በአፍሪካ ደረጃ የዲሞክራሲ ሂደትን ለማበረታታት የተቋቋመው የኢብራሂም የሽልማት ፕሮግራም (የሞህ ኢብራሂም ፋውንዴሽን አካል) በቅርቡ እንዳስታወቀው፤ የመድብለ ፓርቲ ባህል በሃገሩ ለማስጀመር ወይም ለማስቀጠል የቆረጠ የአፍሪካ መሪ በመታጣቱ በያዝነው ዓመት ያዘጋጀውን የሽልማት ገንዘብወደ ካዝናው መልሶታል፡፡ የሽልማቱ መጠን አጓጊ ሲሆን በአስር ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ አምስት ሚሊየን ዶላር ገንዘብና እድሜ ልክ በየአመቱ የሚከፈል ሁለት መቶ ሺህ ዶላር የጡረታ አበል ያካትታል፡፡ እንደ ድርጅቱድረ ገጽዘገባ፤ ለሽልማቱ ለመወዳደር እጩ የሚሆኑ የአፍሪካ መሪዎች በምርጫ ወደ ስልጣን የወጡ፣ በህገ መንግስታቸው የተደነገገውን የምርጫ ግዜ አጠናቀውከስልጣን በሰላም የወረዱ እንዲሁም በስልጣን ዘመናቸው ምሳሌ የሚሆን ተግባር የፈጸሙ መሆን ይገባቸዋል። ድርጅቱ ከተቋቋመ 2006 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ብቁ ተሸላሚዎች ሲታጡ ለተደጋጋሚ ግዜ መሆኑንም ገልጿል፡፡
እንደሚታወቀው እንደ አፍሪካ አህጉር የሶሻሊዝምን ቀብር ፈጽመን በመድበለ ፓርቲ ስርዓት አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ከደረስን ሩብ ክፍለ ዘመን ተቆጥሮአል፡፡ ከጥቂት በይፋ የአንድ ፓርቲ /ግለሰብ አገዛዝን ካወጁ ሃገራት በቀር ስምምነቱ የሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ነበረ፡፡ በህገ መንግስታቸው በማካተት ጭምር፡፡ ነገር ግን ከዛ ሁሉ መሃላና ግዝት በኋላ ከሃምሳ አራቱ የአፍሪካ ሃገራት መካከል በመድበለ ፓርቲ ሂደት ውስጥ ለማለፍ የቆረጠ ቢያንስ አንድ መሪ መታጣቱ ጉዳዩን አስደንጋጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቀሙት፤ ከኤሽያ፣ ምስራቅ አውሮፓና አፍሪካ ሃገራት በዴሞክራሲ ግንባታ የአፍሪካን ያህል ቀሚሴ አደናቀፈኝ የሚበዛበት አህጉር የለም፡፡ የገዥዎቻቸውን እድሜ ለማጽናት በቆረጡ ደጋፊዎች እንደሚነገረው፤ መሪዎቻቸው የየሃገራቱን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የተፈጠሩብቸኛ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ተተኪ እንደማይገኝላቸው ይሰበካል፣ ትንታኔም ይሰጣል፡፡ በዚህ የሂሳብ ስሌት በሚራመዱ ደጋፊዎችና ገዥዎች ትስስር ምክንያት መሪዎቹ በስልጣን ለመቆየት ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እስከ ማድረግ ይደርሳሉ፡፡ መጠየቅ ካለብን ጥያቄው መሆን ያለበት፣ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን የሙጥኝ ባይነት ምንጩ ምንድን ነው የሚል ይሆናል፡፡ እውንየሃጉሪቱ መሪዎችና ቁልፍ ሰዎቻቸው እንደሚናገሩት፤ እነሱ ከሌሉ የየሃገራቱ ውስብስብ ችግሮች ይባባሳሉን? የየሃገራቱስ ህልውና ያከትማልን? ምናልባት ቦታ መልቀቅ እንዳለባቸው እራሳቸው መሪዎቹ አያውቁት ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።
የብዙ አምባገነን መንግስታት ደጋፊዎች እውነት የሚመስሉ ከላይ የገለጽናቸው አይነት መግለጫዎችን የሚሰጡት በገዥዎቻቸው ፍትሃዊ አመራር ተማርከው አይደለም፡፡ ይልቁኑ ገዥዎቹ በእቅድ በሚመሩት የ“ከፋፍለህ ግዛ” አገዛዝ ተጠቃሚ በመሆናቸው እንጂ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከሆነ አምባገነን መንግስታት ስልጣናቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም እንዲመቻቸው ከህብረተሰቡ ውስጥ በተሻለ ሊረዳቸው የሚችል ቡድንን በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው መስክ ከሚጠብቀውና ከሚገባው በላይ ተጠቃሚ ያደርጉታል፡፡ በቡድኑ አጋርነትም የስለላና አፈና ተቋሞቻቸውን ያደራጃሉ፡፡ ይህ ጥቅመኛ ቡድን በማናቸውም ሌላ ፍትሃዊ የመንግስት አደረጃጀት ሊያገኝ የማይችለውን ጥቅም የሚያገኝ በመሆኑ መሪዎቹን በስልጣን ለማቆየት በእጁ የገባውን ዘዴ ሁሉ ይጠቀማል፡፡ መሪዎቹ ከስልጣን ዞር ካሉ ሃገራቱ እንደሚጠፉ ይሰብካል፡፡ ሌሎች ለመሪነት የሚመጥኑ ሰዎችና ፓርቲዎች እንዳልተፈጠሩም ያውጃል፡፡ በሌላ አነጋገር አገዛዙን ለማጽናት ተግቶ ይሰራል፡፡ ለሶስተኛ ግዜ በምርጫ ለመወዳደር ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እስከ ማድረግ እንዲሁም ከህገ መንግስታቸው በተቃራኒ የቻይና መሰል ስርዓት እንከተላለን ድርሰት እስከ መድረስ የደረሱ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች መበራከት የዚሁ የጥቅም ፖለቲካ ውጤት ተደርጎ መወሰዱ እውነታው የገዘፈ ነው፡፡
የአፍሪካን ፖለቲካሳስብ ከሚያስገርሙኝ ጉዳዮች መካከል የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማጥላላት በመሪዎቹና በጥቅመኛ ደጋፊዎቻቸው የሚሰራጨው ስብከት ነው፡፡ በቀላል አማርኛ ስናስቀምጠው፤ “መንግስት ለኛ ከኛ በላይ ያውቃል፤ አይሳሳትምም” አይነት ይዘት አለው፡፡ ይህ የጥቅመኞቹ ስብከት በመጨረሻ ከተራው ህዝብ አልፎ እራሳቸው መሪዎቹን እስከማሳሳት ይደርሳል። ይህም ለአምባገነናዊ መንግስታት መሰንበት ጥቅመኛ ደጋፊዎች የሚጫወቱትን ሚና ያሳያል፡፡ የዚምቧቡዌው ዛኑፒኤፍ ፓርቲ ወጣት ክንፍ “የ92 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ የእድሜ ልክ ፕሬዝደንት ይሁኑልን” ማለቱ ለዚህ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ልብ አድርጉ እጅግ ውስብስብ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ተቋም/ሀገር የአዕምሮና የአካል ንቃቱ በተዳከመ አዛውንት እጅ እንዲወድቅ ሲሰበክ፡፡
በሌላ በኩል ምክንያታዊ ለመሆን የሚሞክሩ የተወሰኑ የአፍሪካ መንግስታት ለአምባገነናዊ አገዛዛቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት “በቅድሚያ ልማት” የሚለውን ሃሳብነው፡፡ ይህ አባባል በአንዳንድ ምሁራን ዘንድም ድጋፍ ሲቸረው ይታያል ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን የኢኮኖሚ እድገት በቅድሚያ መረጋገጥ አለበት በሚል፡፡ የሚገርመው እነዚህ አምባገነን መንግስታት በቅድሚያ መሰረተ ልማትና ድህነት ላይ መረባረብ አለብን ባዮች ቢሆኑም ይህንን ሊደግፍ የሚችል የተጠያቂነት ስርዓትን ግን አምርረው ይጠላሉ፡፡ ምክንያቱም የከፋፍለህ ግዛ ፕሮግራማቸውን ፉርሽ ያደርግባቸዋልና፡፡ ነጻ ፍርድ ቤቶች፣ ያለ ተጽዕኖ የተደራጁ ሲቪክ ማህበራትና ነጻ ፕሬስ በነዚህ መሪዎች አይፈለጉም፡፡ ወይም እንዲዳከሙ የሃገር ሀብት ይባክናል፡፡
አፍሪካ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ተስፋ ይኖራት ይሆን? ከኢኮኖሚ ውድቀትና ከወታደራዊ አገዛዝወደ ዲሞክራሲ የተሸጋገሩ ደሃ ሃገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን የኢኮኖሚ እድገትቅድመ ሁኔታ አለመሆኑን ነው፡፡በሌላ በኩል የትምህርት መስፋፋት፣ የመገናኛው መስክ እየረቀቀ መሄድ፣ የባህሎች መወራረስና የከተሞች መስፋፋት የህዝቦችን ምክንያታዊነት እያዳበረው እንደሚሄድ የዴሞክራቲክ ሃገራት ጉዞ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መወለድና ዘላቂነት ከኢኮኖሚ እድገት ይልቅ የሰው ሃብት ልማትና ለዲሞክራሲ ባህል ቅርብ መሆን የተሻለና ፈጣን ሚና እንዳለው ያሳየናል፡፡