በባህር ዳር ከተማ ከ900 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጭ የሙዚየም ግንባታ ለማካሄድ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

በከተማዋ አየር ጤና አካባቢ ለሚገነባው ሙዚየም የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚህ ወቅቱ እንደገለፁት የሚገነባው “የአማራ ህዝቦች ሙዚየም” የክልሉን ህዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና መሰል ሃብቶችን አካቶ የሚይዝ ነው ።

15 ሺህ 650 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለሚያርፈው የሙዚየሙ ግንባታ ዲዛይን ስራ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ ማስተካከያዎች እየተደረጉለት መሆኑን ተናግረዋል።

“ግንባታው በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ ተጀምሮ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ” ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት ሙዚየሙ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚሰራ ይሆናል።

እንደ አቶ ገዱ ገለፃ የሙዚየሙ ግንባታ የአማራን ህዝብ ያለፈ ታሪክ የሚያሳዩ ቅርሶችን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ አላማ ያደረገ ነው ነው።

“የክልሉ መንግስት የግንባታ ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ያደርጋል ” ብለዋል።

የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ