ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ተቋርጠው ተጫዋቾች ወደ ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ሲመለሱ ለ2018ቱ የሩስያ አለም ዋንጫ ዝግጅት በወዳጅነት ጨዋታ የሚገናኙ ይሆናል።

ዛሬ ምሽት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የ2014ቱ የአለም ዋንጫ አሸናፊ ጀርመን በሲግናል ኤዱና ፓርክ እንግሊዝን የምታስተናግድበት ጨዋታ ትኩረትን የሳበ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች የቅርብ ተቀናቃኝ ከመሆናቸውም በላይ ከፈረንሳዩ የአውሮፓ ዋንጫ ወዲህ ተሸንፈው አለማወቃቸው የዛሬው ጨዋታ ትልቅ ፉክክር ሊታይበት እንደሚችል ግምት እንዲሰው አድርጓል።

በምሽቱ ጨዋታ ፊል ጆንስና ሚኬል አንቶኒዮ በጉዳት ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አይሰለፉም፤ በጀርመን በኩል ሜሱት ኦዚል ጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዛሬው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ታውቋል።

130ኛና የመጨረሻ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታውን የሚያከናውነው ሉካስ ፖዶልስኪ ዛሬ ምሽት የጀርመን ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ተገልጿል።

በእንግሊዝ በኩል አምበሉ ዋይኒ ሩኒ ለብሄራዊ ቡድኑ አለመመረጡን ተከትሎ የቼልሲው ተከላካይ ቲም ካሂል በአምበልነት ቡድኑን ይመራል።

በሌሎች የዛሬ ምሽት ጨዋታዎች ስኰትላንድ ከካናዳ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ከሉቴኒያ የሚገናኙ ይሆናል።