የማህበራዊ ትስስር ገጽ የሆነው የትዊተር ኩባንያ 636 ሺህ 248 የትዊተር አድራሻዎች መዝጋቱን አስታወቀ።
ኩባንያው ከፈረንጆቹ 2015 አጋማሽ ጀምሮ ነው ይህን እርምጃ የወሰደው።አድራሻዎቹን ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል መዝጋቱንም ኩባንያው ገልጿል።
እርምጃው ኩባንያው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የማደርገው እንቅስቃሴየ አካል ነው ብሏል።ከዚህ ውስጥ 376 ሺህ 890 የሚሆኑት በ2016 የመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት የተዘጉ መሆናቸውንም ነው የገለጸው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉና የሚያስተዋውቁ የግለሰብ አድራሻዎችን፥ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲከታተሉና እርምጃ እንዲወስዱ ሃገራት እየወተወቱ ይገኛል።ይህ የመንግስታት ውትወታም በሰባት በመቶ መጨመሩን ነው የኩባንያው መግለጫ የሚያሳየው።
የተለያዩ ሃገራት ከሽብር ጋር ተያያዥነት ያላቸውና ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ መረጃዎች ከማህበራዊ ትስስር ገጾች ማስወገድ የሚቻልበት አሰራር እንዲሰፍን ይፈልጋሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚጠረጥሯቸው ግለሰቦች አድራሻዎች እንዲፈተሹና እርምጃ እንዲወሰድም ነው የሚጠይቁት።ከዚህ ባለፈም በጋዜጠኞች እና በሚዲያ ተቋማት የሚለጠፉና የሽብር ጥቃትን የሚያሳዩ መረጃዎችን እንዲያነሱም ይጠየቃሉ።
በዚህ በኩል ታዋቂ የሆኑ ጋዜጠኞች የሚለጥፏቸውን የሽብር ጥቃት ውጤቶች፥ እባክህ አጥፋለን የሚል ጥያቄን በተደጋጋሚ ማስተናገዱን ኩባንያው ይገልጻል።
ይህን መሰሉ ህጋዊ የአጥፋልን ጥያቄ፥ ውስጣዊ ደህንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ መረጋጋትን ለማስፈን በሚል እንደሚቀርብለትም ያነሳል።እንደ ኩባንያው ገለጻ ከዚህ ጋር በተያያዘ 88 ጥያቄዎች ቀርበውለታል።
ይሁን እንጅ አብዛኛዎቹን ከማጥፋት ይልቅ ባሉበት እንዲቆዩ አድርጌያለሁ ነው ያለው መቀመጫውን ሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው ኩባንያ።ለምሳሌ በቱርክ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ተከትሎ የተፈጸመን የሽብር ጥቃት የሚያሳዩና አሰቃቂ ሊባሉ የሚችሉ ምስሎችን አለማጥፋቱን አንስቷል።
በሚወራው ልክ ከአሰራር አንጻር ግልጽነትን ለማስፈን የሚመጡ ጥቆማ እና ጥያቄዎችን እንደ ሁኔታው እንደሚስተናገዱም ነው ኩባንያው የገለጸው።አሁን አሁን የማህበራዊ ትስስር ገጾች የጥላቻ እና የዘረኝነት ጽሁፎችን በማባዛት እና በማጋራት በመንግስታት ዘንድ ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።ይህን ተከትሎም ኩባንያዎቹ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ መጀመራቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።