ፍቅረኛውን ሌላ ወንድ ይዛብኛለች በሚል ምክንያት አሲድ ፊቷ ላይ በመድፋት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ።

ተከሳሽ ክበበው አሳየ በአማራ ክልል አዊ ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ጋጉና ማሪያም ቀበሌ ነዋሪ ነው።

ከተማሪ ብርቱካን ስማቸው ጋር የትምህርት ገበታ ለመቋደስ በጋራ ወደ ትምህርት ቤት ከመመላለሳቸው የተነሳ፥ አብረው በማጥናትና ያልገባቸውን በመጠያየቅ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋትን አላማ አድርገው ተቀራርበዋል።

በጊዜ ሂደትም ትምህርት፣ ጥናት እና መተጋገዝ ላይ የተመሰረተው የሁለቱ ግንኙነት አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ፍቅር አመራ።

የተማሪዎቹ ፍቅር የግል ተበዳይ ቤተሰብን እያሳሰበ በመምጣቱ ልጃቸውን ራቅ ወዳለ ቦታ ወስዶ ማስተማርን አማራጭ አደረጉ።

ለዚህም ደብረ ማርቆስ ከተማን መርጠው ተማሪ ብርቱካንም ትምህርቷን በዚያው ቀጠለች።

ፍቅረኛሞቹም የቦታው ርቀት እንደወትሮው ሊያገናኛቸው ባይችልም በስልክና በተለያዩ መንገዶች ግንኙነታቸው እንዲቀጥል ማድረግን አማራጭ አደረጉት።

ይሁንና እንደወትሮው ፍቅረኛውን ማግኘት ያልቻለው ተከሳሽ እንደቦታው እኔንም በሌላ ፍቅረኛ ቀይራኛለች የሚል ጥርጣሬን በመያዝ፥ ሃሳቡን ለግል ተበዳይ ተማሪ ብርቱካን ቢገልጽም ሁልጊዜም አብረን ነን የሚል ምላሽን ያገኛል።

ሃቁ ይህ ቢሆንም ተከሳሹ ፍቅረኛየ ሌላ ወንድ ይዛብኛለች በሚል፥ በፍቅር ጓደኛው ላይ የከፋ ነገር ለመፈፀም በማሰብ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ ጥር 16 ቀን ያመራል።

በዕለቱም ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ በከተማዋ 03 ቀበሌ፥ አዲሱ ገበያ በተባለው ቦታ የግል ተባዳይ ላይ ደብቆ የያዘውን አሲድ ይደፋባታል።

የተከሳሽ ፍቅረኛ የነበረችው የግል ተበዳይም በተደፋባት አሲድ፥ በፊቷ፣ በአንገቷ፣ በደረቷ፣ ጀርባዋና ጉልበቷ ላይ ጉዳት ቢደርስባትም በህክምና በተደረገላት ርብርብ ህይወቷን ማትረፍ ተችሏል።

ጠቅላይ አቃቢ ህግም ተከሳሹ በፈፀመው ከባድ የመግደል ሙከራ ክስ መስርቶበታል።

ተከሳሹ በምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ተነቦለት፥ ወንጀሉን ሆን ብየ ሳይሆን በቸልተኝነት ፈጽሜዋለሁ በሚል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

አቃቢ ህግም የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ አስደምጧል፥ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለቱ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነህ ብሎታል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሽን ሶስት የቅጣት ማቅለያዎች በመያዝ ሌሎችን ያስተምራል ተከሳሹንም ያርማል በማለት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።