በተለመደው የቀን ውሎዎ ውስጥ የሚያደርጓቸው ለውጦች በራስዎ ላይ ደስታን የማምጣት አቅም አላቸው።
አዳዲስ ቀናት በመጡ ቁጥር ነባር እና የቆዩ ታሪኮችን ከማየት ህይዎትዎ ላይ አዲስ ነገሮችን መጨመሩም መልካም ነው።
እነዚህ የሚጨምሯቸው ነገሮች ታዲያ ህይዎትዎ ላይ ደስታን የሚያመጡና የሚጨምሩም ይሆናሉ።
ዋጋ የማይከፍሉባቸው ግን በመከወንዎ ብቻ ደስታን የሚያገኙባቸው መንገዶችን ደግሞ እነሆ፤
በቂ እንቅልፍ ማግኘት፦ በአግባቡ መተኛትዎ ቀኑን ከድካምና ድብርት ተላቀው በተሻለ ጥንካሬና በደስታ እንዲያሳልፉ ያግዝዎታል።
ከዚህ ባለፈም በቀን ውሎዎ ንቁ እንዲሆኑና ለመላው ጤንነትዎም ይጠቅማል፤ እናም ከሰባት እስከ 9 ሰዓታትን በ24 ሰዓት ውስጥ በእንቅልፍ ማሳለፍን አይዘንጉ።
ማለዳ ከወትሮው ቀደም ብሎ መነሳት፦ ዘወትር ከሚነሱበት ጊዜ ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ቀደም ብለው መነሳት መልመድም ለእርስዎ የደስታ ምንጭ ይሆናል።
ይህን ሲያደርጉ ቀንዎን የሚያሳልፉባቸውን መንገዶች የተሻለ ጊዜ በመውሰድ ለማሰብና ለመዘጋጀት በማስቻል ጫናን ይቀንሳል።
ተመስጦ፦ የቀን ውሎዎን ከመጀመርዎ በፊት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ተመስጦ ቢያደርጉ ሙሉ ቀኑን በትኩረት እንዲያሳልፉና ብሩህ ቀን ይኖርዎት ዘንድ ያስችላል።
ሲመሰጡ አዕምሮዎን ንጹህ ማድረግ ይችላሉ፤ ከዚህ ባለፈም ቀና እና መልካም እንዲያስቡም ያደርጋል።
ከተለመደው የእለት ተዕለት ውሎዎ ተላቀውም አሁናዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩና የተሻለ እንዲከውኑም ያስችልዎታል።
ጭንቀትና ውጥረትን ማስወገድና በተቃራኒው ደስታን ማላበስም የተመስጦ ሌላው ጠቀሜታ ነውና ይጠቀሙበት።
አላስፈላጊ ነገሮችን ማስወገድ፦ አንዳንድ ጊዜ ቤት ውስጥም ይሁን በስራ ቦታ ያሉ እቃዎች በሙሉ አስፈላጊ እንደሆኑ በማሰብ አካባቢን በእቃ ማጨናነቅ የተለመደ ነው።
እውነታው ግን መኖሪያ ቤትም ሆነ ቢሮ በእቃ ታጭቆ ሲተፋፈግ፥ አዕምሮን እና መንፈስን የማወክ አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ክፍሉ በእቃ ብዛት ሲታጨቅ ማየት በራሱ የመንፈስ መረበሽንም ያስከትላል፤ ጥቂት ጊዜን በመውሰድ የሚገለገሉባቸውን ብቻ በታቀደ መልኩ ማስቀመጥና ሌሎችን ማስወገድ።
ይህ ሲሆን ክፍሉም ቀለል ያለ እይታ ይኖረዋል መንፈስዎም ይታደሳል ቀለል ባለ እይታ ደግሞ ደስ የሚል ስሜትን መፍጠርም ይችላሉ።
አዳዲስ ነገሮችን ማወቅ፦ አዲስ ነገር ባወቁና በተማሩ ቁጥር የደስታዎ ስሜት እንደሚጨምር እሙን ነው።
ነገሮችን አውቀው ለማሻሻል በሰሩ ቁጥርም የአዕምሮን ንቃተ ህሊና በመጨመር በሚያዩት አዲስ ነገር የደስታዎ ስሜት ይጨምራል።
ባወቁ ቁጥር የእውቀት ባለቤት በመሆን የራስ መተማመን ስሜትዎንም ያሳድጋሉ።
የእግር ጉዞ ማድረግ፦ በቀን ውስጥ 30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ የነርቭ ስርዓትን ለማሻሻል እንደሚረዳ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።
ይህን ሲያደርጉ ደግሞ የተሻለ ብርታት ያገኛሉ ሰውነትዎን በማነቃቃትም ደስታን ይጎናጸፋሉ።
በጎ ተግባር መፈጸም፦ ለሰዎች መልካምና በጎ ነገር ማድረግ ለጤና ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው ይነገራል።
በሰጡ ቁጥር የአዕምሮወ ሰላም ይበዛል፥ ቢያንስ ያደረጉለት ሰው የሚያተርፈውን ማሰብ በራሱ የደስታ ስሜት ይፈጥራል።
እናም በቻሉት አቅም በቀን ውሎዎ ውስጥ መልካም ተግባራትን በመፈጸም ደስታዎን ማብዛት ይችላሉ።
በእድሜ የገፉ አረጋውያንን ማገዝ፣ ታክሲ ላይ ከእርስዎ የበለጠ ለሚያስፈልጋቸውና ለአቅመ ደካሞች ቅድሚያ መስጠት እና መሰል ተግባራት ብዙ የማይጠይቁ ግን የበዛ ሃሴትን ያጎናጽፉዎታልና ይከውኗቸው።
ከደስተኛ ሰዎች ጋር ማሳለፍ፦ ቀና አሳቢና ደስተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ መቻልም ሌላው የደስታ ምንጭ ነው።
ይህን ሲያደርጉ በእነርሱ ስሜት የመዋጥና እርስዎም በእነርሱ ስሜት ይገኙ ዘንድ የውስጥ ተነሳሽነትን ይፈጥራል።
ቢያንስ የተጋሩት ስሜት የደስታ ምንጭዎ የመሆን አቅምም አለው።
አሉባልተኛ አይሁኑ፦ አሉባልታ መውደድና ባልተጨበጠ ነገር መመራት ለህይዎት የማይበጅና አላስፈላጊ ልማድ ነው።
በአሉባልታ በተመሩ ቁጥር ከእውነታው እየራቁ በይሆናል በመመራት ራስዎን ለጭንቀት ይዳርጋሉ።
አሉባልታ ጥሩ የሚሉትን ወዳጅና ጓደኛም ያሳጣልና ከዚህ ራቅ ብለው ስለሰዎች መልካም ብቻ ማሰብን ይልመዱ።
በተገለሉ ቁጥር ደግሞ የበዛ ጭንቀት ብሎም ደስታ የራቀው ህይዎትን ይጋፈጣሉና ከዚያ ይራቁ።
ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ጊዜዎን ማሳለፍ፦ ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ጊዜዎን ማሳለፍ፥ ይህ ባይሆን እንኳን በኢሜልና መሰል አጋጣሚዎች መልዕክት በመለዋወጥ ያለዎትን ግንኙነት ማጎልበት።
ይህ ሲሆን ለእርስዎ የደስታ ምንጭ ይሆናል ለጤናም ይበጃል ይላሉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች።
የእኔ ከሚሉት ወይም ከባለቤትዎ አልያም ከቤተሰብዎ ጋር ስላሰለፏቸው የደስታ ጊዜያት ማሰብ በራሱ ትልቅ የደስታ ምንጭ ይሆንዎታል።
ከቻሉም በሳምንት ውስጥ ከእነርሱ ጋር ብቻ የሚያሳልፉባቸውን ጊዜያት ፕሮግራም በማውጣት መተግበር።
በተጨማሪም ማስታወሻ መጻፍና ያንኑ ከቻሉ በሳምንት ለሶስት ቀናት መከወን ለአዕምሮ ሰላምን የመስጠት አቅም አለው።
በዚህ መልኩ የሚያሰፍሯቸውና ራስዎን የሚገልጹባቸውም ሆነ ሌሎች ማስታወሻዎች በራስ የመተማመን አቅምን ማዳበርና አዕምሮን የማጎልበት አቅምም አለው።
ከዚህ ባለፈም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጥዶ መዋልና በብዛት መጠቀም ለአዕምሮ ጤና መልካም አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚያ ይልቅ ለሩብ ሰዓት ያክል መረጃዎችን ማየትና ቀለል ያሉና አዕምሮን የሚያዝናኑ ጨዋታዎችን በመጫዎት ማሳለፍን ይመክራሉ።
ራስን መንከባከብና ለራስ ጊዜ መስጠትም ሌላው የደስታ ምንጭ እንደሚሆን ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ይህን ሲያደርጉ ጭንቀትና ፍርሃትን ማስወገድና በተቃራኒው በጎ ነገሮችን እንዲያስቡ ያግዝዎታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለእርስዎ የደስታ ምንጭ የሚሆኑ ተግባራትን በየቀኑ መከወንም ሌላው አማራጭ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት የስነ ልቦና ባለሙያዎች ለራስ ደስታ ለማምጣትና ደስተኝነትን ለመላበስ ይረዳሉ ያሏቸው ሃሳቦች ናቸውና ይጠቀሙባቸው።
ምንጭ፦ psychologytoday.com