በአዲስ አበባ በሚገኙ ነዳጅ ማዳያዎች በተፈጠረ የቤንዚን አቅርቦት ችግር ለእንግልት መዳረጋውን  አሽከርካሪዎች ገለፁ፡፡ ባለፉት 3 እና 4 ቀናት በአዲስ አበባ የሚገኙ  ነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች ሲያስተናግዱ ተስተውለዋል᎓᎓ ችግሩም በቤንዚን አቅርቦት ላይ እየተስተዋለ መሆኑን ነው ኢቢሲ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች የገለፁት᎓᎓

የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ አሽከርካሪ የተፈጠረው ችግር በስራው ላይ እቅንቅፋት እንደሆበት ለኢቢሲ ተናግሯል፡፡

“ቢያንስ እኔ የቆምኩት ከ2 ሰአት በላይ ሁኖኛል፤ ከቤተመንግስት አካባቢ ነው የመጣሁት ፡፡የተጨመረው ተጨምሮ ቤንዚኑ በቶሎ ይድረስልን” ሲል ጠይቋል᎓᎓

የነዳጅ ማደያዎች ግን የአቅርቦት ችግር ያለመኖሩን ነው የሚገልፁት᎓᎓በማደያዎቹ አካባቢ ሰልፉ መኖሩን አምነው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ፣ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ችግሩ የአቅርቦት  ሳይሆን ኢታኖል የተቀላቀለበት ቤንዚን ከመጋቢት 7 ጀምሮ ወደ ገበያ በማቅረብ ሂደት የተፈጠረ መስተጓጎል ነው ብሏል᎓᎓

ይሁን እንጂ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚኒስቴሩ ባለሙያዎች በተደረገ ማጣራት አሁን ላይ እየተቃለለ መምጧቱን ገልጿል᎓᎓ችግሩ እንዳይፈጠር ቅድም ዝግጅት ማድረግ አይገባም ነበር ወይ  ሲል አቢሲ ለሚኒስቴሩ ባነሳው ጥያቄ ፣ ሚኒስቴ ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት መደረጉን ገልጾ ይሁንጂ ጊዜው ካለመብቃቱ ጋር ተያይዞ ማደያዎች ለማሽን ማፅጃ የተሰጣቸው ተጨማሪ አንድ ሳምንት ችግሩን እንደፈጠረው አስታውቋል፡፡

ችግሩ በቀጣዮቹ 2 ቀናት ሊፈታ  እንደሚችልም  ሚኒስቴሩ ገልጿል᎓᎓

ሪፖርተር ፡‑ ጌታቸው ባልቻ