‹‹መፅሐፍ እያነበብክ ጊዜህን ማሳለፍ ትመርጣለህ ወይንስ ከሰዎች ጋር መዝናናት?›› የሚል ጥያቄ እንደ ሰውየው ምርጫ የሚወሰን ከመሰለቻችሁ ተሳስታችኋል፡፡
“መፅሐፍን እመርጣለሁ›› ብሎ በፍጥነት የሚመልሰው አስመሳይ ነው፡፡ አላዋቂ አስመሳይ። ተንኮል አስቦ ላይሆን ይችላል ወገኛ መልስ የሚሰጠው፡፡ ሁሉ ሰው ይኼን መሰል ጥያቄ ሲቀርብለት፣ በማህበረሰቡ “ማንበብ” ተቀባይነት አለው ብሎ ስለሚያስብ፣ መፅሐፍ አንባቢነትን ይመርጣል፡፡ ሁለቴ ሳያስብ፡፡
“ከሰዎች ጋር በመሆን ጊዜዬን ማሳለፍ እመርጣለሁ” የሚለውም የዘፈቀደ ምላሽ፣ ሁለቴ ሳያስቡ የሚሰጥ ነው፡፡ በመሰረቱ ጥያቄው ራሱ አሳሳች ነው፡፡ በሁለቱም አንፃር ቢመለስ ያልተሟላ ወይንም ለጥያቄው መልስ የሚሰጠውን ሰው የሚያስወነጅል የጥያቄ አይነት አለና፡፡
“ዘንድሮስ መዋሸት አቁመሀል?” ለሚል ጥያቄ የ“አዎ” ወይንም “አይደለም” መልስ ጠያቂው ለመስጠት ከፈቀደ፣ መላሹ ራሱን ከመወንጀል አይተርፍም፡፡ ዘንድሮስ መዋሸት አቁመሃል? ሲባል “አዎ” ካለ፤ ከዘንድሮ ቀደም ሲል ይዋሽ እንደነበር ማመኑ ነው፡፡ “አይ”ም ካለ በውሸታምነቱ መቀጠሉን ነው የሚናገረው፡፡ በመሰረቱ ስህተቱ ያለው በጥያቄው ላይ ነው፡፡ በጥያቄው ላይ እና በመልስ አማራጭ ውስንነቱ ላይ፡፡
“መፅሐፍ እያነበብክ ጊዜህን ማሳለፍ ትመርጣለህ ወይንስ ከሰዎች ጋር ሆነህ በመዝናናት” ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልሱ “Depends on the book – depends on the people” የሚል መሆን አለበት፡፡
መፅሐፍት በማንበብ ጊዜዬን ማሳለፍን እንድመርጥ በቅድሚያ “ምን አይነት መፅሐፍ” የሚለው ጥያቄ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ከሰዎች ጋር ጊዜዬን ማሳለፍንም ለመምረጥ “ምን ዓይነት ሰዎች” ጋር? የሚለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በስመ ሰው እና በስመ መፅሐፍ የመላሹ ምርጫን ማወቅ ጠያቂውም አይችልም፤ … መላሹም የሚያቀርበው ፍላጎቱ ግልፅ ካልሆነ መረጃ የመነጨ ስለሆነ እውነተኛ አይሆንም፡፡
መጀመሪያ ቅድመ ሁኔታዎቹ መገለፅ ይኖርባቸዋል፡፡ …. ለምሳሌ የባስ ሾፌር ወይንም ትኬት ቆራጭ “መፅሐፍ ማንበብን እመርጣለሁ” ካሉ “በምን ጊዜ” የሚል ጥያቄንም አብረው መግለፅ አለባቸው፡፡ “በትርፍ ጊዜዬ” የሚል ልዩ የጊዜ ሁኔታን ከዕለት ተለት ስራው በተነጠለ መልኩ የሚነፃፀርበትን ሁኔታ መጠቆም ይገደዳል፡፡
“ትርፍ ጊዜ ሳገኝ መፅሐፍ ባነብ እመርጣለሁ” ማለታቸው ነው፡፡ ምክኒያቱም፤ አብዛኛው ጊዜያቸው በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የዋለ በመሆኑ ነው፡፡ ምርጫ ሁሉ ምኞት ወይንም ህልም ሳይሆን ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚናበብ፣ ካልሆነ እንደ ፅኑ መረጃ መውሰድ አይቻልም፡፡
የባሱ ሾፌር “ከሰዎች ጋር ጊዜዬን ማሳለፍ ነው ምርጫዬ” ብሎ ቢመልስም እኮ ትክክል መልስ ሰጠ ሊባል አይችልም፡፡ ሰዎችን ሲያመላልስ ነው የሚውለው፤ ምርጫው ግዴታውም ነው። … ሰዎችን ማመላለስ ከሰዎች ጋር ጊዜን ማሳለፍ ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ “ምን አይነት መፅሐፍ?” የሚለው ጥያቄ መፅሐፍ ማንበብ ለሚመርጠው እስካልቀረበለት ምርጫው ድፍን እንደሚሆነው ሁሉ … “ከሰዎች ጋር መዋል ነው ፍላጎቴ” ለሚለው ደግሞ “ምን አይነት ሰዎች?” የሚለው እስካልተጠየቀ ምርጫው ትርጉም ያለው መረጃ ስለመራጩ ፍላጎት አይነግረንም፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች ግልፅ ከሆኑም በኋላ ሌላ ‹‹Necessary conditions›› የግድ መግባት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ‹‹Consciousness›› ነው፡፡ ራስን በራስ የማወቅ ተፈጥሮአችን ልለው እችላለሁኝ፡፡
…አሁን እያሰብኩኝ ነው… የማስበውን ሀሳብ ምን ያህሉን አውቀዋለሁኝ… በእይታዬ ክልል የሚገባውን ትዕይንት ስንቱን ቦታ ሰጥቼ ልብ እለዋሁ… የተመለከትኩትን፣ ያሰብኩትን… የተገነዘብኩትን… በአስፈለገኝ ጊዜ መልሼ ማስታወስ እችላለሁኝ…
እነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች ከመስተሐልይ (Consciousness) ጋር የሚሄዱ ናቸው፡፡ ‹‹መፅሐፍ ማንበብ ከሰዎች ይሻለኛል›› ብሎ የመረጠው ሰው፤ መፅሐፍ ማንበብ ምን ማለት እንደሆነና…ማንበብ ምን እና ምንን የሚያሟላ የመስተሐልይ ሂደት እንደሆነ ካላወቀ የመረጠው ምርጫ ባለማወቅም ይሁን በማወቅ ጎዶሎ ሆኗል፡፡
ለምሳሌ…መንፈሱን ሰብስቦ በጸጥታ ሙሉ መፅሐፍን ለማንበብ ትዕግስት ይሁን ጥሞናን ያላደበረ ሰው፤ መፅሐፍን ለማንበብ ሊመርጥም ሆነ ሊመኝ አይችልም፡፡ ምኞት፤ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያነቃቃ ስሜታዊ ፍላጎት ነው፡፡ አልያም ቅዥት ነው፡፡
መፅሐፍን ለማንበብ ፊደልን መቁጠር ግድ እንደሆነው፣ ፀጥታና ጥሞና ደግሞ የተነበቡትን ፊደሎች ወደ መስተሐልይ ለማስገባት ቁልፍ ናቸው። ከሰዎች ጋር በመሆን ጊዜውን ማሳለፍ የሚፈልግ ሰው፤ ከሰዎች ጋር መግባቢያውን ቋንቋ ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚያሳልፋቸውን ሰዎች ስነልቦና እና ባህላዊ ስነምግባርም (Etiquette) ጠንቅቆ ማወቅና መተግበርም መቻል ይኖርበታል፡፡
መፅሐፍም ለመነበብ ይችል ዘንድ መግባቢያ ቋንቋ አለው… የንባብ ስነልቦና እና ስነምግባርም ወይንም ሲጠቃለል ‹‹የንባብ ባህል›› ሳያዳብሩ ለማንበብ መሞክር ጭንቅ ውስጥ መውደቅ ነው። ጭንቁ ከመፅሐፍ ምርጫ ስህተት ሳይሆን የራስን አቅም ምርጫውን ከሚጠይው አስገዳጅ ትዕግስት ጋር ማጣጣም ማቃት ነው ችግሩ፡፡ ምርጫው ጠንቅቆ የሚያውቅ ካለ ከመፅሐፎች ጋር ለመግባባት የሚያስፈልገውን ትዕግስት በሂደት ሊፈጥረው ይችላል፡፡ ግን ስለፈጠረው ዝም ብሎ ይቆያል ማለት አይደለም፡፡ ሁሌ እንደ ጡንቻ ወይንም እንደ ጅማት ልምምድ እየተደረገ ካልዳበረ፣ ካልነበረበት ወደመሆን እንደመጣው ሁሉ… ከመሆን ደግሞ ወደ መሟሸሽና መጥፋት ይሄዳል፡፡
የኮንግኒቲቭ ሳይኮሎጂ አጥኚዎች መስተሐልይን (Consiousness) ከጥሞና (Attention/Awareness ) ጋር አንድ ያደርጉታል፡፡ በመንፈሳዊ ምህዋር የሚመላለሱ ሀሳባዊያን ‹‹ነፍስ› (Soul) የሚባል የማይቆረጥ፣ የማይቀነስ ከስጋ ባህርይ የተለየ አንዳች ልክ (Unite) እንዳለ እንደሚያምኑት ሁሉ… የኮንግኒቲቭ ሳይኮሎጂ አፈ-ቀላጤዎች ደግሞ አንጎልና የነርቭ መዋቅርን እንደ ነፍስ ያዩታል፡፡
በመሆኑም፤ በነርቭ እና በነፍስ መዋቅር የተሰራ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የመስተሐልይ የህልውና መአከል አድርገው ያጠኑታል፡፡ ነፍስን ሀጢአት ወይንም ፅድቅ በቀጥታ ተፈጥሮዋን ከፍና ዝቅ የማድረግ ሚና ይጫወታል… እንዲሉ መንፈሳዊያኑ..የኮግኒቲቭ ሳይኮሎጄ አራማጆቹ ደግሞ ‹‹Attention እና Awareness›› ያጣ መስተሐልይ፣ ሲኦል እንደገባ ነብስ አድርገው ያነፃፅሩታል፡፡
ስለዚህ፤ ማስተዋል የማይችል ቢመለከትም ዋጋ የለውም፡፡ ለማስተዋል ደግሞ ጥሞና የግድ ነው። ለምሳሌ፤ ጥሞና የማድረግ ቀውስ (Attention deficit disorder) ተጠቂ የሆነ ሰው፤ መፅሐፍን ማንበብ ቢመርጥም ሆነ ቢጥር ልፋቱ ከንቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥሞና ያጣበትን ምክኒያት መጀመሪያ ከመመለስ ነው መነሳት ያለበት፡፡ የጠፋው ጥሞና ትክክለኛ መንስኤ ተገኝቶ ፈውስ ካገኘ በኋላ “ስለ ንባብ ምርጫው” ሊጠይቅ ይችላል፡፡
“መፅሐፍ ማንበብ ይሻልሀል ወይንስ ከሰዎች ጋር በመሆን መዝናናት?” ለሚለው የመነሻ ጥያቄያችን፡፡ ‘It depends upon the book’ ወይም `It depends on the people` ብዬ ነበር፡፡፡
ግን በመፅሐፉ አይነት ብቻ ሳይሆን … የመፅሐፉ አይነትን ለማንበብ ከሚፈልገው የጥሞና አይነትም ጋር የተያያዘ እንደሆነ የግድ መቀበል እንገደዳለን። መፅሐፉ የሚፈልገው የጥሞና አይነት ደግሞ መፅሐፉን በሚያነበው ሰው ውስጥ ያለው የትዕግስት፣ የአስተውሎት አቅምና አንባቢው የሚገኝበት አካባቢ የሚለግሰው የፀጥታ ድባብ ይወሰናል፡፡
አካባቢው ለአንባቢው (physical space) የሚለግሰው የድምፅ ቅነሳን ብቻ አይደለም። የኢኮኖሚም ይሁን የፖለቲካ ሰላም ወይንም በአጠቃላይ አዎንታዊ ተስፋ መፅሐፉ የሚፈልገውን የጥሞና አቅም (Attention/awareness) በትብብር ይፈቅዱለታል፡፡ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ሰላም ሳይኖር ጥሞና የሚፈልግ መፅሐፍን ለማንበብ መምረጥም… በማወቅም ይሁን ባለማወቅ… ወይንም በዘልማድ ወገኝነት በተደጋጋሚ እየተሰራ ያለ ስህተት ነው፡፡
“የማይረባ ወሬ በማውራት ከሰዎች ጋር ከማሳለፍ ጥልቅ የሆነ የረባ መፅሐፍን ማንበብ እመርጣለሁኝ” ሊል ይችላል፤ ስነሳ የጠየቅሁን ጥያቄ እንዲመልስ የተጠየቀው ሰው፡፡ ይቀጥልናም፡- “ግን ጥልቅ የሆነ መፅሐፍን ለማንበብ ጥልቅ የሆነ ጥሞና መጀመሪያ ማደራጀት አለብኝ፡፡ ያደራጀሁትን ጥልቅ ጥሞና የሚደግፍ ውጫዊ ሀገር ካልሰጠኝ ግን በቀዳዳ በርሜል ውሃ እንደመሙላት ነው፡፡ መፅሐፍን የማንበብ ፍላጎቴም እንደ ምኞቴ ስኬታማ አይሆንም፡፡”
ይህ ከላይ በትምህርተ ጥቅስ ያስቀመጥኩት እስካሁን ስፅፍ የመጣሁዋቸውን ሀሳቦች የሚያጠቃልል ምላሽ ነው፡፡ ምላሹ መጀመሪያ ስነሳ ለጠየቅሁት ጥያቄ መሆኑ ያልገባው ካለ፣ ይሄንን መጣጥፍ በተበታተነ ጥሞና በማንበቡ ምክኒያት መሆኑን ይወቀው፡፡