ለሞቱ ሰዎች ዳግም ህይወት መዝራት እንደሚያስችል የታመነት ምርምር የመጀመሪያ ሙከራ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለታል።
በአሜሪካ ፊላደልፊያ ተቀማጭነቱን ያደረገው ኩባንያ ባዮኩዋርክ በ2016 መጀመሪያ የአዕምሮ ሞት የማይቀለበስ ነገር እንዳልሆነ መግለጹ ይታወሳል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ኢራ ፓስተር በግንደ ህዋስ ወይም ስቲም ሴል የህክምና ዘዴ (የሰውን ልጅ ከበሽታ ለመፈወስ በራሱ ህዋስ የማከም ዘዴ) በላቲን አሜሪካ በቅርቡ ሙከራ ይደረግበታል።
ሞትን ለማስቀረት ያስችላል የተባለው ሙከራ በየትኛው ሀገር እንደማይካሄድ ስራ አስኪያጁ ባይጠቅሱም በቅርቡ አጠቃላይ የሙከራውን ሂደት የተመለከተ ዝርዝር መረጃ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ሞተ የሚባለው የልብ ምቱ ሲቆም፣ መንቀሳቀስ ሲያቆም እና መተንፈስ ሳይችል ሲቀር ነበር።
አሁን ግን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ልብ ስራዋን ብታቆምም በሰውነታችን ውስጥ ኦክስጅን እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የአዕምሮ ግንደ ህዋሳት ስራቸውን ማስቀጠል ይቻላል።
በዚህም ምክንያት አሜሪካ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ሞትን ከአዕምሮ ግንደ ህዋሳት ስራ ማቆም ጋር ያቆራኙታል።
የባዮኩዋርክ ስራ አስኪያጅ ኢራ ፓስተር በመርፌ የሚሰጡና ስራ ያቆመ አዕምሮን የሚያስነሱ መድሃኒቶችን መፍጠራቸውንና በሰው ልጅ ላይ በዚህ አመት እንደሚሞከሩ ተናግረዋል።
ሙከራውን ከሰው ልጅ በፊት በእንሰሳት ላይ የማድረግ እቅድ እንደሌላቸውም ነው የገለጹት።
ፓስተር እና አጋራቸው ሂማንሹ ባንሳል የመጀመሪያውን ሙከራ ባለፈው አመት በህንድ ለማድረግ ነበር ያቀዱት።
ይሁን እንጂ ሞትን ከንቱ የማድረግ እቅዳቸው ሙከራ በህንድ የህክምና ምርምር ተቋም ምክር ቤት ውድቅ በመደረጉ ሳይሳካ ቀርታል።
የምርምር ቡድኑ በአደጋ ምክንያት አዕምሯቸው ስራ ማቆሙ በኤም አር አይ የተረጋገጠ እድሜያቸው ከ15 እስከ 65 የሚሆኑ ህመምተኞች ላይ ነው “የአዕምሮ ሞትን” መመለስ ይቻላል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ለማድረግ ያሰቡት።
ተመራማሪዎቹ የሙከራ ተግባራቸውን በሶስት ክፍሎች ለመከፋፈል ማቀዳቸውንም ገልፀዋል።
በመጀመሪያው ክፍል ከታካሚዎች ደም በመውሰድ የግንደ ህዋስ (ስቲም ሴል) ያባዛሉ፤ ከዚያም የተራባውን ግንደ ህዋስ ወደ ታካሚዎቹ ሰውነት ያስገባሉ።
በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ታካሚዎቹ የአንድ ወይም ሁለት አሚኖ አሲድ ውህድ የሆነ (ፔፕታይድ) በአከርካሪ አጥንታቸው በኩል ይሰጣቸዋል።
በመጨረሻም ለ15 ቀናት የሞተ አዕምሮን ወደቀደመ ስራው ለመመለስ የአዕምሮ ነርቮችን የማነቃቃት ተግባር (በሌዘር እና ሚዲያክን የነርቭ ማነቃቂያ ስልቶች) ይከናወናል። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚታዩ ለውጦች በኤም አር አይ ስካን ይመዘገባሉ።
የባዮኩዋርክ ሙከራ ሪአኒማ የተሰኘው ሰፊ ፕሮጀክት አካል ሲሆን፥ ኢራ ፓስተር የሪአኒማ የቦርድ አማካሪ ናቸው።
ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk