የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሰንግ አዲሱን ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ስልኩን ትናንት በይፋ አስተዋውቋል።

ጋላክሲ ኤስ8 ኩባንያው በኖት 7 ስልኩ ያጋጠመውን የ3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማካካስ እንደሚረዳው ነው የተነገረው።

የአይፎን ተፎካካሪ ሳምሰንግ አዲስ ስልክ በሁለት አይነት የስክሪን ስፋቶች ነው የመጣው፤ ጋላክሲ ኤስ8 በ5 ነጥብ 8 ኢንች እንዲሁም ጋላክሲ ኤስ8 ፕላስ በ6 ነጥብ 2 ኢንች።

ኩባንያው ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ስልኩ ከዚህ ቀደም በጋላክሲ ኤስ7 ስልኮቹ ሲያጋጥም የነበረው አይነት የመፈንዳት ችግር እንደማያጋጥመው ገልጿል።

የመለቀቂያ ጊዜ

ሳምሰንግ አዲሱን ጋላክሲ ኤስ8 ስልክ ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 21 2017 ጀምሮ ለአሜሪካ ገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

ከሚያዚያ 28 ጀምሮ ደግሞ ብሪታንያን ጨምሮ ወደ መላው አለም ስማርት ስልኩ ለገበያ ይውላል ብሏል።

በቅድመ ትዕዛዝ ግን ከሚያዚያ 20 በፊት ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ ነው ኩባንያው የገለፀው።

ዋጋ

ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ስልክ 720 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል።

ይህም በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ ካሉ ስማርት ስልኮች ሁሉ ውዱ ያደርገዋል።

ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ስልክ…

– 64 ጊጋ ባይት ውስጣዊ የመያዝ አቅም አለው፤ የመያዝ አቅሙን እስከ 256 ጊጋ ባይት ለማሳደግም ሚሞሪ ካርድ ይቀበላል።

– 4 ጊጋ ባይት ራም ያለው ሲሆን፥ በቻይና እና በኮሪያ ለገበያ የሚቀርቡት ስልኮች 6 ጊጋ ባይት ራም እንዲኖራቸው ተደርጓል።

– 12 ሜጋ ፒክስል የጀርባ፤ 8 ሜጋ ፒክስል የፊት ካሜራ ይዟል።

– ባትሪው 3000 ሚሊአምፒር በስአት ነው።

– በጣም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው (አልትራ ኤች ዲ) ቪዲዮዎችን ያጫውታል።

– ሁለት ጥራት ያላቸው ድምፅ ማጉያዎች አሉት።

– አቧራ እና ውሃን መቋቋም የሚችል ሆኖ ነው የተሰራው።

– በፍጥነት ሀይል ይሞላል (ቻርጅ ይደረጋል)።

– የስልኮቹ ባለቤቶች በፊት ምስላቸው አማካኝነት ስልካቸውን መዝጋት እና መክፈት ይችላሉ።

– በጥቁር፣ ሰማያዊ፣ ግራጫ፣ ወርቃማ እና ሲልቨር የቀለም አማራጭም ነው የቀረበው።

ሳምሰንግ በጋላክሲ ኤስ8 እና ኤስ8 ፕላስ ስማርት ስልኮቹ ተቀዛቅዞ የነበረውን ገቢውን እንደሚያሻሽልና የስማርት ስልክ ገበያውን እንደሚቆጣጠር ይጠበቃል።