልችልም፡፡ ብዙ ትኩረቴ አይደለም፡፡ ግን መሥራት ካለብኝ በደንብ እሠራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዴ ባሎች ሚስቶቻቸው የሚሠሩላቸውን ምግብ ይሻሉና ባለቤትዎ እባክሽ ይኼ አምሮኛልና ሥሪልኝ ብለው አያውቁም? መሥራትስ ችለዋል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እችላለሁ፡፡ ደስ ይለዋል፡፡ በቀጥታ ይኼ አምሮኛል ሳይሆን የሚለው አንዳንዴ ቀላል የሆኑ ነገሮችን ጠባብሼ ሳቀርብ በጣም ጥሩ ነው ይላል፣ ይፈልጋል፡፡ ዳር ዳር ይላል፡፡ በማዕድ ቤት አካባቢ መመርያ እንድሰጥ ይፈልጋል፡፡ ወደዚያ ቀረብ ያልኩ ቀን ደስ ይለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁል ጊዜ አያገኘውም፡፡ ዋና ትኩረቴ እንዳልሆነም ያውቀዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ልክ እንደ እርስዎ ያሉ ብዙ ጊዜ ሥራቸው ከቤት ውጭ የሚያደርጋቸውና ሥራ ላይ የሚያሳልፉ ሴቶች ለትዳር ምቹ አይደሉም ይባላል፡፡ ይስማሙበታል? ምክንያቱስ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ የባህሉም ሁኔታ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ሙያቸው ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ከሆነ፣ ትኩረታቸው ውጭ ያለ ሥራቸው ላይ ከሆነ ያንን በኅብረተሰቡ የተቀመጠ የተለመደ የሚና ክፍፍል አለ፡፡ ሴቶች እናቶች ናቸው፣ የቤት ውስጥ ኃላፊነት የእነርሱ ነው፣ እህል ማስፈጨቱ፣ ሽንኩርቱንም የመግዛት የእነሱ ነው፡፡ ስለዚህ ሴት ይህ ሚና እንዲኖራት ብዙ ወንዶች ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡ ይህንን ደግሞ ሴትዋ በሚፈለገው መጠን ማስተካከል ካልቻለች ውጥረት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሁለተኛው ግን በራስ የመተማመን ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደማየው በአገራችን የቤት ውስጥ ሥራን በተመለከተ አጋዥ ሰው አለ፡፡ ቀጥረህ ማሠራት ትችላለህ፡፡ ነገር ግን እኔ የበለጠ የሚፈጠረው ሴቷ ከጥገኝነት ነፃ ስትሆንና የራስዋ ገቢ ሲኖራት ባሎች የመደንገጥ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ግን ጎልቶ ይታያል ብለው ያስባሉ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በራስህ የምትተማመን ጎበዝ ከሆንክ የሚስትህ ገቢ ማደግ ያስደስትሃል፡፡ ጎበዝ ከሆንክ ሚስትህ ጠንካራ ሆና ማየት ያስደስትሃል፡፡ ግን ይህ ሁሉንም ይወክላል ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወ/ሮ መዓዛ ቀድሞ የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በመመሥረትና በዚያ ላይ በመንቀሳቀስ ነው፡፡ ቆይተው ደግሞ ወደ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው ገብተዋል፡፡ እንደሚታወቀው እናት ባንክን ከሌሎች አጋርዎችዎ ጋር በመሆን ማቋቋም ችላችኋል፡፡ እንዴት ወደ እዚህ ዘርፍ ገቡ? የእናት ባንክ አመሠራረትስ የተለየ ታሪክ አለው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ የቢዝነስ ሰው አይደለሁም፡፡ የቆየ ልምዴም ብዙ ከቢዝነስ የራቀ ነው፡፡ የእናት ባንክ መመሥረት በአጋጣሚ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሸራተን አዲስ ስብሰባ ተጠራን፡፡ አንድ የሴቶች ድርጅት ያዘጋጀው ስብሰባ ነው፡፡ የስብሰባው አጀንዳም ‹‹ሴቶች ቢዝነስ የሚሠሩበት ቦታ የላቸውም፣ ይህ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው›› የሚል ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ ከጎኔ ወ/ሮ ሣራ አበራ ነበረችና፣ ‹‹ሴቶች እኮ ብር ቢኖራቸው ቦታ መከራየት፣ ቦታ መግዛት ይችላሉ፡፡›› አለች፡፡ ከዚያም የዚህ ስብሰባ አጀንዳ መሆን የነበረበት ሴቶች ፋይናንስ እንዲያገኙ ምን መደረግ አለበት መሆን ነበረበት አለች፡፡ እስቲ ለሴቶች የሚያግዝ ባንክ ቢኖር ብላ ሐሳቧን ሰነዘረች፡፡ እኔንም እንዳስብበት ጠየቀችኝ፡፡ ከዚያም ስብሰባውን አቋርጠን ወጣንና ሒልተን ሄደን ወይን እየጠጣን ስለሴቶች ባንክ ማውራት ጀመርን፡፡ በነጋታውም ከዚያም በኋላ ስለሴቶች ባንክ መቋቋም መወያየት ጀመርን፡፡ ሐሳባችን ሁሉ እሱ ሆነ፡፡ ሦስት አራት ወራት ይህንኑ ጉዳይ እያነሳንና እየተወያየንበት ብንቆይም፣ መሀል ላይ ግን ሥጋት የሚፈጥሩብንም ነገሮች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን? የሥጋቱ ምንጭ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ምክንያቱም የእኛ ሐሳብ ጥሩ ቢሆንም ገንዘብ የለንም፡፡ ባንክ የሚያቋቁሙት ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ናቸውና ይኼ ነገር ይሳካልን ይሆን አይሆን ብለን ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ነገሩን ስናወጣ ስናወርድ ቆየን፡፡ እዚህ ውስጥ እከሌን ብናስገባ እከሊትን ብንጠራ እያልን ከእኛ ጋር ሊሠሩ ይችላሉ ያልናቸውን ሴቶች ሰበሰብን፡፡ እኔና ሣራ ከእኛ ጋር ሊሠሩ ይችላሉ ያልናቸው ሴቶች ማሰብ ጀመርን፡፡ ያሰብናቸውን አሥራ አንድ ሴቶች ጠራን፡፡ ነገር ግን ይህንን እስክናደርግ ድረስ እኔና ሣራ ስለነገሩ ሰዎችን ከማማከርና ከማወያየት ውጪ ምንም የተጨበጠ ሥራ አልሠራንም፡፡ አሥራ አንዳችን በነገሩ ተስማምተን ወደ ተግባር ለመሸጋገር ወሰንን፡፡ አክሲዮን መሸጥ ገባን፡፡ በመሥራችነት የተሰባሰቡት አሥራ አንዱ ሴቶች ጠንካሮች ነበሩ፡፡ የሚገርምህ ነገር አሥራ አንዱም እያንዳንዳቸው በራሳቸው ብዙ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይ በቢዝነሱ ዓለም ብዙ የለፉ፣ የደከሙና የሠሩ ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ የሚታዩም ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ካለን ልምድ አንፃር ተጋግዘንና ተበረታተን ባንኩን ለማቋቋም እስከ መጨረሻው በመሄዳችን ተሳክቶልናል፡፡ ውጤቱ በጋራ የሠራነው ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናት ባንክን ለማቋቋም ግን ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ በመካከል  ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እንዳጋጠሙዋችሁም አስታውሳለሁ፡፡ ችግሩ ምን ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ዋናው ፈተና አክሲዮን እየሸጥን በነበረበት ወቅት የገጠመን አንዱ ነው፡፡ ባንኩን ለማቋቋም የሚያስችለንን ካፒታል ለመሙላት የምናደርገው የአክሲዮን ሽያጭ ሄዶ ሄዶ 13 ሚሊዮን ብር ላይ ደርሶ ቀጥ አለ፡፡ ከዚህ ከፍ ለማድረግ ፈተና ሆነ በቃ፡፡ ቆምን፡፡ የሚፈለገው እስከ 100 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ነገር ግን ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሄድ ተቸገርን፡፡ ምን እናድርግ እያልን ሳለ ከእኛ አንዷ የሆነችው ወ/ሮ ሒሩት አላምረው ጎበዝ ሴልስ ብዙ ሰው ታውቃለች፡፡ እርሷ የምታውቀውን ሰው እንዲመጣ አድርጋ በፕሮጀክት ማኔጀርነት እንዲቀጠር አድርገን የምንፈልገውን ካፒታል በአምስት ወራት ውስጥ ሞላን፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ አነሳሳችሁ የሴቶች ባንክ በማቋቋም ሴቶችን ለመደገፍ ነው፡፡ ደግሞ ልክ እንደ እናንተው ‹‹ሔዋን›› የሚል ስያሜ ያለው ሌላ የሴቶች ባንክ እየተቋቋመ መሆኑ አስደንግጧችሁ ነበርም ይባላል፡፡ እናት የሚለውስ ስያሜ እንዴት ወጣ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እዚህ ላይ የሚገርም ታሪክ አለ፡፡ እኛ ይህንን ባንክ እውን ለማድረግ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ ይህንን ነገር ይዘን ለሕዝብ ስንቀርብ ያስኬደናል ወይ? እንወጣዋለን ወይ? እያልን ብዙ ወራት ፈጅተናል፡፡ በመካከል ግን ሌሎች የሴቶች ባንክ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል መረጃ ደረሰን፡፡ ሁለት የሴቶች ባንክ ሊቋቋም ይችላል፡፡ ነገር ግን ለእኛ የታየን ይህ ከሆነ ሕዝብ ብዥታ ውስጥ ሊገባ ነው፡፡ ሁለታችንም እንዲህ ካደረግን ሕዝቡን ማደናበሩ ብቻ ሳይሆን ሁለታችንም ልንወድቅ እንችላለን የሚል ሥጋት ፈጠረብን፡፡ ነገር ግን እኛ መፍጠንና ቶሎ ቶሎ መራመድ አለብን ብለን ቀጠልን፡፡ እኛ ያኔ ስንነሳ የባንኩን ስያሜ ‹‹Women’s Bank of Ethiopia›› ነበር ያልነው፡፡ በዚህ ስያሜ ንግድ ሚኒስቴር ልናስመዘግብ ሄድን፡፡ ነገር ግን ያኔ አቶ ግርማ ብሩ ነበሩና ‹‹Women’s Bank of Ethiopia›› አይሆንም ጄኔሪክ (የወል) ስለሆነ አይሆንም ሲሉን አዘንን፡፡ ምክንያቱም የሴቶች ባንክ የሚለውን ነገር ፈልገነው ነበር፡፡ ከዚያ ስሙን ለመለወጥ ሌላ ስያሜ ለማግኘት ፍለጋ ገባን፡፡ ሁላችንም ብዙ አሰብን፡፡ አሁንም ከመካከላችን አሁንም ሒሩት ስም ሊያወጣ ይችላል ብላ ላሰበችው ሰው ስልክ ደውላ ይሆናል ብሎ የነገራትን ይዛልን መጣች፡፡ ‹‹እናት ኢትዮጵያ›› ነበር ያሉት፡፡ ይህንን የሰሙ አንዳንዶቹ ውይ ይኼማ የደርግ ስያሜ ይመስላል አሉና ባይሆን እናት በሚለው እንርጋ ተባለ፡፡

ሪፖርተር፡- እናት የንግድ ባንክ ቢሆንም በግልጽ ያስቀመጣችሁት የተለየ አካሄድ እንዲኖረው ተፈልጓል፡፡ በፋይናንስ ሴቶችን ማገዝ ነው፡፡ እስኪ ስትነሱ የያዛችሁትንና የተነሳችሁበትን ዓላማ ያስታውሱኝ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንደ ማንኛውም ንግድ ባንክ ሠርቶ ማትረፍ አለበት፡፡ የባለ አክሲዮኖች ገንዘብ ነው፡፡ ነገር ግን አሥራ አንዳችን ንግድ ባንክ ለማቋቋም አልነበረም የተነሳነው፡፡ ይህ ፍላጎት አልነበረንም፡፡ የተሰባሰብንበት ዋነኛ ዓላማ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚያስችል፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ለሴቶች መሣሪያ ሊሆን የሚችል የፋይናንስ ተቋም ለመፍጠር ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ባንኩ በአሥራ አንድ መሥራች ሴቶች መቋቋሙና 64 በመቶ ሴቶች መሆናቸው፣ ከ65 በመቶ በላይ የቦርድ አባል መሆናቸው፣ ከ50 በመቶ በላይ ሠራተኞቹ ሴቶች መሆናቸው በዓለም ላይ ልዩ አድርጎታል፡፡ ስለሌላ ነገር ሳንነጋገር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሴቶች አይደለም ባንክ ማይክሮ ፋይናንስም ማቋቋም አልቻሉም፡፡ ሴቶች የሚታወቁት ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 300 እና 400 ብር በመበደር ነበር፡፡ እዚያ ድረስ ነበር የተሰመረላቸው ቦታ፡፡ ይህ ግን የእናት ባንክ መቋቋም ይህንን ሁሉ ለወጠ፡፡ ብዙ ሰዎች ደግሞ እምነትም አልነበራቸውም፡፡ የትም አይደርሱም እስከ መባል ደርሰን ነበር፡፡ እንዲያውም የታወቁትና የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ደግፈውን ነበርና እሳቸው እንኳን በጣም እያበረታቱን ነው ብለን ሌሎቹን ድጋፍ ስንጠይቅ፣ ‹‹አቶ ኢየሱስ እየደገፏችሁ ያሉት የትም አትደርሱም ብለው ነው፤›› ብለው የቀለዱብንም አሉ፡፡ ግን ሁሉ ነገር ተሳካ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ይህ ባንክ እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱለት የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ ትኩረት አድርገው ሴቶች ከሠሩና ከተባበሩ ትልቅ ነገር መሥራት እንደሚቻል ነው፡፡ እኛ አሁን ትልልቆች ነን፡፡ ዕድሜያችን ትልቅ ነው፡፡ ከእኛ በኋላ ላሉት ምሳሌ ይሆናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በነገራችን ላይ  በተለይ ሴቶች ሁልጊዜ የተሻለ ሠርተንና ልዩ ነገር ይዘን ካልወጣን በስተቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ በሌላ አገር ጥቁር ከሆንክ በጣም የተለየ አፈጻጸም ከሌለህና አፈጻጸምህ እንደ ሌላው ሰው ከሆነ በልዩነት ነው የምትፈረጀው፡፡ ወይም ችሎታ የለህም ተብለህ ነው የምትታየው፡፡ ስለዚህ ሴትም ተሁኖ የተለየ ውጤት ይጠበቃል፡፡ ሥራን በራሳችን መንገድ ነው ማስኬድ ያለብን፡፡ መሥራት ነው፡፡ የምናስመዘግበው ስኬት ደግሞ የሌላውን ዓይን ለመሙላት ሳይሆን በራሱ ማሳየት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማጎልበትና ለመደገፍ ካላችሁ የተነሳችሁበት ዓላማ እየተሳካ ነው? ባሰባችሁት ደረጃ ለሴቶች ፋይናንስ ማቅረብ ችላችኋል? ሴቶችን ማበደር ችላችኋል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አጠቃላይ የባንኩን ታሪክ ካነሳህ በመጀመሪያው ዓመት አትራፊ ሆኖ የወጣ ባንክ ነው፡፡ የግል ባንኮች በሙሉ ወደ ትርፍ ለመግባት ሁለት ሦስት ዓመት ይወስድባቸዋል፡፡ እኛ ግን በመጀመሪያው ዓመት ነው ያተረፍነው፡፡ ይህንን ካነሳህ አደራጆች እንደ አደራጅነታችን አምስት ሳንቲም አልተከፈለንም፡፡ ከመሥራቾቹ ሦስቱ በባንኩ ቦርድ ውስጥ ገብተናል፡፡ ጥሩ ቦርድ ስለነበረም ከማኔጅመንቱ ጋር ሆነን በጥንቃቄ በመሥራታችን በመጀመርያው ዓመት አትርፈናል፡፡ ሴቶችን በተመለከተ እናት ባንክ ሴቶችን የሚደግፍ ልዩ ፕሮግራሞች አዘጋጅቶ እየሠራ ነው፡፡ ይኼ ግን በምንፈልገው ፍጥነት  አልሄደም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ምክንያቱም ባንካችን ሁለት ዓላማ ይዞ ስለሚሄድ ነው፡፡ አንደኛው ለባለ አክሲዮኖችን ትርፍ ማስገኘትና ቀጣይ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሴቶችን አጀንዳ ይዞ መሄድ አለበት፡፡  ሁለቱ ጉዳዮች በአንድ በኩል የሚደጋገፉ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ለማሳካት በተለይ የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥልን እንድንችል፡፡ ይህንን ለመድረስ ቀጥታ ተጠሪነቱ ለፕሬዚዳንቱ የሆነ አንድ ዲቪዥን አቋቁመናል፡፡ ይህ ዲቪዥን የሴቶችን የፋይናንስ አገልግሎት የሚያዳብር ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላላ ጉባዔው ወይም ባለ አክሲዮኖች ከባንኩ ዓመታዊ ትርፍ አምስት በመቶ የሚሆነውን ‹‹ሪስክ ፈንድ›› እንዲገባ በመወሰን፣ ለሴቶች ብድር የሚመቻችበትን መንገድ መቀየስ አንዱ ነው፡፡

ይህም አንድ ሴት ጥሩ የሆነ የቢዝነስ ሐሳብ ያላት ሆና ይህንን ሐሳቧን መሬት ላይ ለማውረድ የሚያስችል አቅም ከሌላት ወይም ብድር ለማግኘት ለማስያዣ የሚሆን ንብረት ከሌላት፣ ለብድር ማስያዣ የሚሆነውን ከፈንዱ መጠቀም ነው፡፡ እንዲህ ባለው አሠራር ለ17 ሴቶች በአማካይ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ብድር ሰጥተን እንዳሉት ‹‹ፕሮግራም እየሠሩ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር እየሠራን ነው፡፡ ገጠር ላይ አቅም ለሌላቸው እስካሁን ለ500 ሴቶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ዩኤስኤይድና ሲዳ የአሥር ሚሊዮን ብር ‹ጋራንቲ ሌተር› ሰጥተውናል፡፡ ይህንን ብር በከፊል እንደ ዋስትና በመጠቀም ለበርካታ ሴቶች ብድር ለመስጠት ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ሴቶችን በፋይናንስ በመደገፍ ረገድ እያደጉ የመጡ ሥራዎች አሉ፡፡ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረጉ ረገድ ባንካችን የሚሠራው ሌላው ነገር በየጊዜው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ተማሪዎችን እያሠለጠንን ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡ በዚህ መንገድ ከተቀጠሩት 150 ከሚሆኑት ውስጥ 120 ሴቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ግል ጉዳይዎ ልመልስዎና ከዚህ በኋላ የሚያስቡት ሥራ አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ በዚህ ጊዜ ይህንን አደርጋለሁ ብዬ አይደለም የምጓዘው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ብልጭ የሚል ሐሳብ ይመጣልኛል፡፡ በአጋጣሚ ከሰዎች ጋር ሳወራ ወይ ሳነብ ወይ ፊልም ስመለከት ብቻ በሆነ አጋጣሚ የሚመጣልኝን ነገር ለመተግበር፡፡ ወደፊት ምን ለማድረግ እንደምችል አሁን አላውቅም፡፡ ልሠራ የምችለው ነገር እንደሚኖር ግን አምናለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በቡድን መሥራት፣ የሰዎችን ሐሳብ መስማትና በጋራ መሥራት የሚፈልጉ አሉ፡፡ እኔም ከእነሱ ውስጥ አንዷ ነኝ፡፡ እኔ ይህንን ያህል የቢዝነስና የገንዘብ አጀንዳ ብዙ የሚገፉኝ አይደለሁም፡፡ መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ኢንተርፕሩነርሺፕ መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ በጣም ነው የማደንቀው፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ መፈተን ይወዳሉ፡፡ በጣም አከብራቸዋለሁ፡፡ የበለጠ ግን እኔ ተለዋዋጭ የሆነ ነገር እፈልጋለሁ፡፡ እንደገና ደግሞ ተጨባጭ የሆነ ነገር እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መቼም አሁን ፋሲካ ደርሷል፡፡ በዓል እንዴት ነው የሚያሳልፉት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ፋሲካ የቤተሰብ በዓል ነው፡፡ አሁን እንግዲህ ሾላ ገበያ ሄጄ መከለሻ ገዛሁ ብልህ አታምንም አይደል? ግን አድርጌዋለሁ፡፡ ቤተሰብ እንጠይቃለን፡፡ ሞቅ አድርገን ነው የምናከብረው፡፡