በምስሉ ላይ የሚታየው መሣሪያ በእጅ የሚሠራ የብርኬት ማምረቻ ማሽን ነው፡፡ ማሽኑ በፈጠራ መብት ባለቤቷ ወይዘሮ ስንትአበባ ፈለቀ ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በአነስተኛ የፈጠራ ሥራ ዘርፍ ተመዝግቧል፡፡ በፈጠራ ባለመብቷ የተሰራው በእጅ የሚሰራ ማሽን ለማገዶ የሚውል የብርኬት ምርት ማምረቻ ሲሆን፤ ወደ ላይ አንድ ሜትር ከግማሽ፣ ወደጎን ደግሞ አንድ ሜትር በሆነ መጠን ሙሉ በሙሉ ከተቀቀለ እንጨት የተሰራው ነው፡፡

በማሽኑ ከቡና ገለባ፣ ከእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ)፣ ከእርሻና ከተለያየ ተረፈምርት የብርኬት ማገዶው ይመረታል፡፡ የምርት ሂደቱም ግብአቱን ወደታች ጨምቆ ማውረድ በሚያስችለው መሣሪያ ወይም ኃይድሮሊክ በመጫን ቅርፅ ይዞ እንዲወጣ በማድረግ ይከናወናል፡፡

ከተለያየ ምርት የሚገኘውን አንድ እጅ ተረፈምርት ለማጣበቂያ የሚውል አንድ እጅ አፈር በውሃ ተዋህዶ ወይም ተቦክቶ ወደማሽኑ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ማሽኑን በእጅ በማንቀሳቀስ በግማሽ ሰዓት ውስጥ እስከ 10 የሚደርስ መጠኑ ከግማሽ እስከ አንድ ኪሎ የሚመዝን የብርኬት ማገዶ ይመረታል፡፡ ማሽኑ በአንድ ቦታ የሚቀመጥ ቢሆንም ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቀላል ነው፡፡

ለጥሬ ዕቃ፣ ለእጅ ባለሙያና የተለያዩ ወጪዎችን ጨምሮ ለማሽኑ መስሪያ 25ሺህ ብር ወጪ ሆኗል፡፡ ማሽኑን አሁን ካለበት ደረጃ የማምረት አቅሙንም ከፍ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፤ መጠኑን ከፍና ዝቅ በማድረግ እንደሚፈለገው ቁመት ማስተካከያ በማድረግ አሁን ካለው የተሻለ ማዘመን ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ የፈጠራ ባለመብቷ አሁን ባላት የገንዘብ አቅም ዘመናዊ ማድረግ አልቻ ለችም፡፡ የማመረት አቅሙን ግን ከ10 ወደ 15ከፍ እንዲል አሻሽላ ሰርታዋለች፡፡ ወይዘሮ ስንትአበባን ለፈጠራ ሥራዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ5ኛው አገርአቀፍ የሳይንስ፤ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሽልማት የነሐስ፣ ዋንጫና ገንዘብ ማበረታቻ ሸልሟታል፡፡ የመጀመሪያ ሽልማቷን ያገኘችው ግን ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተብሎ ከሚጠራው ተቋም ነው፡፡ በወቅቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግር ፈቺ ምርምር ያካሄዱ ሰዎችን ለማበረታታት ባወጣው ውድድር ሥራዋን በማቅረብ ተሳትፋለች፡፡

ተቋሙም ከተወዳዳሪዎች ከለያቸው ምርጥ 40 የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል አንዷ በማድረግ ሸልማት፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ለአምስት ዓመት የምትጠቀምበት 120ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ፣ 20ሺህ ብርና የምስክር ወረቀት በመስጠት ነው ያበረታታት፡፡ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥልጠና በመስጠትና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ኢንተርፕሪነር ዲቨሎፕመንት ሴንተርና ክላይሜት ኢኖቬቲቭ ሴንተር ሥልጠና በመስጠት ለተሻለ ፈጠራ እንድትነሳሳ እንዳደረጓትም ትናገራለች፡፡ ወይዘሮ ስንትአበባ እንደነገረችኝ ሌላው የፈጠራ ሥራዋ ወደጎን አንድ ሜትር ከሃምሣ ሳንቲ ሜትር፣ ከፍታው ደግሞ ሁለት ሜትር በሆነ ቦታ ላይ 75ችግኞች መትከል የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ነው።

ስድስት ሜትር ፒቪሲ ተቆራርጦ 14 ቦታ ተበስቶ ተዘጋጀ፡፡ ቀዳዳዎቹ ሦስት ሴንቲ ሜትር ክፍተት አላቸው፤ እነርሱ የተዘጋጁት ለማዳበሪያ መያዣ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጀው ፒቪሲ በመሬት ላይ በተዘጋጀ የእንጨት ርብራብ ላይ በማድረግ በእያንዳንዱ የፒቪሲ ቀዳዳዎች ውስጥ 75 የተለያዩ ችግኞችን በመትከል የጓሮ አትክልትን ማልማት የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ነው፡፡ ሌላው በሂደት ላይ የሚገኘው የፈጠራ ሥራ ደግሞ በእንስራ ወይንም በጀሪካን የውሃ ሸክምን የሚያሰቀር ነው፡፡ ልክ እንደ ላፕቶፕ ቦርሣ ዓይነት የሚያገለግል መያዣ ለመስራት ነው እቅዷ፡፡ እንስራውና ጀሪካኑ ወገብን በማጉበጥ ጉዳት እንደሚያስከትል የምትናገረው ወይዘሮ ስንትአበባ እርሷ ልትሰራ ያሰበችው የፈጠራ ሥራ ችግሩን የሚያቃልል ነው፡፡

እርሷ እንዳለችው የፈጠራ ሥራዎቿ ትኩረት ያደረጉት የሴቶችን የሥራ ጫና በሚያቃልሉ ላይ ነው፡፡ በተለይም በገጠርና በከተማ ሆነው ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ ሴቶችን ተደራሽ የሚያደርግ ሥራ መስራት ነው ፍላጎቷ፡፡ እስካሁንም የሠራቻቸው ፍላጎቷን መሠረት ያደረጉ ችግር ፈች የፈጠራ ሥራዎች እንደሆኑ ታስረዳለች፡፡ በእጅ የሚሠራ የብርኬት ማሽኑን ስትሰራም መነሻ የሆኗት በእንጨት ፍቅፋቂ ወይም ሰጋቱራ እንጀራ የሚጋገሩ ሴቶች ናቸው፡፡ የሰጋቱራ ማገዶ እሳቱ ኃይለኛና የሚጎዳ በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል መላ ስትፈልግ ተረፈ ምርቱን ወደተሻለ ማገዶ የሚለወጥበትን መንገድ አቀደች፡፡

በዚህ መልኩ ነው ማሽኑን ለመስራት የተነሳሳችው፡፡ የጓሮ አትክልት ለማልማት የሚረዳውንም ፈጠራ የሠራችው በቦታ ችግር ትኩስ የጓሮ አትክልት መብላት ያልቻሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እንደሆነም ገልጻለች፡፡ እንዲህ ያለው የማምረት ዘዴ የጊዜ ብክነትንና የገንዘብ ወጪንም ከማዳኑ በተጨማሪ ትኩስ አትክልት ለመመገብ እንደሚያግዝም ተናግራለች፡፡ ከቤታቸው ርቀው ውሃ በወገባቸው ተሸክመው የሚሄዱ እና እህል እየወቀጡ ምግብ የሚያዘጋጁ ሴቶችን ችግሮች በፈጠራ ሥራዋ ለማቃለል ከፍተኛ ፍላጎት አላት፡፡ ሌሎች የፈጠራ ሥራዋን ወስደው ለተጠቃሚው ቢያደርሱም ፍላጎቷ ነው፡፡

የፈጠራ ሥራ መስራትም ሆነ ስለፈጠራ ሥራ ማሰብ እንደማይደክማት የምትናገረው ወይዘሮ ስንትአበባ «አንዲት ሴት ከፀነሰችበት ጊዜ ጀምሮ ልጇን አቅፋ እስክትስም የምትጨነቀውን ያህል እኔም በአዕምሮዬ የመጣውን ፈጠራ በወረቀት አስፍሬ ውጤቱን እስከማይ እጨነቃለሁ» ስትል ለፈጠራ ሥራ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ተናግራለች፡፡ ሴቶች በፈጠራ ሥራዋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን በፈጠራ ሥራውም መሣተፍ እንዳለባቸው መክራለች፡፡ ወይዘሮ ስንትአበባ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በትምህርቷም በሰው ኃይል አስተዳደር ዲፕሎማ አላት፡፡

በአንድ የግል ድርጅት ውስጥም ለተወሰነ ጊዜ ሰርታለች፡፡ ወደፈጠራ ሥራ ከገባች ወዲህ ግን ላለፉት ሦስት ዓመታት «ኢኮሴፍ ኃይል ቆጣቢ ማንደጃ ማምረቻ» የሚል ስያሜ ያለው ድርጅት ከፍታ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ወደፊትም አካባቢ ላይ ተፅዕኖ በማያሳደሩ ኃይል ሰጪ ሥራዎች ላይ በሰፊው እንደምትሰራም ተናግራለች፡፡   ለምለም መንግሥቱ