ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ብራንድ ወይም ልዩ ምልክት የሆነው ኢትዮጵያ ዘላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ “ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት” የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ይፋ ሆነ፡፡
የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
ምክር ቤቱ በባለፈው ጉባኤው ሃገሪቱ በቱሪዝም የምትተዋወቅበት ልዩ ምልክት “ኢትዮዽያ ዘ ላንድ ኦፍ ኦሪጂን” አፀድቆ የነበረ ሲሆን በዚህኛው ጉባኤውም ትርጓሜውን “ኢትዮዽያ ምድረ ቀደምት”የአማርኛው የቱሪዝም ልዩ ምልክት ሁኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ፀድቋል᎓᎓
የትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ቢሆንም አገሪቱ ካላት ሰፊ የቱሪዝም ሃብት አነፃር ሲታይ አሁንም ተግባሩ አናሳ መሆኑን ገልፀዋል᎓᎓
የቱሪስት መስተንግዶ ተቋማት በተለይም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ከአለም ቱሪዝም ድርጅት በመጡ ባለሙያዎች የስልጠናና ደረጃ አገልግሎቱን እንዳሻሻለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደ ማሪያም ተናግረዋል᎓᎓
ነባርና አዲስ የመዳረሻ ልማት ስራዎች በቱሪዝም የተከናወኑ ተግባራት የ6 ወር የስራ ሪፖርትም ቀርቧል᎓᎓
የምክር ቤቱ አባላትም የቱሪዝም ሃብቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በአለም ዙሪያ መተዋወቅ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል᎓᎓
ምክር ቤቱ በአገሪቱ የመጀመሪያውን አስጎብኝ ድርጅት በማቋቋም እንዲሁም ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት ስትተዋወቅበት የነበረው የ13 ወር ፀጋ የሚለውን በመፍጠራቸው የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት በመባል ለሚታወቁት ለአቶ ሃብተስላሴ ታፈሰ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰርተፊኬት፣ የኒሻንና የብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል᎓᎓
ሪፖርተር ፡‑ ስብኃት ግርማ