በመካከለኛው የሜዲትራኒን ባህር በርካታ ስደተኞችን ይዛ የሰመጠችውን ጀልባ ሲፈልጉ የነበሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች የአራት ቀን እድሜ ያላት ህጻን ጨምሮ 480 ስደተኞችን መታደጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ሁለት ጀልባዎች ከ200 የማያንሱ ስደተኞችን ይዘው ከሊቢያ የባህር ዳርቻ 22 ማይል ርቀት በሜዲትራኒያን ባህር የሰመጡ ሲሆን፥ ህጻኗም በአንደኛው ጀልባ ውስጥ ነበረች ተብሏል፡፡

ጀልባዎቹ ከመካከለኛው እና ሰሜን አፍሪካ፣ ከስሪ ላንካ እና ከየመን የተነሱ ስደተኞችን ይዘው ነው የሰመጡት፡፡

ከነፍስ አድን ሰራተኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ዳኒኤል ካልቬሎ “ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰዎችን በባህሩ ውስጥ ሞተው አስከሬናቸውን አውጥቼ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አዲስ ህይወትን ታድጊያለሁ” ሲል ተናግሯል፡፡

rescue.jpg

የህጻኗ እናት የ29 ዓመቷ ናይጀሪዊት እና አባቷ የ34 ዓመቱ ጋናዊ በሕይወት አድን ሰራተኞች ከባህሩ ወጥተዋል፡፡

እነኝህ ሰዎች በሊቢያ ከሁለት ዓመት በላይ የኖሩ ሲሆን፥ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላም ወደ አውሮፓ ለመግባት ነበር ጉዟቸውን የጀመሩት፡፡

“ወደ ጀርመን ወይም ወደ ፈረንሳይ ለመግባት ነበር ፍላጎታችን፤ በዚያም ቤተሰቦቻችን እንዲኖሩ እንመኝ ነበር፤” ሲል የህጻኗ አባት ሪቻርድ ኦሄኔ ገልጿል፡፡

የነፍስ ማዳን ስራው በስፔኑ “ፕሮአክቲቫ ኦፕን” መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው የተሰራው፡፡

በሕይወት የተገኙት ስደተኞችም ቀድሞ በአሳ ማጥመጃ ጀልባነት ያገለግል ወደነበረው ጎልፎ አዙሮ ጀልባ የተሸጋገሩ ሲሆን እሁድ አመሻሽ ሲሊ ደርሷል ተብሎ ይገመታል፡፡

በፈረንጆች በዚህ ዓመት ከ600 የማያንሱ ሰዎች በሜዲትራኒን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሰጓዙ የባህር እራት ሆነዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባስቀመጠው መረጃ መሰረት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 4 ሺህ 600 ስደተኞች ሞተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

ምንጭ፡-http://africa.cgtn.com