የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሳውዲአረቢያ  የጀመሩት  የመጀመሪያ የውጭ አገር ይፋዊ ጉብኝት  ውጤታማ ነበር ተባለ ።

አሜሪካና ሳዑዲ አረቢያ የ350 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የአረቡ አገራት አክራሪነትና ጽንፈኝነትን እንዲዋጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያቸውን የውጭ ሀገር ይፋዊ ጉብኝት በሳዑዲ አረቢያ አድርገዋል ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሪያድ ንጉስ ካሊድ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በንጉስ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝና ሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት አሜሪካ ከሳዑዲ አረብያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር አጀንዳን የሰነቀ ነው ተብሏል፡፡ አክራሪነትን መዋጋትም ሌላው የመሪዎቹ ውይይት የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡

ሁለቱ አገራት በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ተወያይተዋል መክረዋል፡፡ የመሪዎቹን ውይይት ተከትሎ በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የሆነውን የ350 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም 110 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው በመከላከያ ዘርፍ የሚውል መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

አገራቱ በኢኮኖሚና በመከላከያ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ የፈረሙት የንግድ ስምምነት በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚተገበር እንደሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን መናገራቸውን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡

የንግድ ስምምነቱ ሳዑዲ አረቢያ በ2030 ላቀደችው ዘመናዊና ሁሉን ዓቀፍ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይን ዕውን ለማድረግ ይረዳል ተብሏል፡፡ የፕሬዚዳንቱ የሳዑዲ ጉብኝትም ውጤታማ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

አሜሪካ ፅንፈኛውን አክራሪ ድርጅት አይ ኤስን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት እያረገች መሆኑን ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስረድተዋል፡፡

የአረብ ኢስላሚክ አሜሪካ ስብሰባ ላይ በመሳተፍ አክራነትን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ የአረቡ አገራት ተገቢውን ጥረትና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ የአረቡ አገራት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጠበቅ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተስፋ ማድረጋቸውን ቢቢስ በዘገባው አመልክቷል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚን ካሰናበቱ ወዲህ በሀገር ውስጥ ተቃውሞው በርትቶባቸዋል። ይህም በጉብኝታቸው ላይ ጥላውን እንዳያጠላ ስጋታቸውን የገለፁ አልጠፉም፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለስምንት ቀናት በሚዘልቀው ጉብኝታቸው ከሳዑዲ አረቢያ በተጨማሪ ሰኞና ማክሰኞ እስራኤልና  የፍልስጤም ግዛቶችን ይጎበኛሉ፡፡ ረቡዕ ደግሞ ሮምና ቤልጂየምን የመጎብኘት ዕቅድ የያዙ ሲሆን ከፖፕ ፍራንሲስና ከቤልጂየም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ፡፡

ሀሙስ በብራሰልስ በሚደረገው የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ስብሰባ ላይም ይገኛሉ ተብሏል፡፡

አርብ በጣልሊያኗ ሲሲሊ ከተማ በሚከፈተውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው የቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ላይ በመሳተፍ የስምንት ቀናት ይፋዊ የጉብኝት መርሃ ግብራቸውን እንደሚያጠናቅቁ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ( ምንጭ:ሲኤን ኤን)