አሜሪካዊቷ የናሳ ጠፈርተኛ ፔጊ ዊትሰን በህዋ ላይ ረጅም ጊዜ በመቆየት አዲስ ክብረ ወሰን ይዘዋል፡፡

እኒህ ሴት የጠፈር ተመራማሪ ዛሬ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ አማካኝነት ከኦቫል ኦፊስ በቀጥታ መልዕክት ይገናኛሉ ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ልጃቸው ኢቫንካ ፔጊ ዊትሰንን እንኳን ደስ አለዎት እንደሚሏቸው ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) መረጃ እንደሚያሳየው ዊትሰን በጀፍ ዊሊያም የተያዘውን ለ534 ቀናት በጠፈር የቆይታ ጊዜ ነው ያሻሻሉት፡፡

ዊትሰን ህዋ ላይ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ማዕከል የደረሱት፥ በፈረንጆች ህዳር 19 ቀን 2016 ላይ ነበር፡፡

በመጪው መስከረም ወርም ወደ ምድር እንደሚመለሱ ይጠበቃል፡፡

ዊትሰን የጠፈር ምርምር ጣያቢው ሴት አስተዳዳሪ በመሆን፥ የመጀመሪያዋ ተመራማሪ ናቸው፡፡

ማዕከሉን ሁለት ጊዜ ማለትም በፈረንጆች 2008 የመሩት ሲሆን አሁንም እያስተዳደሩት ይገኛሉ።

በተጨማሪም ወደ ህዋ ብዙ ጉዞዎችን ያደረጉ የመጀመሪያዋ ሴት ጠፈርተኛ በመሆን የሚቀድማቸው የለም ነው የተባለው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኦቫል ኦፊሳቸው ሆነው ዊትሰን ደግሞ በዓለም አቀፉ የጠፈር የምርምር ማዕከል ህዋ ላይ ሆነው፥ የ20 ደቂቃ ቀጥታ የመልዕክት ልውውጥ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ይህ ሁነትም በናሳ ቴሌቪዥን፣ በፌስቡክ ገፁ እና በድረ ገጹ እንደሚተላለፍ ተጠቁሟል፡፡