በጥንዶች መካከል ክህደት ተፈፅሞ ወዳጅነት ሲሻክር መተማመንን እንደገና መመለስ እንደሚቻል የስነልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ጤናማ የሆነ ወዳጅነት እና ግንኙነት አለ የሚባው ጥንዶቹ የጋራ ግባቸውን ለማሳካት በአንድ ላይ ሲሰሩ እና እርስ በርስ እየተረዳዱ ሲኖሩ ነው፡፡

መተማመን የሚመጣው በጥንዶቹ መካከል አንዳቸው ለአንዳቸው ልባዊ ፍላጎት ሲያድሩ እና ስኬታማ ግንኙነትን መፍጠር ሲቻል ነው፡፡

መተማመን ጥንዶቹ በተስፋ እንዲኖሩ፣ ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዲጥሩ እና እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ በፍቅራቸው ላይ ተጨማሪ እሴት እየፈጠሩ እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡

በጥንዶች የኑሮ ሂደት ውስጥ የግል ጥቅም እና ፍላጎትን ብቻ ለማሟላት መሞከር ይህንንም ለዘወትር መፈጸም መተማመንን ፈተና ውስጥ ይከተዋል፡፡

የፍቅር ግንኙነት ረጅም እና ውስብስብ ነገሮችን ያቀፈ በመሆኑ፥ በጊዜ ሂደት ከጥንዶች መካከል አንዱ በሆነ አጋጣሚ ክህደት ሊፈፅም ይችላል፡፡

የሰው ልጅ ፍፁም ወይም ከስህተት የፀዳ ባለመሆኑ፥ ሁል ጊዜም ጥንዶች አጋሮቻቸው የሚጠብቁትን ያሟላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡

እናም ሰዎች በስነልቦና ረገድ ብዙ ደካማ ውሳኔዎች የሚወስኑ ፍጥረታት በመሆናቸው በአጋራቸው ላይ ክህደት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡

በዚህ ጊዜም ጥሩ የነበረው የፍቅረኞች ግንኙነት ሊሰበር እስከ መጨረሻውም ሊያበቃለት ይችላል፡፡

ስለሆነም በስህተት የተፈፀመ ክህደት ብርቱውን ፍቅር እና ትዳርን እንዳይፈታ ስለተፈጠረው ጉዳይ መወያየት አስፈላጊ ሲሆን፥ ጥንዶቹ የሚከተሉትን ስልቶች በመጠቀም ክህደትን መቅረፍ እና ፍቅራቸውን ማፅናት ይችላሉ ስንል አቅርበናቸዋል፡፡

1ኛ፡- በተፈፀመው ክህደት ላይ መወያየት

በውይይቱም ክህደት የፈፀመው አጋር በሌላኛው ላይ ጉዳት ማድረሱ በተጎጂው በአግባቡ መገለፅ አለበት፡፡

ይህም የፈፀምነው ክህደት በፍቅረኛችን ወይም በትዳር አጋራችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መፍጠሩን በማመን እንድንፀፀት እና እንድንታረም ይረዳል፡፡

“በተፈጠረው ነገር ተጎድቻለሁ” ከማለት ይልቅ “በፈፀምክብኝ ክህደት ጎድተኸኛል ወይም በፈፀምሽብኝ በደል ጎድተሸኛል” ብሎ መናገሩ ክህደቱን የፈጸመው ሰው የበለጠ ሃላፊነት እንዲሰማው ያደርጋል፡፡

2ኛ፡-ሃቆችን በግልፅ ማውጣት

የፍቅር አልያም የትዳር አጋሮቻችን በፈፀሙት በደል ላይ ሃላፊነታቸውን ከወሰዱ፥ የተከሰተው ሁኔታ ነባራዊ ሃቁ ለምን እና እንዴት እንደተከሰተ በግልፅ መውጣት አለበት፡፡

ከጥንዶች ውስጥ ክህደት የተፈፀመበት ሃቁን ማወቅ ስለሚፈልግ ሁሉንም ነገር በሃቅ እና በግልፅ መናገር መረጋጋት እና መተማመንን እንደገና ለማደስ ይጠቅማል፡፡

3ኛ፡-ክልብ ይቅርታ መጠየቅ እና ይቅርታውን መቀበል

በክህደቱ ውስጥ ጥንዶቹ ይቅርታ መጠየቅ እና መቀበላቸው ተገቢ ነው፡፡

የፈፀሙትን ጥፋት አምኖ ይቅርታ መጠየቅ እና “በሰራሁት መጥፎ ድርጊት ጎድቸሃለሁ፣ ወይም ጎድቸሻለሁ፣ በጥፋቴም ተፀፅቻለሁ” ብሎ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ መተማመንን እንደገና ለማምጣት ይረዳል፡፡

በይቅርታ መጠየቅ ሂደት ውስጥ ፈፅሞ ማመንታት እንደማይገባም ነው የተመከረው፡፡

4ኛ፡-ለክህደቱ በቂ ምክንያት ማቅረብ

ጥንዶቹ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ አጋሮቻቸው ለምን መተማመናቸውን እንደጣሱ ወይም ክህደት እንደፈፀሙ መገንዘብ አለባቸው፡፡

ክህደቱን ለመፈፀም የዳረጓቸውን መሪ ምክንያቶች እና ያነሷቸውን ነገሮች በግልፅ እና በአጥጋቢ ሁኔታ መግለፅ መተማመንን ለማምጣት ወሳኝነት አለው፡፡

5ኛ፡- እቅድ መንደፍ

ጥንዶቹ መካካዱ ለምን እና እንዴት እንደተፈፀመ ካወቁና የጋራ ግንዛቤ ከያዙ በኋላ፥ በወደፊት የህይወት ጉዟቸው ላይ ድጋሚ ክህደት እንዳይፈጠር እና የእርስ በርስ መተማመን እንዲኖር ጥሩ እቅድ መንደፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህም እቅድ ከአሁን በፊት የተፈጠረው ክህደት የተከሰተበትን ነባራዊ ሁኔታ በሚያስረዳ መልኩ በማድረግ፥ በድጋሚ ክህደት እንዳይፈፀም አስቀድሞ ለመከላከል ያመቻቸዋል፡፡

የግል ፍላጎት እና ጥቅምን በግልፅ በመወያየት የጋራ ለማድረግና ገንቢ አስተያየቶች ለመለዋወጥም ያስችላል ።

6፡- እቅዱን የመተግበሪያ ስልት ማውጣት

ክህደትን ለመከላከል እቅድ ከመንደፍ በሻገር መተግበሪያ ስልቶችን ማውጣት የሚገባ ሲሆን፥ ስልቶቹም ክህደትን ላለመፈፀም ትክክለኛ አቋም ለመያዝ ይረዳሉ፡፡

እቅዱን ገቢራዊ በማድረግ ሂደት ህግና ደንቦችን በማውጣት እርስ በርስ መገማገም እና የባህሪ ለውጦችን መቆጣጠርም ይቻላል፡፡

ግልፅነት መተማመንን እንደገና ለመገንባት ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡

7፡-የእቅዱን ገቢራዊ ሂደት መገምገም

ጥንዶች በህይወት ኡደታቸው ውስጥ መተማመንን ለማምጣት ያወጡት እቅድ፥ በምን መልኩ እየቀጠለ እንደሆነ የሚገመግሙበት የጊዜ ገደብ ሊያስቀምጡም ይገባል፡፡

ምን ዓይነት ስራ እየተሰራ እንደሆነ እና ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ተግባራት ካሉም ለመለወጥ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቁጭ ብሎ መወያየት ወሳኝ ነው፡፡

አንዳቸው ለአንዳቸው በገቡት ቃል መሰረት እየኖሩ ከሆነ፥ እየተመሰጋገኑ እና ቀጣይ እንዲሆን እየተመኙ ህይወትን መምራትም መልካም መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

8ኛ፡- ለሚፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ትዕግስተኛ መሆን

በኑሮ ሂደት ውስጥ በተፈጠረ ስህተት ጠፍቶ የነበረውን መተማመን፥ እንደገና ለመመለስ ረጅም ጊዜ እና ፈታኝ ሁኔታዎችን ሊጠይቅ ይችላል፡፡

አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች አሉታዊ ጫና የማይፈጥሩ ከሆነና በድንገት የተከሰቱ ከሆነ፥ እንዳላዩ ሆኖ በትዕግስት ማለፍ መተማመኑን ለመመለስ መልካም አጋጣሚ ይሆናል፡፡

ለሚሰሩ ስህተቶች ይቅር ባይ መሆን ለጥፋተኞቹ ሃላፊነቱ በእነርሱ ላይ እንዲሆን እና ከስህተታቸው እንዲታረሙ ይገፋፋቸዋል፡፡

ባለፈው ጥፋትም አጋርን መኮንን እንደማያስፈልግ ነው የተገለጸው።

በጥንዶች መካከል የጥሩ ጓደኝነት መኖሩ የሚረጋገጠው ጥሩ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በሚኖራቸው ደስተኛነት ሳይሆን፥ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በቅርበት አብረው ችግሩን ለመቅረፍ በሚጥሩበት መንገድ ነው፡፡

የአጋራችን ጉዳት የእኛም ጉዳት ሲሆን እና የተፈጠረውን ስህተት አርሞ ታማኝ ሲሆኑ እውነተኛ ፍቅር ይኖራል፡፡