የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ረዳቶች ከሩሲያ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር የሂላሪ ክሊንተንን የምረጡኝ ዘመቻ የሚጎዱ መረጃዎችን መልቀቃቸውን የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ፍንጭ ማግኘቱ ተሰማ፡፡

ኤፍ ቢ አይ የሰብዓዊ ስለላ መረጃዎችን ማለትም የጉዞ፣ የንግድ እና የስልክ ቅጂዎችን እንዲሁም የፊት ለፊት ግንኙነቶች እየመረመረ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እየተናገሩ ናቸው፡፡

የምርመራ ቢሮው የትራምፕ አራት የቀድሞ ረዳቶች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ተነግሯል፡፡ማይክል ፍሊን፣ ፖል ማንፎርት፣ ሮጀር ስቶን እና ካርተር ፔጅ ከሩሲያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ቢሆንም፤ አራቱም በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ኤፍ ቢ አይ ድምዳሜ ላይ ባይደርስም የትራምፕ ረዳቶች ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ከመሆናቸው በላይ የሩሲያ ባለስልጣናት የግንኙነት አግባቦቻቸውን ሳይለውጡ እንዳልቀረ እና ይህም ለክትትል እክል እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡

የኤፍ ቢ አይ የአጸፋ ስለላ ምርመራዎች ጊዜ የሚወስዱ ከመሆናቸውም በላይ ተጠርጣሪዎችን በመደበኛ የወንጀል ክሶች ለማስቀጣት መሞከር ባብዛኛው የሀገሪቱን ምስጥራዊ ፕሮግራሞች እንዲታወቁ እና ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በጥንቃቄ እየመረመረ መሆኑን ነው ያስታወቀው ፡፡

መርማሪዎቹ ከበርካታ ምንጮች የሰበሰቧቸውን መረጃዎች እና ፍንጮች እየመረመሩ መሆኑን ከመግለጽ ሌላ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ምንጭ፦ሲ ኤን ኤን እና ኢንዲፔንደንት