ዓለማችን በብዙ ምርጫዎች የተሞላች ነች ፡፡ ምርጫ የሌለበት የለም፡፡ የማይመረጥም የለም፡፡ ልብስ ይመረጣል፤ ጓደኛ ይመረጣል፤ አጭር፣ ረጅም፣ ቁመት ይመረጣል፤ ምግብ ይመረጣል፤ መጠጥ ይመረጣል፤ የቤት ምርጫ አለ፤ የሠፈር ምርጫ አለ፤ ወዘተ. ምርጫ የሌለባቸው የዓለማችን ቀናት አልነበሩም፤ ወደፊትም የሚኖሩ አይመስለኝም፡፡

ያኔ ያኔ የሥልጣኔው ሀ ሁ ሲጀመር አንዳንድ የፈጠራ ውጤቶች ብርቅዬና ድንቅዬ በመሆን አማራጭ የለሽ ሆነው አማራጭ እስከሚገኝላቸው ድረስ ማንኪያ ላይ እንዳለ «እንቁላል» በጥንቃቄ ይዘን፤ በስስት ዐይን እያየን የምንጠቀምባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ግን በምርጫ ማዕበል ተገፍተውና ተወስደው ከእኛ ርቀው ትዝታና ታሪክ ሆነዋል፡፡

በየትኛውም ዘመንና ጊዜ ግን ለእናት እና ለአገር ምርጫ የለም፡፡ እናት በማህፀኗ ተሸክማ የወለደች አጥብታ ያሳደገች የሕልውና መሰረት ናት፡፡ አገርም የእናት ተምሳሌት፡፡ እናትን ዱሮና ዘንድሮ እያሉ አያማርጧትም።

የዜግነት ክብር እና የማንነትም መገለጫ የሆነችው አገርም እንዲሁ ናት፡፡ ማንም እናቴ የጥንት ናት፤ አገሬም እንደዚሁ ብሎ ሊለውጥ፣ ሌላ አማራጭ ለማምጣት ቢሞክር አይችልም። ይደክማል እንጂ፤ ሌላ አማራጭ አያገኝም፤ ስለዚህ አማራጭ የለውም ፡፡

ብዙ ምርጫዎች ባለባት በሰለጠነችው አሜሪካ ምድር የዚያች አገር መሪ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በደሀዋና የጥቁሮች አህጉር ተብላ በምትጠራው አፍሪካ በምድረ ኬንያ ከተፈጠሩት አባታቸው አብራክ ስለመውጣታቸው ኬንያን በጎበኙበት ወቅት እና ከዚያም በፊት ብዙ ተብሏል። ይህን ደግሞ አገሪቱን በይፋ ሲጎበኙ ፕሬዚዳንቱ በአንደበታቸው አረጋግጠውታል፤ ከሥጋ ዘመዶቻቸውም ጋር ራት በሉ፡፡ ይህ የፕሬዚዳንቱ ምርጫ የሌለው የራሳቸው ታሪክ ነው፡፡ ለአባታቸውና ለአገራቸው ኬንያ አማራጭ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ የእርሳቸው የዘር ግንድ፤ የእርሳቸው የመነሻ ምድር ጥቁሯ አፍሪካ ናት፡፡ ጥቁር አሜሪካዊ፡፡ እውነቱ ይሄውና ይሄው ብቻ ነው። ‹የአባት፤ የእናት፤ የአገር ጉዳይ ነበር፤ግን በዚህ ቀየርኩት› አይባልም

ጊዜ በራሱ መዘውር ውስጥ ሲዘዋወር ቀናት በቀናት እየተተኩ የሥልጣኔውም ነፋስ ከሰሜን ወደ ደቡብ፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ እየነፈሰ፤ በፋብሪካ በተፈበረኩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ልዩ ልዩ ማሻሻያና ማዳበሪያ እየተደረገላቸው ለምርጫ ሲቀርቡ፤ ብርቅዬዎች ተብለው እነኛ በስስት ዐይን ይታዩ የነበሩ ነገሮች፤ በአዲሶቹ ተተክተው እየተለወጡ፤ አንዳንዶቹም በቅርስነት እንዲታዩ ወደ ሙዚየም እንዲላኩ ሲደረግ በየዘመናቱ ታይቷል፡፡ በአገርና በእናት ላይ እንዲህ ያለ አይታሰብም፡፡ አሮጌ በአዲስ የመለወጥ፤ የቆየና አዲስ የማለት እሳቤ ፍፁም የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም ፡፡

አገርም አገር ነች፤ እናትም እናት ነች፡፡ ሁለቱም የሁልጊዜ ምርጫዎች፤ የሁልጊዜ አዲሶች ናቸው፡፡ «እናት ብታረጅ፤ ብትደክም አርጅታለች፤ ደክማለች ትሙት» የሚል የሰው ፍጡር ያለ አይመስለኝም፡፡ እናትና አባት አገር እና ቤት ዞሮ መግቢያ ናቸው፡፡

ቤት፤ ምንም ይሁን ምንም፤ የትም ውለን፤ የትም ዞረን ተመልሰን የምንገባበት እና የምንጠለልበት ደግሞም የምንውልና የምናድርበት ነው፡፡ አሮጌ ነው፤ አዲስ ነው ብለን ምርጫ ነገር ውስጥ አንገባም፡፡ ከሌላም ጋር አናወዳድረውም፤ ብናወዳድርና አቃቂር ብናወጣለት እንኳን እኛ ነን ትዝብት ላይ የምንወድቀው፤ እውነቱ ግን በእርሱ ውስጥ መኖራችን ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ቤት የእኛ ነው፡፡ የእኛም እናት የእኛ ናት፡፡ አገራችንም ምንጊዜም አገራችን ናት እኛም ልጆቿ፡፡

በአገራችን «የሰው ነገር የሰው ነው» ይባላል፤ አባባሉ የሌላን ሰው ነገር ቢወዱትና ቢመርጡት አያዋጣም እንደማለት ነው፡፡ የሰው የሆነ ሁሉ ባለቤቱ ማን እንደሆነ ይታወቃልና ወደ ባለቤቱ መመለሱና የባለቤቱ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ «የተውሶ ይመለሳል፤ ታጥቦ ተተኩሶ» ይባላል፡፡ የእኛ ያልሆነው ነገር የእኛ ነው ብለን ቃና እና ጣዕሙ ባልጣመን ወቅት «ያልወለድኩት ልጅ አባባ ቢለኝ ፤ አፌን ዳባ ዳባ አለኝ» እንላለን። አማራጭ ለሌለው ነገር አማራጭ በፈጠርንለት ጊዜ የቀደመው አማራጫችን ምን ያህል ጣዕም እንደምናሳጣ ይታወቃል።

በምድራችን ላይ ለበርካታ ነገሮች አማራጮች እውን በመሆናቸው በየዘመናቱ የተፈጠሩትን አማራጮች ስናነሳ ሊመረጡ የሚችሉ ቁሳዊ ነገሮች በሽበሽ ናቸው፡፡

እስቲ ወደኋላ እናስብና በሥልጣኔና በዕውቀት አማካይነት እየተለወጡ የመጡትን እና አማራጭ የተፈጠረላቸውን አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት። ጥንት ለትራንስፖርት የምንገለገልባቸው የቤት እንስሳት ፈረስና በቅሎ በዓለምም በእኛም አገር በመኪና ተተክተዋል፡፡ መኪናም ሌላ አማራጭ ተገኝቶለታል። ባቡር፣ መርከብ፣ አውሮፕላን፣ ወዘተ አማራጮች ተገኝተውለታል።

ስልክን እናንሳ ብርቅዬው ባለቀጭኑ ሽቦ በዘመናት ሂደት ሽቦ አልባ ሆኖ ብቅ ብሏል። ቤት ውስጥ ብቻ ከመቀመጥ ወጥቷል። በየሰው ኪስና ቦርሳ ውስጥ ሆኖ ገጠር ከከተማ ይከረከራል። ድምፅ ማሰማት ብቻ ሳይሆን መልክንም ማሳየት ጀምሯል፡፡ ለምርጫም የተመቻቸ ሆኗል፡፡

እናትና አገር ግን ሁልጊዜም ያው ናቸው። በመልክም በቅርፃቸውም አይለዋወጡም። ሌላ አማራጭም አናመጣላቸውም፡፡ እናት ለልጇ ዘወትር አንድ መልክ ነው ያላት፡፡ የአገራችንም ውበትና ማንነት ከቶም በወቅቶች እንዲሁም በዘመናት መፈራረቅ አይለዋወጥም፡፡ እናትና ሀገር በፍቅራቸው፣ በሰብሳቢነትና እንክብካቤያቸው አማራጭና ወደር የላቸውም። እንዲያውም ዘመን ተሻጋሪ ማንነት እና ተመራጭነት ለእናት እና ለአገር ነው የሚታሰበው፡፡

እናት ከቤቷ ወጥተው የከረሙ ልጆቿን ዐይን ለማየት የምትጓጓ፤ ሲመጡላትም እጇን ዘርግታ የምትቀበል ቤት ያፈራውን አቅርባ የምታቋድስ ናት፡፡ ይህ እውነት ደግሞ ያለምንም ቅሬታና ማመንታት ለተወለድንባት፣ ለምንኖርባትና ሁለንተናችንን አቅፋ ደግፋ ለያዘችው አገራችን እውነተኛ መገለጫ ነው፡፡ ለእናታችንና ለአገራችን አማራጭም ምርጫም የለንም፡፡

ይህንን እውነት ዛሬ ላይ ስንፈትሸው እውነትነቱን አጉልተው የሚያሳዩን አያሌ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ማነው እናቴ ከሳች፤ ጠቆረች፤ ጎሰቆለች፤ አጣች፤ ነጣች «ወዘተ ብሎ ሊቀይር የሚነሳ? ቢነሳስ ይችላል ወይ? በፍፁም፡፡ የእናት እናትነቷ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ያው ነው፡፡ አገርንም በማንኛውም ነገረምክንያት ለመለወጥ መፈለግ ወይም ሌላ አማራጭ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ የዘር ግንድ ሲታሰብ፤ የማንነት ጥያቄ ሲነሳ፤ እትብት የተቀበረባት ምድር መጠቀሷ አይቀሬ ነገር ነው፡፡

ማነው ከጥላው መሸሽ የሚችል? ጥላው አካሉን ይከተለዋል። ስለምን ቢባል አካሉ የጥላው መንስኤ ነዋ!! በወረቀት ላይ የእናትንም የአገርንም ስም በሌላ አማራጭ ስም መለወጥ ይቻል ይሆናል፤ ስያሜ ግን እውነቱን አይቀይረውም፡፡ ስም ሳይሆን ስም የተሰጠው በተጨባጭ ያለው ሕልው የሆነው ነገር ነው ወሳኙ። «ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብርም ዝንጉርጉርነቱን…» ይለውጥ ዘንድ ይቻለዋልን? አይመስለኝም፡፡

ስለዚህ የትም ያሉ የአገሬ ሰዎች አንድ እናት አንድ አገር ነው ያላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን ሲያወያዩ ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ማስገንዘባቸውን አስታውሳለሁ።

ልዩ ልዩ ምክንያቶች ከቦታ ቦታ እንድንዘዋወር ቢያደርጉንም፣ «እንጀራ ሆነና ዋናው ቁም ነገሩ፤ አልቀመጥ አለ የሰው ልጅ ባገሩ» ቢባልም ዘወትር እናትን ከማሰብ ወደ አገር ቤት ከመግባት ሌላ አማራጭ የለም፡፡ እናትና አገር ያለምንም ማመንታት የሁሉም ዘመን ምርጫ ናቸው!! እናትና አገርን በምን ይተኳል?! በምንም፡፡

በአማራጭ የተሞላው ዘመናችን ዛሬ ለምንጠቀምባቸውና ለምንገለገልባቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ወደፊትም ሌሎች አማራጮችን ይዞ መምጣቱ አያጠራጥርም፡፡ ይሁንና አማራጭ የሌላቸውን ሁለቱን «እናት እና አገርን» ከልብ እየወደድን እየተንከባከብንና እያሳመርን እንቀጥል!! ይሄው ነው መቋጫው ሃሳቤ፡፡ በተረፈ አንባቢዎቼ ከእናትና ከአገራችሁ ጋር ያኑራችሁ!! እያልኩ ደግሜ ሌላ ጊዜ አንዳች ሃሳብ ይዤ ብቅ እስከምል ድረስ ብዙ ሰላም ተመኘሁ! ሰላም !!!

ፀሐፊው ሳምናስ ( ዓምደኛ )