የተለያዩ የጥበብ መሣሪያዎችን በሥራዎቿ ላይ ማዋሏ ኤልሳቤጥ ሀብተ ወልድን ሁለገብ አርቲስት ያስብላታል፡፡ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር ሁልጊዜም የምትታትረው ኤልሳቤጥ የተሰጣት ሠዓሊ ናት፡፡ ለዚህም ምስክርነቱ አንዱ በኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ኪዩሬተርነት የተሰናዳው ‹‹ራስን በራስ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ዐውደ ርዕይ ነው፡፡ ይህ ዐውደ ርዕይ በዘመናዊ ሥነ ጥበባት ሙዝየም በገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል ከሚያዝያ 13 እስከ ግንቦት 13 ለሕዝብ ክፍት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸውን አገር በቀል ተክሎች እንሠት እንዲሁም ኮባና የተለያዩ ፎቶግራፍ የአኒሜሽን ሥራዎች በመጠቀም ምን ያህል በመሣሪያዎች መገደብ እንደማይቻል ያሳየችበት ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ጥምረት ብዙዎችን ያስደነቀ ውህደት በመፍጠር ለየት ያለ የጥበብ ሥራም ማሳየት ችላለች፡፡ በእነዚህም ሥራዎች የተለያዩ ሐሳቦችን ትዝታን፣ ሴትነት፣ ዘመናዊነት፣ ተፈጥሮንና ሌሎች ሐሳቦችንም አንስታበታለች፡፡ ይኼ ሁለገብነት ብዙ ተመልካቾችን አዕምሯቸውን እንዲፈትሹ ያደረገ ሥራ ነወ፡፡ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ኤልሳቤጥ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከ32 ዓመት በፊት ተመርቃለች፡፡ የትምህርት ጉዞዋንም በመቀጠል ባልቲሞር ሲቲ ኮሚዩኒቲ ኮሌጅ እንዲሁም በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በሥዕል የትምህርት ጥናት ዘርፍ የድረ ምረቃ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ በትሁትነቷ የምትታወቀው ኤልሳቤጥ አዲስ አበባ ከተመለሰችበት ከ15 ዓመታት ጀምሮ በጥበቡ ትዕይንት ላይ በንቁ ትሳተፋለች፡፡ ከእነዚህም ሥራዎቿ ውስጥ ‹‹አፍሪካ ራይዚንግ›› በሚል ርዕሥ በአፍሪካ ኅብረት የታየው ሥራዋ፣ ስለኢትዮጵያ ሴት አርቲስቶች ታሪክ የሚዘግበው ‹‹ድምጿ›› የሚለው ፊልም ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማ በዓለም አቀፍ መድረክም በፓሪሽ ጋለሪ፣ በስሚዝሶኒያን ናሽናል ሙዝየም አፍሪካን አርትና ሳሙኤል ፒ ሀርን ሙዝየም አሳይታለች፡፡ በቅርቡ የተከፈተውን ዐውደ ርዕይና የጥበብ ጉዞዋን በተመለከተ ከሪፖርተር ጥበበሥላሴ ጥጋቡ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርብ ከተከፈተው ዐውደ ርዕይ ርዕሥ እንጀምርና ‹‹ራስን በራስ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይኼ ስያሜ ለጥበብ ሥራዎችሽ ከተጠቀምሽበት ኮባና አገር በቀል ተክል ከሆነው እንሠት ጋር ስለተያያዘ ነው፡፡ ወይስ ካነሳቻቸው ሐሳቦች በቀጥታ ስለሚገናኝ ነው?
ኤልሳቤጥ፡- ‹‹ራስን በራስ›› የሚለው ብዙ ነገርን ይሸፍናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በራስ መቆም የሚለውን ሐሳብ ይገልጻል፡፡ ለመሥሪያ የተጠቀምኩበትን እንሠትን ቀጥታ ብንወስደው የራሳችን የሆነ አገር በቀልና ብዙ ጥቅሞች ላይ የሚውል ተክል ነው፡፡ ይህ ተክል ከምግብ በላይ ለልብስ፣ መጠለያ፣ ቅርጫት፣ ለበዓላት አገልግሎት የሚውል ነወ፡፡ በተለይም ከምግብ ደኅንነት ጋር ተያይዞ፣ ከረሃብ፣ ከልመና የሚያወጣን ባንክ ውስጥ እንዳለ ጠቃሚ ሀብትና ቅርስ መታየት ያለበት ተክል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዐውደ ርዕዩ ወቅት ተደርጎ በነበረው ውይይት ላይ የጥበብ ሥራዎችሽ ሴትነት፣ ትዝታ፣ ድግግሞሽ፣ ሕይወት፣ እንዲሁም ዕውቀትን ከማፍራት ጋር ተያይዞ ተነስቷል፡፡ በሥራዎችሽ ልታነሻቸው የፈለግሻቸው ሐሳቦች ምንድን ናቸው? ለመሥሪያ ከተገለገልሽበት ቁሶች ጋር ያላቸው የሐሳብ መስተጋብር ምን ይመስላል?
ኤልሳቤጥ፡- ሁልጊዜም ቢሆን ለጥበብ አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎች የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ አንድ መልዕክት ወይም የጥበብ ሥራ በምንሠራበት ወቅት ታሪኩ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክ የመንገሪያ ዘዴ፣ የምንጠቀምበት መሣሪያ ከፍተኛ ሥፍራ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ብዙ ሐሳቦች የሚነሱት ደግሞ ከአካባቢያችን ነው፡፡ ጠዋት ጠዋት ልጆቼን ትምህርት ቤት ላደርስ በምሄድበት ወቅት ከተማው ሲጠረግ ያጋጥመኛል ወዲየው ደግሞ ይቆሽሻል፡፡ ይኼ በሬ አካባቢም ያለ ሁኔታ ነው፡፡ ይኼነገር ግራ ያጋባኛል፡፡ በአንድ ቀን ሊቀየር የማይችልና በከፍተኛ ሥር ነቀል ለውጥ ሊስተካከል የሚችል ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ሐሳብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ባዮሚሚክሪ›› ስለሚባል እሳቤ ብዙ የምርምር ሥራዎችን እያነበብኩ ነው፡፡ ይህ ባዮሚሚክሪ የሚባለው እሳቤ ሰው ለሚያጋጥመው እክሎች ወይም ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የተፈጥሮን ሕግጋት፣ ዘዴዎች ማየት እንዲሁም መተግበር ነው ተፈጥሮ ለዘመናት እኛ የምንታገላቸውንና የምንንገዳገድባቸውን ችግሮች ፈታለች፡፡ ስለዚህ በተፈጥሯዊ መንገድ ማምረት፣ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ ሒደቶችንም መከታተል ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ በመማር አሁን ላለውም ሆነ ወደፊት ለሚቀጥለው ትውልድ የምትሆን ምቹ ዓለምን መፍጠር ነው፡፡ በዚህም ምርምሬ ወቅት ራሷን በራሷ ከቆሻሻ ስለምታፀዳው የሎተስ ተክልን አገኘሁ፡፡ የሰው ልጅ በዓለም ላይ ካሉት ፍጡራን የበላይ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ ነገር ግን ቀላል የሚመስለውን ቆሻሻን የማስወገድ ሥራ በመታገል ላይ ነው፡፡ ለሺዎች ዓመታት ግን እንስሳት፣ አትክልቶች ከእኛ በመብለጥ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ያውቃሉ፡፡
ወደ ጉራጌ አካባቢ በምሄድበትም ወቅት ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቀውን የእንሠት አዘገጃጀትና ምንጣፍ ሲሠሩ ተመለከትኩ የሥራን አስፈላጊነትና ያለንን ጊዜ ማባከን እንደሌለብን የተረዳሁበት ወቅት ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼም የሎተስን ምሳሌ በመውሰድ አካባቢዬን ማፅዳት ጀመርኩ፡፡ በሒደቱም ወደ ጠቃሚ ቁስ መቀየር ጀመርኩ፡፡ በዚህም ነው ለቡና ማስቀመጫነት የሚገለገሉበት የማቶትን ሥራ የጀመርኩት ማቶት ለሚሠበሩ ነገሮች ለምሳሌ ለጀበና ማስቀመጫነት ያገለግላል፡፡ ዘይቤያዊውን ፍቺ በምንወስድበት ወቅት ማቶት መሠረታችንና መነሻችን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እንሠት ከዐመት ዓመት የማይነጥፍ ተክል ነው፡፡ ይኼም የማያቋርጥ መሆኑ ሕይወትን ይገልጻል፡፡ የማቶት አሠራር ላይ ያለው ድግግሞሽና ክብነትም የሕይወትን ድግግሞሽና የማያቋርጥ ዑደት በተጨማሪ ይወክላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መሥራትን ማቶት ሲሠራ ያለው ድግግሞሽ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ የማቶት ክብ ቅርፅ ኅብረትን እንዲሁም የሴትነት መንፈስን ይወክላል፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ የሴትነት መንፈስ (ንጥረ-ነገር) በውስጣችን አለ፡፡ ይህ የሴትነት መንፈስ (ንጥረ-ነገር) ጥበብ፣ ማመዛዘንና መተሳሰብን፣ ሐዘኔታ በውስጡ አለበት፡፡ እነዚህ ጥሩ ነገሮች ብዙ ጊዜ ይረሳሉ፡፡ ይኼ ወንድ ወይም ሴት ከመሆን ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ነገር ግን በውስጣችን ያለው የሴትነት መንፈስ በተፈጥሮ የተሰጠንና ፀብንና መላተምን የማያበረታታ ነው፡፡ በዚህ ዐውደ-ርዕይ ላይ ማቶት፣ የፎቶግራፍ ትዕይንት፣ አኒሜሽን፣ ፅናትን መቻቻልን ኅብረትን፣ ዕውቀትንና የመሳሰሉትን ብዙ ሐሳቦችን ያነሳል፡፡
ሪፖርተር፡-በቀደመው ጊዜ ሰዎች የማምረቻ መሣሪያዎችን እንዲሁም ምርትን በተወሰነ መልኩ ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ በተለይም ከምግብና ከልብስ ጋር በተያያዘ መልኩ በአሁኑ ሰዓት ግን ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲሁም የግብይት ሥርዓት ይኼንን ሁኔታ ቀይሮታል፡፡ ምናልባት እንሠትና ኮባን መጠቀምሽ የማምረቻ መሣሪያዎችን ወይም ምርትን እንደገና የመመለስ ጥያቄ ይሆን?
ኤልሳቤጥ፡- አዎ በትክክል፡፡ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ አንድ ቤት ሄጄ ዳንቴል አየሁ፡፡ ዳንቴል ለዘመናት ቤትን ማስጌጫ ይጠቀሙበታል ያለው የቀለም ጥምረት በጣም የሚገርም ነው፡፡ ይህ የቀለም ውህደት ለዘመናት ሴቶች ቤተሰብ ውስጥ አንድ ላይ ቤተሰቡን ለማምጣት የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚና ይወክላል፡፡ በአኒሜሽን ሥራዬም የተጠቀምኩትም ቴክኒክ (ኢንቨርስ) የሚባለውን ነው፡፡ ይኼም ቴክኒክ የውኃ ጠብታ ከቅጠሏ ፈሶ ሲመለስ የሚያሳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አባባል ‹‹የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም›› የሚል አለ፡፡ ምንም እንኳን የምወደው አባባል ቢሆንም አይቻልም የሚባሉ ነገሮችን መመለስ መቻል አለብን፡፡ በዳንቴሉ ላይ ያለውን የክር ትስስር የቀለም ውህደት ላይ በአሁኑ ጊዜ ለምን አንተገብርውም፡፡
ሪፖርተር፡- ባለው የዘመናዊነት ጉዞ ከፖለቲካውና በኢኮኖሚው ከምዕራቡ ዓለም በተቃራኒው ያለው የደቡብ የዓለም ክፍል በከፍተኛ ደረጃ ያለው ዕሴት እየተተካ በምዕራቡ የአኗኗር ዘዴ፣ ባህልን እየተቃኘ ሄዷል፡፡ ይኼ ‹‹ራስን በራስ›› የሚለው ላለው የምዕራብ ተኮር እንቅስቃሴ ተቃውሞ ነው?
ኤልሳቤጥ፡- አዎ የዘይቤያዊ ትርጉሙ ይኼን ነው የሚያመለክተው በተለይም እንሠትን በምንመለከትበት ጊዜ ራሳችንን መመልከት፣ ለራሳችንም ችግሮች መፍትሔ ከራሳችን መሻት መፈለግ አለብን፡፡ የራሳችንን ዕውቀቶች ማጥናትና ማዳበር መቻል አለብን፡፡ የጥበብ ሥራን ለማጊዬጫ መንገድ ብቻ መጠቀም የለብንም ለእኔ የማኅበረሰቡን ጉዳዮች ነቅሰን የምናወጣበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህም በላይ መፍትሔን የምናመለክትበት ነው ምንጊዜም ቢሆን በጥበብ ሥራዎችና በዕደ ጥበብ ውጤቶች ትርጉም መካከል የትኛው ምንድን ነው የሚለው ግራ ያጋባል፡፡ ለእኔ ይኼ የጥበብ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ሉዓላዊነት ትስስር በጠነከረበት ወቅትም መመሳሰል እየበረታና በምዕራባውያን እሴትና ባህል እየተዋጥን እንገኛለን፡፡ ሁሉ ነገር ደረጃ አለው ጥያቄው ግን የትኛው ነው የኢትዮጵያዊ ወይም የእኛ የምንለው? ደረጃውስ የማን ነው?
ሪፖርተር፡- ከተፈጥሮ የመማሪያ መንገዶችን ስናወራ የታዋቂዋ ምሁርና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች አንጀላ ዴቪስ አንድ ጥቅስ አለ፡፡ ‹‹ሁላችንም ከዓለም ጋር ባለን ግንኙነት የራሳችን ርዕዮተ ዓለም አለን የሚል የአንቺ ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ኤልሳቤጥ፡- ተፈጥሮ ያላትን በመቅዳት እንከተል፡፡ በቀጥታ መቅዳት ሳይሆን ተግባሩን መከተል ነው፡፡ ለምሳሌ ሸረሪቶች በአካባቢያቸው ዙሪያ ድር ያደራሉ፡፡ ይኼንን ምሳሌ ብንወስድ በአካባቢያችን ካሉ ነገሮች መፍትሔ መፈለግ አካባቢያችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን እንማራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የሰው ልጆች ከተፈጥሮ በተፃራሪ በመሆን አካባቢውን በመበከል፣ ዛፍን በመቁረጥ፣ ያለውንም በማበላሸት ላይ ተሰማርተናል፡፡ የዚህንም አሉታዊ ተፅዕኖ እያየን ነው፡፡ ስለዚህ የሎተስ ተክል ራሷን ማፅዳትን እንደ ምልክት በውሰድ ተግባሯን መከተል እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- እንሠትና ኮባን ድሮም አሁንም የምንጠቀምባቸው ሲሆኑ ለጥበብ ሥራሽ እንደ ፎቶ፣ አኒሜሽን፣ ቪዲዮ ትጠቀሚያለሽ፡፡ ይኼ በጥበብ ሥራሽ ላይ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል?
ኤልሳቤጥ፡- ቴክኖሎጂ ያስደንቀኛል፡፡ የተለያዩ ምርምሮችንም አደርጋለሁ፡፡ በ1960ዎቹ ገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹አብስትራክት ኤክስፕረሺኒዝም›› የሚባለውን የአሳሳል ስልት ዘይቤ ሲከተል ተቃውሞ ደርሶበት ነበር፡፡ ለዚህም የሰጠው መልስ ‹‹ጊዜያችንን መምሰል አለብን›› የሚል ነበር፡፡ ካለው የቴክኖሎጂ ማዕበል ልናመልጥም ሆነ ልንደበቅም አንችልም፡፡ ለእኔ ቴክኖሎጂን እንደ መሣሪያ ነወ የምጠቀምበት፡፡ የጥበብ ሥራዎቼንም ሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ የምጠቀምበት አንድ መሣሪያ ነው፡፡ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ዲግሪዬን ካጠናቀቅኩ በኋላ ወደ ድሮ ትምህርት ቤቴ ባልቲሞር ሲቲ ኮሚዩኒቲ ኮሌጅ ተመልሼ ለአምስት ዓመታት ያህል አስተምሬያለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ነው የቴክኖሎጂ ዓለምን መፈተሽ እንዲሁም የጥበብ ሥራዬ ውስጥ ማስገባት አስፈላጊነቱ የታየኝ ከዚያ በኋላም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ጠልቆ በመግባት የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን ወስጃለሁ እንዲሁም በዩቲዩብ ቪዲዮዎችን በመመልከት ራሴን በየወቅቱ አስተምራለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በኢንተራክቲቭ መልቲሚዲያ ዘርፍ ለአንድ ዓመት አጥንቻለሁ፡፡ ይኼም በጥበብ ሥራዬም ላይ ሆነ ማስተላለፍ የምፈልገውን መልዕክት በደንብ እንዲሁም አጉልቶ እንዳስተላልፍ አድርጎኛል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዐውደ ርዕይ ላይ በነበረው ቪዲዮ የኮባ ዛፍ ሲገሸለጥ የሚያሳይ ትዕይንት አለ፡፡ ይኼ ትዕይንት ወደኋላ ቀስ ባለመንገድ እንዲሁም በፍጥነት ይመላለሳል፡፡ ይኼንን ማድረግ የተቻለው የተለያዩ የሶትፍዌር ፕሮግራሞችን በመጠቀም ነው፡፡ ይኼ የኮባ ዛፍ ሲቀደድ ወይም ሲገሸለጥ የሚሰማው ድምፅ ይረብሻል፡፡ ይኼ ሕመምን ያሳያል፡፡ አንዳንዶችም ጥቃትን፣ መደፈርም ብለው የተረጎሙትም አልታጡም የቴክኖሎጂው መኖር ማለት የምፈልገውን በተቀናበረ መልኩ እንዳስተላልፍ ረድቶኛል፡፡ የድሮውን፣ የአሁኑንም መሣሪያዎች በማዛመድ መፍጠር የምንፈልገውን የጥበብ ሥራ እንድንፈጥር ያስችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- እስቲ ወደኋላ እንመለስና ወደ ጥበቡ ዓለም እንዴት ገባሽ?
ኤልሳቤጥ፡- የተማርኩት መነን ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዛን ወቅት አስተማሪያችን ከነበሩት አንዱ የኢትዮጵያ ፊደላትን በመጠቀም የጥበብ ሥራውን የሚሠራው ወሰኔ ኮስሮፍ ነው ብዙ የሚያበረታታንና ለወደፊቱም መቀጠል ከፈለግን የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት እንዳለ ያሳወቀን እሱ ነው፡፡ በዛን ወቅት በነበረው የትምህርት ሥርዓት ስምንተኛ ክፍልን መጨረስ ወደ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት የሚያስገባ ነበር፡፡ ስምንተኛ ክፍልንም እንደጨረስኩ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ወደ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት አቀናሁ፡፡ እናም የክረምት ኮርሦቹን ወሰድኩ፡፡ ቤተሰቦቼ ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ማጠናቀቅ እንዳለብኝ አጥብቀው ስለነገሩኝ የክረምት ፕሮግራሙን ነወ የተከታተልኩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቼ በሥዕል ዘርፍ ተመርቄያለሁ፡፡ በጣም የሚታወስና ደስ የሚል ጊዜ ነበር በተለይም አራተኛ ዓመት በነበርኩበት ወቅት ራሺያ የሥነ ጥበብ ትምህርት አጥንተው የተመለሱት እነ ታደሰ መስፍን የመማር ማስተማሩን ሒደት እንዲያንሠራራ ያደረጉበት ወቅት ነው፡፡ በቀን ውስጥ ስልሳ የሚደርሱ ሥዕሎች (ንድፍ) እንድንስል ይጠበቅብን ነበር፡፡ ለሥዕል የሚሆኑ ሞዴሎችንም ለመፈለግ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜያችንን እናሳልፍ ነበር፡፡ በፀጥታ የሚፀልዩ ሰዎችንም እንሥል ነበር፡፡ እነዚህንም ንድፎች የኮላዥ ሥራዬን በምሠራበት ወቅት ተጠቅሜበታለሁ፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መንፈሳችንን ያነቃቃና ደስተኛ ቦታችን ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ከተመረቅን በኋላም ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ ብዙ ጊዜያችንን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነበር የምናሳልፈው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሴት አርቲስቶችበሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ወቅታቸው በሴትነታቸው ጫና ይደርስባቸው እንደበር ይናገራሉ፡፡ የአንቺ መልስ ለዚህ ምንድነው?
ኤልሳቤጥ፡- ከሌላው ተለይቼ የታየሁበትን ሁኔታ አላስታውስም ጠንክረን እንድንሠራ ብዙ ያበረታቱን ነበር ምናልባት አንዳንድ ጊዜ የመስመር አጫጫራችንን የወንድ ይመስላል የሚሉ አስተያየቶች ይኖራሉ፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም ነገር ግን እንዲህ ከበድ ያለ ነገር አላጋጠመኝም በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታዬ ብዙ የማስታውሰውን ቀልዱን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዛን ጊዜ ለመሥራት የሚያነሳሳሽ ሐሳብ ምን ነበር?
ኤልሳቤጥ፡- ለእኔ ለመሥራት የሚያነሳሳኝ አካባቢዬ፣ ማኅበረሰቡ በውስጡ ያለው ባህልና የአኗኗር ዘዬ ነው፡፡ በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መመረቂያዬ የሠራሁት በጉራጌ አካባቢ ለመስቀል በዓል ላይ የሚደረገው ጭፈራ ላይ ነው፡፡ በአካባቢዬ የነበሩ አርቲስቶች አፄ ቴዎድሮስ ላይ እንዲሁም ሰፋ ባለው የአገሪቱ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሥራዎችንም የሚሠሩ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ የእኔ የጥበብ ሥራዎች ማዕከል ያደረጉት ሰውንና ሕዝብን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሜሪካ ቆይታሽ ወቅት ታሪካዊ ከሆነው የጥቁር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአንዱ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትሽን ተከታትለሻል፡፡ ይኼ ልምድሽ በተለይም ከዘር አረዳድ ጋር በተገናኘ ምን ይመስላል?
ኤልሳቤጥ፡- መጀመሪያ አሜሪካ በሄድኩበት ወቅት የገባሁበት ትምህርት ቤት ባልቲሞር ሲቲ ኮሙዩኒቲ ኮሌጅ ነበር፡፡ እህቶቼም በወቅቱ ባልቲሞር ነበር የሚኖሩት ምን ብዬ እንደምጠራው አላቅም ድንጋጤ ይሁን እኔንጃ አሜሪካ ከደረስኩ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሥዕል መሥራት አልቻልኩም ነበር፡፡ በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታችን ወቅት ብዙ የመልክዐ ምድር ገፅታ የሚያሳዩ ሥራዎችን እንሠራ ነበር እሱ ሁሉ ነው የጠፋብኝ፡፡ በባልቲሞር ቆይታዬም ግራፊፊክስ አርት ለማጥናት ነበር የገባሁት፡፡ ምክንያቱም የሥነ ጥበብ (ፋይን አርት) ለማጥናት በጣም ውድ ስለሆነ ተቀራራቢ የሆነ ትምህርት መምረጥ ነበረብኝ፡፡ አሜሪካም ውስጥ ቢሆን በገንዘብ አቅም ያላቸው ናቸው የሥነ ጥበብ ትምህርት የሚማሩት፡፡ የጥበብ መሥሪያ ቁሳቁሶችንም መግዛት ቀላል አይደለም፡፡ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ትምህርቴን ለመቀጠል ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀልኩ፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬም ከካልፎርኒያ የመጣች ፕሮፌሰር በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት በነበርኩበት ወቅት ይሠሩ የነበሩትን የአሳሳል ዘዬዎች የምትከተል ነበረች፡፡ ከእሷም በግሌ ኮርስ ወሰድኩኝ፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ተቋርጦ የነበረውን የጥበብ ሥራዬንም በአዲስ መንፈስ ቀጠልኩ፡፡ ይኼ ዩኒቨርሲቲ የነጮች ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የዘመናዊ ጥበብ ታሪክ መጻሕፍት ላይ አንድም ጥቁር አርቲስት የለም፡፡ ከአንድ የመንፈቅ ዓመት የትምህርት ቆይታዬ በኋላ ፈለቀ አርምዴ የሚባል ታዋቂ ሰዓሊ የድረ ምረቃ ትምህርቴን ሀዋርድ ማጥናት እንደምችል ነገረኝ፡፡ የሱን ምክር በመስማትም ነው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀልኩት፡፡ ታዋቂውና ፈር ቀዳጁ ሠዓሊ ስኩንድር ቦጐስያን መንገዱን በሀዋርድ ስለከፈተልን ዩኒቨርሲቲው በደንብ ነው የተቀበለን፡፡ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ስኩንድር ታላቅ ስም የነበረውና የሚወደድ አርቲስትም ነው፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ሌላ ዓለም ነው፡፡ ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ብሔድም በሚያሳፍር መልኩ ስለ አፍሪካ የአሳሳል ሥልትም ሆነ ጥበብ ምንም አላውቅም ነበር፡፡ በተቃራኒው ስለ ፒካሶ ብዙ እናውቃለን፡፡ ለዓመታት በምዕራባውያን ዘዬ የተማርነውን የዘመናዊ ጥበብ ማፍረስና አፍሪካዊ በሆነ ቃና የምንማርበት መንገድ ነበር፡፡ የእኛ ጥናትም ከሀርለም ሬናይሰንስ፣ እንዲሁም በጥቁር አሜሪካውያን ይደረግ የነበረውን የነፃነት የትግል ታሪክ እንዲሁም አስተዋጽኦ ያደረጉ እንደሆነ ማርከስ ጋርቬይ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ያማከለ ነበር፡፡ እነዚህ ኮርሶች እንደነ ደብልዩ ኢ ቢ ዱቦይ እንዲሁም አሌይን ሊሮይ ሎክ የመሳሰሉ ታላቅ አሳቢዎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎልናል፡፡ ዓይን ገላጭ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ስለታዋቂው አርቲስት ሄንሪ ማቲስ ብዙ እናውቃለን ግን በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ወቅት ነው ከኢትዮጵያ የባህላዊ ጥበብ ብዙ እንደወሰደ የተረዳሁት በተለይም አማካሪዬ የነበረው ፕሮፌሰር አል ስሚዝ የተለያዩ መጽሐፎችን እንዳነብ እንዲሁም የተለያዩ ጽንሠ ሐሳቦችን እንዳውቅ ረድቶኛል፡፡ የምዕራቡ ዓለም የአፍሪካን ጥበብ ወይም የአሳሳል ዘዴ ለማንቋሸሽ ኋላቀር ይሉታል፡፡ ነገር ግን እነሱ ስለማይረዱት ነው እንጂ በአፍሪካ የአሳሳል ዘዬ ጭንቅላት ትልቅ የሚሆነው መንፈስ ምን ያህል ከአካል እንደሚበልጥ ለማስረዳት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በማንነታችን ታሪካችን በዕውቀታችን እንድንኮራ አድርጎናል፡፡ አሁንም ቢሆን ግራ የሚያጋባኝ ለምን የራሳችንን ዕውቀት ለልጆቻችን እንደማናስተምር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ያገኘሽው ምላሽ በተለይም የአፍሪካን ጥበብ ከፍ የማድረግ ሁኔታ ምን ያህል ቀይሮሻል?
ኤልሳቤጥ፡- ምንም እንኳን በአሜሪካውያን የሥራ ባህል ብደነቅም አሜሪካ የተለየ ቦታ ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ የሸማችና የተጠቃሚነት ባህል የሰፈነበት ነው፡፡ ለእኔ ሳድግ ዋናውና ጠቃሚው ነገር ከዕቃ በላይ የተማርኩት ሰብዓዊነትን ወይም ሰውን ማስቀደምን ነው፡፡ ምንም እንኳን ያለው ባህል ሌላ ቢሆንም ያደግኩበት ባህል አልተናወፀም፡፡ በዛ ወቅት የነበሩትም ሥራዎቼም የሸማችነትን እንዲሁም የተጠቃሚነት ባህል የሚተቹ ነበሩ፡፡ አፍሪካዊ አሜሪካዊው ሮማሬ ቢርደን የኮላዥ ሥራዬ ላይ ብዙ መነቃቃትን ፈጥሮልኛል፡፡ በዚህም ኮላዥ ሥራዬ አዲስ አበባ እያለሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሳልኳቸውን ንድፎች ተጠቅሜባቸዋለሁ፡፡ በዚያንም ወቅት የሠራኋቸውን ሥራዎች ‹‹ዘ ፎርጋትን ሶውልስ›› በሚል ርዕስ ስሚዝሶኒያን ናሽናል ሙዝየም ኦፍ አፍሪካን አርት አሳይቻቸዋለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ሎንሊ ማዞር›› (ብቸኛዋ እናት) በሚል እናቴ አሜሪካ በምትኖርበት ወቅት የደረሰባትን መነቀል የሚያሳይ ሥራ ነው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ90ዎቹ እናቴ አሜሪካ ከእኛ ጋር በምትኖርበት ወቅት የቋንቋ ችግር እንዳለ ሆኖ በአንድ አፓርትመንት ውስጥ ተዘግታ ነበር የምትውለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በብዛት ኢትዮጵያውያን ስለሚኖሩ ለየት ያለ ሁኔታ ነው በዛን ጊዜ ግን እሥር ቤት ማለት ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ካለ ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስርና ግንኙነት ቦታ መጥቶ አንድ ቤት መቆለፍ ለጤናም ጥሩ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አገርሽ ከተመለስሽ በኋላ በአገሪቷ የጥበብ ትዕይንት ያለሽ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ኤልሳቤጥ፡- እዚህ ከተመለስኩ በኋላ አሜሪካ በሚገኘው ፓሪሽ ጋለሪ ሥራዎቼን አሳይቻለሁ፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዐውደ ርዕይም በአስኒ ጋለሪ በ1999 ዓ.ም. አሳይቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ዐውደ ርዕዮችም ነበሩኝ፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚያስደስተኝ አንዱ ለአፍሪካ ኅብረት ወይም በቀድሞ መጠሪያው ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት 50ኛ ምሥረታ በዓል ከአራት ዓመት በፊት ያቀረብኩት ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ በሀዋርድ ቆይታዬ ወቅት አንድ የምትጣደፍ ሴት ንድፍ ነው፡፡ ይህ መጣደፍ ወደፊት የመሄድን ዕድገትን የሚወክል ነው፡፡ ይህች የንድፍ ሥራ በአፍሪካ ኅብረት በነበረው የመስታወት የጥበብ ሥራ ላይ እንዲሁም በቅርቡ በነበረው አኒሜሽን ላይ እንደ ዋና ግብዓት ተጠቅሜባታለሁ፡፡ በተለይም በአኒሜሽን ሥራው ይህቺ ንድፍ ብዙ ሆና ትመጣለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በደሳለኝ ሆቴል የሞዛይክ ሥራ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመተባበር ሠርተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ድምጿ›› በሚል ርዕስ ስለሠራሽው ዘጋቢ ፊልም ንገሪኝ እስቲ፡፡ ብዙ ሴት አርቲስቶች ከተመረቁ በኋላ ያገቡና በጥበብ ሥራቸውም አይቀጥሉበትም ይኼንን ዘጋቢ ፊልም መሥራቱ ምን ያህል ጠቃሚ ነበር?
ኤልሳቤጥ፡- ፊልሙ ራሳቸው ሴት ሠዓሊዎቹ ታሪካቸውን የሚናገሩበት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ያስተማሩና ትምህርት ቤት ስላልገቡ ብዙ ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ያሉ እንዲሁም በተጓዳኝ የጥበብ ሥራቸው የሚሠሩ አሉ፡፡ እንዴት ነው ጊዜያቸውን የሚያመቻቹት የሚገጥማቸውንስ ፈተና እንዴት ነው የሚወጡት የሚለውን ፊልሙ ይመልሳል፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም ከሠራኋቸው ሥራዎች አንዱና ጠቃሚ ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለወደፊቱ ምን ለመሥራት አስበሻል?
ኤልሳቤጥ፡- አሁንም ለወደፊትም ምርምሬን መቀጠል፣ መማር እንዲሁም የጥበብ ሥራዎቼን መሥራት ነው፡፡ ‹‹ድምጿ›› በሚለው ፊልም ሰባት ሴት አርቲስቶችን አስገብቼያለሁ፡፡ በቅርቡ የሦስት አርቲስቶችን ታሪክ ጨምሬበታለሁ፡፡ ይኼንኑ ፊልም በመቀጠል ወንድ አርቲስቶችን በተለይም ከሴት አርቲስቶች የተጋቡና የግንኙነታቸውን ሁኔታ ለማየት እሞክራለሁ፡፡