ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አምራች ኩባንያ አፕል አዳዲስ ምርቶቹን እያስተዋወቀ ነው።
ኩባንያው ከሰሞኑ ረከስ ባለ ዋጋ የአይፓድ ምርቱን ያስተዋወቀ ሲሆን፥ ከተለመደው ቀለም በተለየ መልኩም የአይ ፎን ስልኩን ለገበያ ሊያቀርብ ነው ተብሏል።
አፕል በቀይ ቀለም አይፎን 7 እና አይፎን 7 ፕላስን ያስተዋወቀ ሲሆን፥ በሳምንቱ መጨረሻም ለገበያ ይቀርባሉ።
ኩባንያው በሚያደርጋቸው አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ስራዎች ገቢ ማስገኛ ከሆኑት የኩባንያው ምርቶች አንዱ የሆነው ቀዩ አይፎን፥ 699 ዩሮ ዋጋም ተቆርጦለታል።
አዲሱ አይፎን ከፍ ያለ የመያዝ አቅም ያለውና ዘመናዊ መሆኑም ተነግሯል።
በኩባንያው በመጭው አርብ ለገበያ የሚቀርበው ሌላው ምርት ደግሞ ርካሹ አይፓድ ይሆናል።
አይፓዱ 9 ነጥብ 7 ኢንች የስክሪን ስፋት ሲኖረው ቀለል ያለና ምቹ ሆኖ መሰራቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።አዲሱ አይፓድ ስክሪኑ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን፥ ተጠቃሚው በአይፓዱ መስኮት የተለያዩ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ማየትና መጠቀም ይችላል።
ከዚህ ባለፈም ተገልጋዩ በስክሪኑ ላይ የከፈታቸውን ምስሎችና መረጃዎች በፈለገው መጠን ማራቅና ማቅረብ እንዲችል ተደርጎም ነው የተሰራው።
ይህ ደግሞ አይፓዱን ተመራጭና ለተገልጋዮችም ምቹ ያድርገዋል ነው የተባለው።አዲሱን አይፓድ የግሌ ማድረግ እፈልጋለሁ ያለ ደግሞ 339 ዩሮን መክፈል ይጠበቅበታል።
ይህ ዋጋ ኩባንያው እስከዛሬ ካቀረባቸው የአይፓድ ምርቶቹ አንጻር ርካሹ መሆኑም እየተነገረ ነው።
ኩባንያው ክሊፕስ የሚል ስያሜ የሰጠውን መተግበሪያም ከአይፓዱ ጋር አስተዋውቋል።
አዲሱ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አኒሜት በማድረግ በማህበራዊ ትስስር ገጾች መጋራት እንዲችሉ የሚያስችል ነው።አፕል የመጀመሪያውን አይፎን ያስተዋወቀበትን 10ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በአመቱ መጨረሻ አይፎን 8ን እንደሚያስተዋውቅ ይጠበቃል።
አይፎን 8 በስልኩ መጠን ልክ ስክሪኑን መጠቀም የሚያስችል ሲሆን፥ ምንም አይነት በተን የሌለው እንደሚሆንም ይጠበቃል።ከዚህ ባለፈም ስልኩ ያለ ገመድ ሃይል ይሞላል፤ በዘመነ ቴክኖሎጅም ደንበኞቹ ጋር እንደሚደርስ ነው የተነገረው።
ምንጭ፦ telegraph.co.uk