አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በስፔን ሳባዴል በሁለት ሺህ ሜትር ያስመዘገበችው አዲስ ክበረ-ወሰን በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጸደቀ።

የክብረ-ወሰኑን መጽደቅ ተከትሎ አትሌት ገንዘቤ የክብረወሰኖቿን ቁጥር ስድስት አድርሳለች።

ገንዘቤ ጥር 30 ቀን 2009 ዓም በስፔን ሳባዴል ከተማ በተደረገው የሁለት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አዲስ ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ ማሸነፏ ይታወሳል።

ርቀቱን 5 ደቂቃ 23 ሰከንድ 75 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ነበር ክብረወሰኑን የሰበረችው።

ገንዘቤ የሰበረችው አዲስ ክብረ-ወሰን በስሟ መመዝገቡን ነው ዛሬ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ይፋ ያደረገው።

አትሌት ገንዘቤ በስሟ ያስመዘገበችው የ2 ሺህ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ከ22 ዓመት በፊት በአየርላዳዊቷ አትሌት ሶኒያ ኦ ሱሊቫን 5 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ 36 ማይክሮ ሰከንድ ተይዞ የነበረ ነው።

አትሌት ገንዘቤ ክብረ-ወሰን ስታስመዘግብ ይህ ለስድስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከስድስቱ አምስቱ በቤት ውስጥ ውድድር የተመዘገቡ ናቸው።

አትሌቷ አዲስ ክብረ-ወሰን ካስመዘገበችባቸው ውድድሮች መካከል በ2015 ሞናኮ ላይ 1 ሺህ 500 ሜትር አንዱ ነው።

ሌሎች አምስቱ ደግሞ ዛሬ የፀደቀውን 2 ሺህ ሜትር ጨምሮ፤ 1 ሺህ 500 ሜትር፣ 3 ሺህ ሜትር፣ 5 ሺህ ሜትር፣ የአንድ እና የሁለት ማይል የቤት ውስጥ ውድድር ርቀቶች ናቸው።