ፍቅር ባላባቱን ሎሌ የሚያደርግ ታላቅ ሀይል እንዳለው ይነገርለታል᎓᎓ የተለያዩ ፀሀፍቶች ብዙ ብለውለታል᎓᎓ ይህ ታላቅ ሀይል ያለውን የፍቅር ስሜት ድምፃውያኑ ሞዝቀውለታል᎓᎓ ይሁን እንጂ ምንም ቢነገርለትም ከስሜቱ ጥልቀት የተነሳ ተነግሮለት የማያልቅ፣ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የሚያስተናግድ እንደሆነ ቀጥሏል። ለአብነትም ፍቅርን በአየር የሚመስሉ ዘፈኖች በብዛት እንሰማለን᎓᎓
«አንተን ማጣት ማለት ልክ አየር በሌለበት ዓለም ውስጥ እንደመኖር ነው»፣ «ስተነፍስ ብቻ ነው የምናፍቅሽ»፣ «የምታስፈልጊኝ ልቤ ሲመታ ብቻ ነው» ተብሎለታል። አስቡት እስኪ ሁሉም የማይቻል ነገር ነው᎓᎓ ነገር ግን በፍቅር ሁሉም ይቻላል᎓᎓ ደግሞም ለአፍቃሪ ሁሉም ነገር ትክክል ነው᎓᎓ እንዴት ከግማሽ አካላችን ውጪ መኖር ይቻለናል? የዘፈኖቹ ሀሳብ እንደምንተነፍሰው አየር ሁሉ ካፈቀሩት ለሰከንድ እንኳን ተለይቶ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ያመላክታል᎓᎓ ትንታኔ ያበዛሁት አይገባችሁም በማለት ሳይሆን የግጥሙ ጥልቀት ዕውነትም የፍቅርን ምንነት ይገልፃል ብዬ ስላሰብኩ መሆኑን ተረዱልኝ።
በቃ በፍቅር ውስጥ ሲኖሩ ዓለምን የገዙ ያህል እንዲሰማዎት ያደርጋል᎓᎓ በተለይ ካፈቀሩት ጋር አንድ ላይ ከሆኑማ በቃ…! ይህ ታላቅ ስሜት አንዱ ለሌላው የመኖር ትልቅ ጥበብንም ያስተምረናል። ራሳችንንም ለመስዋእትነት በሚያስቀርብ ሁኔታዎች ውስጥ ሊያስገባን እንደሚያስችል እንረዳለን᎓᎓ ታዲያ በፍቅር ውስጥ ራስን ለሌላው አሳልፎ የመስጠት ነገርን ሳስብ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬ ካነበበው ያካፈለኝ ፅሁፍ ትዝ አለኝ᎓᎓
ታሪኩ በቻይናውያን ባለትዳሮች ላይ ያተኩራል᎓᎓ ወጣቶቹ በፍቅር ክንፍ ብለው ወደ ትዳር ይገባሉ᎓᎓ ነገር ግን ከጋብቻቸው ጥቂት ጊዜ በኋላ ባል ባልታወቀና ባልታሰበ ሁኔታ ሙሉ አካሉ የመንቀሳቀስ ችግር አጋጥሞት አልጋ ላይ ይውላል᎓᎓ ታዲያ የእንቅስቃሴ ችግር ብቻ እንዳይመስላችሁ ያጋጠመው በአጠቃላይ አምስቱም የስሜት ህዋሳቱ ስራቸውን አቁመው ነበር᎓᎓ በዚህም ምንም እንኳን ባይሰማትም ሚስቱ በእያንዳንዱ ዕለት እንደምታፈቅረው ትገልፅለት ነበር᎓᎓ እንደሳመችው ባይታወቀውም ትስመው ነበር᎓᎓ ምላሹን ባይሰጣትም ለፍቅር አጋሯ ማድረግ የሚጠበቅባትን ሁሉ ታደርግ ነበር᎓᎓ በእንደዚህ ሁኔታ 30 ዓመታትን አሳለፈች᎓᎓ የቤት ውስጥ ስራም በእርሷ ጫንቃ ላይ ነበር የወደቀው᎓᎓ ሁሉም ሰው ሆነ የህክምና ባለሙያዎች ተስፋ አስቆራጭ ሀሳቦችን ሰጥተዋታል᎓᎓ ነገር ግን ከ30 ዓመታት በኋላ እንደተለመደው አብልታው አጠጥታው ፍቅሯን ሰጥታው ወደ እርሻ ማሳዋ ትሄዳለች᎓᎓ በዛን ዕለት ያልጠበቀችው ተዓምር ይከሰታል᎓᎓ ይህን ሁሉ ዓመት የጠበቀችው ባሏ ከአልጋው ተነስቶ (My Red peony) እያለ እየጠራት ወደ እርሷ አመራ᎓᎓ በፈጣሪ!… በሷ ቦታ ሆኜ አሰብኩት᎓᎓ ሊሰማት የሚችለውን ስሜት ሳስበው እኔ ራሴ ደነዘዝኩ᎓᎓
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመልሳችሁ። በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት «ፍቅር አለ? የለም?» ብለው ፍቅርን በዘመን ለሚከፋፍሉ ምላሽ ይሆን ዘንድ ሊስትቨርስ የተሰኘው ድረ–ገፅ አስገራሚ እውነተኛ የፍቅር ታሪክ ብሎ ከለቀቃቸው መሀል አንዱን ላካፍላችሁ᎓᎓
ምናልባት ብዙዎቻችሁ እ.አ.አ በ2004 የወጣውን «ዘ ኖት ቡክ » የተሰኘውን የአሜሪካውያኑ ድራማ ዘውግ ያለው የፍቅር ፊልም አይታችሁታል ብዬ ልገምት። ታዲያ በዚህ ፊልም ላይ አንድ በፍቅር እንጂ የኢኮኖሚ አቅሙ እጅግም ያልጎለበተ አፍቃሪ በገንዘብ አቅሟ ከፍ ካለ ቤተሰብ የተገኘች ወጣት ጋር ፍቅር ይይዘዋል። ታሪኩን ላሳጥረውና በትዳር ቆይታቸውም ሚስት ትውስታዋን ታጣለች። በዚህም ከትውስታዋ ጋር አብራ የረሳችውን ባለቤቱን ትውስታ ለመመለስ ባል የሚያደርገውን ፈታኝ ጉዞ ያሳያል።
ከወደ እንግሊዝ ስንጓዝ ይህንን የፊልም ታሪክ ጃክ እና ፊሊስ ፖተር እውነተኛ አድርገውት እናገኘዋለን።ጃክ ሚስቱን ትውስታዋን በማጣቷ ብቻ ሊተዋት አልፈቀደም። ይልቁንም ከልጅነቱ ጀምሮ የዕለት ተዕለት ውሎውን መዝግቦ የመያዝ ልምድ ስለነበረው ይህም ከባለቤቱ ጋር በነበረው ቆይታም በመቀጠሉ ለባለቤቱ ትውስታ መመለስ መፍትሄን ሊያመጣለት እንደሚችል አመነ።
ጃክ እ.አ.አ ጥቅምት አራት 1941 ፊሊስን ሲያገኛት የነበረውን እና የተሰማውን ፍቅር ዛሬ ላይ እንደሆነ አድርጎ ከትቦት ነበር። ጃክ በፊሊስ ፍቅር የተንበረከከው ልክ እርሷን ካገኘበት ቅፅበት ይጀምራል። ማስታወሻውም እንዲህ ይላል «በጣም ጥሩ ምሽት ነበር። በጣም ከተለየች ሴት ጋር ስደንስም ነበር። ደግሜ እንደማገኛት ተስፋ አለኝ» ይህ ከሆነ ከ16 ወራት በኋላም ዳግመኛ ከመገናኘት ባለፈ በትዳር ይተሳሰራሉ። ኑሯቸውንም ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚሆን ጊዜ በእንግሊዝ ያደርጋሉ።
ቀስ በቀስም የፊሊስ ትውስታ ማጣት የነበራትን ማህበራዊ ህይወት እና አጠቃላይ ደስታዋን ይነጥቃታል። ባለቤቷ ጃክም ለብቻው ይህንን መቋቋም ያቅተዋል። በዚህ ዙሪያ ወደሚሰሩ የእንክብካቤ ተቋም ፊሊስን ማስገባትም ግድ ይሆንበታል። በየቀኑ መጎብኘቱን አስተጓጉሎ አያው ቅም ነበር ። ከማስታወሻው ላይም ያነብላታል። ስለመሰረቱት ቤተሰብና ስለ ቤት እንስሶቻቸው ሳይቀር በፎቶግራፍ እያስደገፈ ያወራታል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ እንኳን ፊሊስ ጃክን ምን ያህል ታፈቅረው እንደነበርና ለእርሱ ያላትን ጥልቅ ስሜት ይረዳላት ነበር ። ሁልጊዜም ቢሆን ጃክ ሊያያት በሚመጣበት ወቅት ከልክ ያለፈ ደስታን ታሳየው ነበር።