በኢትዮ – አይ ሲቲ መንደር በ480 ሚሊየን ብር የሶፍትዌር ልማት ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለማዕከሉ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት፥ ሀገራት ያሉባቸውን የእድገት ክፈተቶች ለመሙላት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትልቅ ሞተር ነው ብለዋል።በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በዕድገት ሂደት ላይ ለሚገኙ አገሮች የቴክኖሎጂ መስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።ባለፈው ዓመት የተመረቀው የኢትዮ አይ ሲቲ መንደር በአሁኑ ወቅት ወደ 20 የሚሆኑ የአገር በቀል ተቋማት ገብተው እየሰሩበት ይገኛል።በቀጣይም “ለአገር በቀል ተቋማት ልምድ ማካፈል የሚችሉ የውጭ ተቋማት እንዲገቡ ይደረጋል” ነው ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን።ከእነዚህ መካከል አንዱ የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ የራሱን ህንጻ ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባር ቀደም መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት።የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ፈጥኖ ወደ ስራ በመግባት ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆኑን ጠቁመው፥ ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኝ ደረጃ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።በአይ ሲቲ መንደሩ ያሉ ተቋማት የዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት አሟልተው ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን፥ መንግስት የተለያዩ ሥልጠናዎችና ልምዶች የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል ብለዋል።የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በእምነት ደምሴ በበኩላቸው፥ የሚገነባው ማዕከል የሶፍትዌር ማልሚያ፣ ማበልጸጊያ እና ምርመራ ማካሄጃ ይሆናል ብለዋል።የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት ከአይ ሲቲ መንደር ህንጻ ተከራይቶ የተለያዩ የሶፍትዌር ማበልጸጊያ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።በዚህም ለ250 የሚሆኑ ሠራተኞች የስራ ዕድል ፈጥሯል።ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከ1 ሺህ 100 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ታውቋል።የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ከተመሰረተበት 1996 ዓ.ም ጀምሮ ለተለያዩ የቢዝነስ ተቋማት ሥራ ማቀላጠፍያ አገልግሎት የሚውሉ የሶፍትዌር ሲስተሞችን በማልማትና በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።