የሩሲያው የ2018 የአለም ዋንጫ ማጣሪያዎች በተለያዩ ቀጠናዎች እየተካሄዱ ነው።

በደቡብ አሜሪካ ምድብ ሌሊቱን የተለያዩ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የምድቡ መሪ ብራዚል ወደ ሞንቴቪዲዮ አምርታ ኡራጓይን 4 ለ 1 አሸንፋ ተመልሳለች።

ባለሜዳዎቹ በካቫኒ ጎል ቀደሚ ቢሆኑም፥ ሴሌሳኦቹ በፓውሊንሆና በኔይማር ጎል ታግዘው ሶስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።

በሊዮኔል ሜሲ የምትመራው አርጀንቲናም ከገባችበት አጣብቂኝ የወጣችበትን ውጤት ማስመዝገብ ችላለች።

በሜዳዋ ቺሊን ያስተናገደችው አርጀንቲና በሊዮኔል ሜሲ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል 1 ለ 0 አሸንፋለች።

Paulinho.jpg

ፓውሊንሆ

ፓራጓይ በበኩሏ በሜዳዋ ኢኳዶርን አስተናግዳ 2 ለ 1 በማሸነፍ አስፈላጊውን ሶስት ነጥብ ይዛ ወጥታለች።

ወደ ሩሲያ ለማምራት እድል ያላት ኮሎምቢያም ቦሊቪያን አስተናግዳ 1 ለ 0 ረታለች።

ቬኒዝዌላ ከፔሩ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ፥ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በደቡብ አሜሪካ ምድብ እስካሁን 13 ጨዋታዎች ሲደረጉ ብራዚል 30 ነጥቦችን በመያዝ ምድቡን ትመራለች።

ኡራጓይ በተመሳሳይ ጨዋታ 23 ነጥቦችን ስትይዝ አርጀንቲና በ22 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዛለች።

ኮሎምቢያ በ21፣ ኢኳዶር እና ቺሊ ደግሞ በእኩል 20 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

የፊታችን ማክሰኞ ጨወታዎች ሲቀጥሉ፥ አርጀንቲና ወደ ቦሊቪያ በማቅናት አስቸጋሪውን ጨዋታ ታደርጋለች።

ኢኳዶር ደግሞ ኮሎምቢያን ስታስተናግድ ረቡዕ ቺሊ ከቬኒዝዌላ ትጫወታለች።

ብራዚል በሜዳዋ ፓራጓይን ስታስተናግድ ኡራጓይ ወደ ፔሩ ታመራለች፡፡

የአለም ዋንጫው በተለያዩ ቀጠናዎች ሲካሄድ፥ዛሬ በአውሮፓ በተለያዩ ምድቦች የሚገኙ ቡድኖች ምሽት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።