በአፍሪካዊቷ ሀገር ማዳጋስካር በአለማችን የብዙዎችን ቀልብ ከሚስበው የእግር ኳስ ጨዋታ ይልቅ የዶሮዎች ግጥሚያ በርካታ ተመልካች አለው።

በመዲናዋ አንታናናሪቮ አምቦሂማንጋኪሊ አካባቢ የዶሮዎች ፍልሚያ መመልከት የተለመደ እና ተወዳጅ መዝናኛ ነው።

የዶሮ ግጥሚያ በሚኖርባቸው ጊዜያት ከ400 በላይ ሰዎች በአምቦሂማንጋኪሊ የዶሮዎች መፋለሚያ ስፍራዎችን ያጣብባሉ።

ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም የዶሮ አርቢዎች ምርጥ ተፋላሚ ዶሮዎቻቸውን ለማሳየት ወደ አምቦሂማንጋኪሊ ያመራሉ።

የግጥሚያዎቹ ተመልካቾችም ያሸንፋል ብለው ለሚያስቡት ዶሮ ገንዘብ በማስያዝ ከሌሎች ሰዎች ጋር ይወራረዳሉ።

በአንድ ግጥሚያ ብቻም እስከ 12 ሚሊየን አሪያሪ ወይንም 3 ሺህ 870 የአሜሪካ ዶላር በውርርድ ይንቀሳቀሳል ተብሏል።

የዶሮዎች ግጥሚያ የሚጠናቀቀው ተጋጣሚዎቹ ለሁለት ስአታት ሳይሸናነፉ ከቆዩ፣ አንደኛው ተጋጣሚ ሁለቱንም አይኖቹን ካጣ አልያም የመፋለም ፍላጎት ካላሳየ፣ ወይንም ሁለቱም ከሞቱ ነው።

በዶሮዎቹ ፍልሚያ የሞት ዜና ብዙ ጊዜ አይሰማም ተብሏል።

ውድድሩ ፊሽካ በያዙ ዳኞች በአግባቡ እንደሚመራም ነው የተነገረው።

በአፍሪካ የዶሮ ፍልሚያ ብዙ የተለመደ ነገር ባይሆንም በማዳጋስካር ከ700 አመት በላይ የቆየ እድሜ አለው። ባህሉ በእስያ ስደተኞች አማካኝነት ወደ ማዳካስካር መግባቱ ይነገራል።

የዚህ ውድድር አዘጋጅ የሆነው ሴትራ ራባሪ አንድሪኒና እንደገለጹት፥ በማዳካስካር የዶሮዎች ፍልሚያ ከእግር ኳስ ጨዋታ ይልቅ ታዋቂ እና በርካታ ተመልካች ያለው ውድድር ነው።

ምንጭ፦ http://africa.cgtn.com/