በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን፣ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ፣ አገር በቀል የሆነው የሞሪንጋ ተክልን የምርት እሴት በመጨመር የአካባቢውን ኅብረተሰብ የሥነምግብ ሁኔታ ለማሻሻል፣ እንዲሁም የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችል የአምስት ዓመት ፕሮጀክት የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ተበሰረ፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት፣ ከክልሉ መንግሥትና ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይኸው ፕሮጀክት፣ በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በወዘካ ቀበሌ በሚገኘው 30 ሔክታር መሬት ላይ ሞሪንጋን በዘመናዊ መንገድ በሙከራ ደረጃ የማልማት ሥራ ይከውናል፡፡

ልማቱ የሚካሄደው በክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አማካይነት ሲሆን፣ ከዚህም ለአንድ ዓመት ሥራ ብቻ የሚውል 23.6 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከጣሊያን መንግሥት መገኘቱን ከዩኒዶ የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

ፕሮጀክቱ በሙከራ ትግበራ ወቅት ለ30,000 የሞሪንጋ ተክል አብቃዮች፣ ሞሪንጋ ተክልን በተገቢው መንገድ ማልማትና በጥንቃቄ መያዝ በመሳሰሉት ዙሪያ ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች እናቶችና ወጣት ልጃገረዶች እንደሚሆኑ መረጃው ጠቁሟል፡፡

‹‹ሽፈራው ወይም ሺፈሬ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ይኸው አገር በቀል ተክል በደቡብ ክልል በሚገኙና ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝብ መደበኛ ምግባቸው መሆኑን፣ ለእንስሳት መኖና ለውኃ ማጣሪያ መዋሉን፣ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ የሚሰጥ መሆኑ በዓለም እየታወቀ መምጣቱን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሞሪንጋ ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎችና አሚኖአሲድ እንዳሉት፣ በመጀመሪያ ደረጃ የተከናወነው ጥናት እንዳረጋገጠና ለኤክስፖርት የሚውል ከፍተኛ የሆነ የሞሪንጋ ተክል ሀብት ካላቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች መረጃው አመላክቷል፡፡

ሞሪንጋ፣ ‹‹ሽፈራው›› ከሚለው መጠሪያው በተጨማሪ ‹‹የጎመን ዛፍ››፣ ‹‹የአፍሪካ ሞሪንጋ›› ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በዝቅተኛው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አካባቢ ከደረቅ እስከ መጠነኛ እርጥበታማ ሥነምህዳሮች እንደሚበቅል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከበርካታ ጠቀሜታዎቹ መካከል ሻይን ጨምሮ ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ለውኃ ማጣሪያነትና ለእንስሳት መኖነት መዋሉ ይገኙበታል።