ፍቅር በዓለም ላይ ካሉ ህልዮቶች ሁሉ የላቀው ነው። ሰውን ጨምሮ ማናቸውም ፍጥረታት ከፍቅር ጋር አንዳች ምስጢራዊ ውህደት ያላቸው ይመስላል። ይህም ህይወት ራሷ ያለ ፍቅር የማትታሰብ በመሆኗ ከፍቅር ጋር የመሰረተችው ወዳጅነት ነው። ከአፏ የደረሰን ምግብ ለልጇ የምታጎርስ ወፍን የተመለከተ ፍቅር ምን ያህል ለህይወት አስፈላጊ ኃይል መሆኑን ይታዘባል። የምድራችን ታላቁ ፍጥረት የሆነውን ሰውንም ስናስብ መላ ህይወቱ ከፍቅር ጋር የተሳሰረ መሆኑን እንረዳለን።

ባልና ሚስትን፣ ወላጆችንና ልጆችን እህትና ወንድሞችን አስተሳስሮ የአገር መሠረት የሆነውን ቤተሰብን የፈጠረው ፍቅር ነው። እግሬን ለጠጠር ግንባሬን ለጦር ብሎ ሰው ክቡር ህይወቱን የሚሰዋው እትብቱ ለተቀበረባት፣ ከአለመኖር ወደ መኖር ሲመጣ እጇን ዘርግታ ለተቀበለችው ለተወለደባት ለተገኘባት ምድር፣ ለእናት አገሩ ባለው ፍቅር ነው።

ለዚያም ነው ከሃይማኖት ሰባኪው እስከ ፈላስፋው፣ ከድምፃዊው እስከ ፀሐፊው፣ ከወታደሩ እስከ አርሶ አደሩ፣ ከተራው እስከ አገር መሪው ስለ ፍቅር የሚዘምረው። እናም እስከአሁን ስለ ፍቅር እጅግ ብዙ ብዙ ነገር ተብሏል። ፍቅር የመላ ዓለም ታላቅ ምስጢራዊ ኑባሬ ነውና የሰው ልጅ ወደፊትም ስለእርሱ ማሰብና መናገሩን ይቀጥላል።

እኔም ለዛሬው የምድራችን ታላቁ ሰው እየተባለ የሚጠራው ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት ለሚወዳት ሴት ልጁ በጻፈው ደብዳቤ ለፍቅር የሰጠው ትርጉም እስከ ዛሬ ከተባሉት ሁሉ ፍቅርን የበለጠ የሚገልጸው ስለመሰለኝ እንደሚከተለው ተርጉሜ አቅር ቤዋለሁ።

ሙሉ ደብዳቤው እንዲህ ይነበባል፦

«የአንጻራዊነትን ንድፈ ሃሳብን ባዘጋጀሁበት ወቅት የተረዱኝ በጣም ትንሽ ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ አሁንም ለሰው ዘር ሁሉ ለመግለጽና ለማስተላለፍ የምፈልገው ጉዳይ ከሰዎች የተሳሳተ አረዳድና ግላዊ አመለካከት ጋር ሊጋጭ ይችላል።

ውዷ ልጄ ዓመትም ይሁን አስር ዓመት የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ ማህበረሰቡ ከዚህ ቀጥዬ የማብራራውን ነገር የሚቀበልበት የዕድገት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የቻልሽውን ያህል ደብዳቤዎቼን ጠብቂያቸው።

እጅግ በጣም ታላቅ የሆነ አንድ ኃይል አለ፤ ሳይንሱም እስከአሁን ድረስ ለዚህ ኃይል መደበኛ የሆነ ትርጉም አላገኘለትም። ማብራሪያም ሊሰጥበት አልቻለም። እርሱም ሌሎች ኃይላትን ሁሉ ጠቅልሎ የሚይዝና የሚገዛ ሲሆን፤ ምናልባትም በመላ ዓለም ውስጥ ከሚፈጠሩ ማናቸውም ክስተቶች በስተጀርባ የሚገኝና ማንኛችንም ቢሆን ልንረዳው ያልቻልነው ታላቅ ኃይል ነው። ይህም ሁለንተናዊ ኃይል ፍቅር ነው።

ሳይንቲስቶች ዓለምን ሁሉ ያስተሳሰረውን የኃይል ንድፈ ሃሳብ ፈልገው ለማግኘት በተነሱበት ጊዜ ይህንን እጅግ ተዓምረኛ የሆነውን የማይታየውን ረቂቅ ኃይል ዘንግተውታል። ፍቅር ብርሃን ነው፤  የሚሰጡትንና የሚቀበሉትን ዕዝነ ልቦና የሚያበራ። ፍቅር ስበት ነው፤ ሰዎች በሌሎች ሰዎች አንዲሳቡ የሚያደርግ ስሜት ይፈጥራልና። ፍቅር ኃይል ነው፤ መልካም ነገሮች እንዲበዙልን በማድረግ የሰው ዘር በጭፍን ራስ ወዳድነት ውስጥ ተውጦ ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋ ይታደጋልና! ፍቅር ይባዛል ደግሞም። ለፍቅር እንኖራለን እንሞታለንም። ፍቅር እግዚአብሔር ነው እግዚአብሔርም ፍቅር ነው።

ይህ ኃይል ሁሉንም ነገር ያብራራል እናም ህይዎት ትርጉም እንዲኖራት ያደርጋል። ይህንን ምስጢር ለረጅም ጊዜ ቸል ብለነው ኖረናል። ምናልባትም ፍቅርን በመፍራታችን ይሆናል፤ ምክንያቱም ፍቅር በመላ ዓለም ካሉ ምስጢራት መካከል የሰው ልጅ ምንነቱን ሊደርስበት ያልቻለ ብቸኛው ኃይል ነው።

ለፍቅር የበለጠ ግልጽ ምስል ለመስጠት በዝነኛው ቀመሬ ውስጥ ቀለል ያለ ተለዋጭ ሠርቼለታለሁ። E= mc2 በሚለው የዕኩልነት ዐረፍተ ነገር ውስጥ ዓለምን ለማዳን የሚያስችለው ኃይል የሚገኘው ፍቅር ሲባዛ የብርሃን ፍጥነት እርስ በእርሱ ተባዝቶ ከሚገኘው ውጤት የሚለውን ብንቀበል ፍቅር የመላ ዓለም እጅግ ታላቁ ኃይል ነው ወደሚል መደምደሚያ እንደርሳለን፤ ምክንያቱም ማለቂያ የሌለው ወሰን አልባ ነውና።

እኛ የሰው ልጆች ተመልሰው ለህልውና ስጋት የሆኑብንን ሌሎች የመላው ዓለም  ኃይላት ልንጠቀምባቸውና ልንቆጣጠራቸው ሞክረን ካቃተን በኋላ በሌላ ዓይነት ኃይል ራሳችንን መርዳት ጊዜ ልንሰጠው የማይገባን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ዝርያችን በምድር ላይ እንዲሰነብት ከፈለግን፣ ህይወት ትርጉም እንዲኖራት ከወደድን ዓለምንና በውስጧ ያሉ ፍጡራንን ሁሉ መታደግ ከፈለግን፣ ፍቅር አንድና ብቸኛው መፍትሔ ነው።

ምናልባትም ዓለምን በጥፋት ጎዳና ላይ እየመሯት ያሉትን ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትንና ስግብግብነትን ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ያለው መሳሪያ፤ የፍቅር ቦምብን ለመሥራት እስከአሁን አልተዘጋጀን ይሆናል። ይሁን እንጅ እያንዳንዱ ግለሰብ ትንሽ የሚመስል ነገር ግን ከፍተኛ አቅም ያለው ጥቅም ላይ የሚውልበትን ጊዜ እየተጠባበቀ የሚገኝ ዕምቅ የፍቅር ጉልበትን በውስጡ ተሸክሟል።

ውዷ ሌይሰርል፣ ይህንን ሁለንተናዊ ኃይል መስጠትና መቀበልን በምንማርበት ጊዜ ፍቅር ሁላችንንም እየገዛን መሆኑን እናረጋግጣለን። ሁሉም ነገር ወደ መጨረሻው የዕድገት ደረጃ ይሸጋገራል ምክንያቱም ፍቅር ለፍፅምና የሚያበቃ የህይወት ማዕከላዊ ህዋስ ነውና።

በልቤ ውስጥ ያለውን ፍቅሬን ልገልጽልሽ ሳልችል በመቅረቴ ህይወቴን በሙሉ እያስቀ የምኩሽ እንደኖርኩ ይሰማኛል፤ እጅግም ይፀፅተኛል። ይቅርታ ለመጠየቅ በጣም ረፍዶ ይሆናል። ሆኖም ጌዜ ራሱ አንጻራዊ እንደመሆኑ መጠን አሁንም ቢሆን በጣም እንደምወደሽ ልንግርሽ እፈልጋለሁ፤ ደግሞም ምስጋና ለአንቺ ይሁንና የመጨረሻው መልስ ላይ ልደርስ ችያለሁ!»

አባትሽ፣

አልበርት አንስተይን