ጋዜጠኛ፣ ተውኔት እና የሲኒማ ጸሐፊ፣ ደራሲና የፊልም አዘጋጅ ናት፤ ኖራ ኤፍሮን። በዓለማችን ካሉ ደፋርና ብርቱ ሴቶች መካከል ትገኛለች። ይህቺ የብዙ ሙያዎች ባለቤት የጾታ መድሎን የታገለች ናት። በተለይም በካሜራ ፊትና ከጀርባ ሴቶች በተሳሳተ መንገድ መገለጻቸውን በብዙ ትቃወማለች፤ ኖራ ኤፍሮን። ይህንንም በተግባር ለመታገል የተጠቀመችው ጥበብን ነበር፥ ከጋዜጠኝነቷ በተጨማሪ ወደ ታላቁ ፊልም አምራች ሆሊውድ አቅንታ ለተለያዩ ሽልማቶች ዕጩ ያደረጓትን የተለያዩ ፊልሞች ከጽሑፍ ሥራው ጀምሮ ዝግጅቱን ሁሉ ሸፍና ሠርታለች። ከዓመት በፊት የወጣ «ማርያ ክሌር» የተባለ መጽሔት «እኔ ለመጻፍ የምሞክረው በትክክልም እንደሚታየው የሴቶችን ውስብስብ እና አስደናቂ የሆነ ሚና ነው» ብላ ተናግራለች ሲል አስፍሯል። ወደሥራ ዓለም ከመቀላቀሏ በፊት ያለፈቻቸው ፈተናዎች ነበሩ። ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ከሞከረቻቸው ሥራዎች መካከል ኒውስ ዊክ ለሚባል መጽሔት በጸሐፊት ለመሥራት ያቀረበችው ጥያቄ ነበር። በዚያም ሴት እንደማይቀጥሩ ሲነግሯት ፖስታ አመላላሽ በመሆን ተቋሙን ተቀላቀለች። ብዙም አልቆየች፤ ተቋሙን ለቅቃ ወጣችና ጾታዊ መድሎ ይፈጽማልና መጽሔቱን ከሰሰች። በአንድ አጋጣሚ ኒውዮርክ ፖስት ላይ በጻፈችው አጭር ጽሑፍ አዘጋጁ ዓይን ውስጥ ገባች። ከዚያም በኋላ የጽሑፍ ሥራዋ ስኬታማ ጉዞውን ቀጠለች። በሴቶች ጉዳይ ላይ በርካታ ሥራዎችን ታስነብብ ጀመር። በሂደትም ወደ ፊልሙ ዓለም ተቀላቀለች፤ እንዲያ እንዲያ እያለ ዛሬ ላይ በተለይ በሴቶች ዙሪያ ብዙ ከሠሩና ጎልተው ከታዩ ስኬታማ ሴቶች መካከል አንዷ ለመሆን በቃች። ኖራ ኤፍሮን ትውልዷ በአገረ አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ከአይሁድ ቤተሰቦች ነው። አምስት ሴት ልጆች ካሉበት ከዚህ ቤተሰብ እርሷ የመጀመሪያ ልጅ ናት። እድገቷም የነበረው የሆሊውድ ባለሙያዎች በብዛት በሚኖሩባተ ቤቨርሊ ሂልስ በምትባል ከተማ ነው። ጥበብን አንድም ከቤተሰቦቿ የወረሰች ይመስላል፤ እናትና አባቷ ሁለቱም በፊልምና ተውኔት ጸሐፊነት ይታወቃሉ። ሁለት ታናናሽ እህቶቿም የተውኔት ጽሑፎችን ያቀርቡ ነበር። ሌላዋ ሀሊያ ኤፍሮን የተባለች እህቷ እንዲሁ ጋዜጠኛ፣ የመጽሐፍ ገምጋሚና ስለወንጀል ታሪክ የምትጽፍ ደራሲ ናት። እንግዲህ በዘር ነው ማለት ሳይቻል አይቀርም። ኖራ ኤፍሮን የትዳር ሕይወቷ ከፍታና ዝቅታን ያስተናገደ ነበር፤ ይህንንም በመጻሕፍቶቿ ውስጥ አካትታለች። ሦስት ጊዜ ያገባች ሲሆን እስከሕይወቷ ፍጻሜ የቆየው ሦስተኛው የትዳር አጋሯ ጋር ሃያ ዓመታትን አሳልፋለች። የሁለት ወንድ ልጆችም እናት ናት። ሕይወቷም ያለፈው በሳምባ ምች በሽታ ምክንያት ነበር፤ በህመሙ ስለመያዟ ለብዙዎች አልተናገረችም ነበርና ሞቷ ድንገተኛ ሆኖ ብዙዎችን አስደግጧል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 የካቲት ወር በሃያ ስድስተኛው ቀን ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው። ሥራና ትግሏ ሁሉ ግን ዛሬ ድረስ የሚነገር ታሪክና ማስተማሪያ ሊሆን ችሏል።