እናቴን እየጠላኋት ነው…
ለራሴም ገርሞኛል… በዚህ ፍጥነት እዚህ ውሳኔ ላይ እደርሳለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር… ግን ሆነ… የምወደውን ሰው ዕድሜ ልክ እንደምወደው በማመን ሞኝነት ውስጥ መክረሜ አልታወቀኝ ኖሯል…
አሁን ይህን የሚያነብ ሰው ‘እምዬን?… እንዴት አስችሎህ?! ምን ዓይነቱ ደንዳና ነህ?’ ከሚል ቁጣ ጋር እንደሚጠይቀኝ አውቃለሁ… አልፈርድበትም… እናቴን ባያውቃት ነው…
ያዝ… የበደለችኝን ልቁጠርልህ…
ልጅ እያለሁ የሰፈራችን ልጅ እንዳልሞት እንዳልሽር አድርጎ ደበደበኝ.. ጥቃቴን ብትመልስ ብዬ ለእናቴ ነገርኳት… ደሜን ስታይ እሪ.. ብላ ጮኸች… ከዚያም የጉልቤው ልጅ ቤተሰብ ዘንድ ሄዳ ያደረገውን አሳየቻቸው… ‘አንቺ ደግሞ.. ልጆች አይደሉ እንዴ.. ነገ ዞረው ይገጥማሉ..’ ብለው አጣጣሉባት… አሁን እንዲህ ዓይነት ጥጋበኛ ቤተሰብ ሲገጥማት ምን ማድረግ ነበረባት?.. መክሰስ ወይ ደግሞ መሳደብ አይደል?… እናቴ ግን አላደረገችውም… ይልቅ ስንመለስ ምን አለችኝ?… ‘ደምስዬ.. እንደገባኝ ጓደኛህ ባደረገው ነገር ተጸጽቷል… ቤተሰቡም በእኛ ፊት ዝም አለው እንጂ ስንወጣ ይቆጡታል… ነገ ትምህርት ቤት ስትገናኙ ሰላምታ ስጠው እሺ… ይቅርታ የሚያደርጉ ተበዳዮች ከበዳይ የተሻለ የመንፈስ ልዕልና እንዳላቸው ልታውቅ ይገባል’ … ዛሬም ድረስ ይህ ቃል እየተደቀነብኝ በበዳዮቼ ፊት እንደተልፈሰፈስኩ አለሁ…
የሆነ ጊዜ 10 ሳንቲም ከጠረጴዛ ላይ አንስቼ ሳምቡሳ ስበላ ደረሰች… እጅና እግሬን ወደ ኋላ ጠፍራ አስራ ቅጥቅጥ አድርጋ ገረፈችኝ… ቆይቼ 25 ሳንቲም ከመደርደሪያ ላይ አነሳሁባት.. በዚህ ጊዜ ይባስ ብላ ከሽቦ አልጋ ጋር አስራ ሰምበር በሰምበር አደረገችኝ… በሁለቱም ጊዜ ‘እኔን እሺ… ይቅርታ አድርግልኝ’ እንደምትለኝ ሙሉ እምነት ነበረኝ… እርሷ እቴ… ‘አድገህ በእንቁላሉ ጊዜ ብትቀጪኝ ልትል አይደል?..’ አለችኝ… በደሏ የገባኝ ከ5 ዓመት በፊት ነው… ‘ወይ አይበላ ወይ አያስበላ’ ብለው እስር ቤት የጣሉኝ ጊዜ… እንኳን ልታሰር ዛሬ ላይ የኔ በምለው ሺህ ምንተሺህ ንብረት በተከበብኩ ነበር እኮ… ይህ ሁሉ የርሷ ጦስ ነው…
ስኳርና ሻይ ቅጠል ግዛ ብላ ትልከኝና ሳመጣላት ሁለቱንም ማንቆርቆሪያ ውስጥ ትሞጅርና ጋዜጣውን ዘርግታ ከመሃል ትመሰጣለች… ምናልባት የጀመረችው ታሪክ ሳያልቅ ከመሃል ጋዜጣው ተቆርጦ እንደሆነ ስትሮጥ ሱቅ ትሄድና ‘ጀማል እባክህን የዚህን ጋዜጣ ቅዳጅ ስጠኝ… ደስ የሚል ታሪክ ጀምሬ…’ ትለዋለች… ለሌላ ካልሰደደው ጉራጁን ይሰጣታል… አንብባ ስትጨርስ ወይ ታለቅሳለች ወይ ደስ ይላታል… ቡና ላይ ለተገኙ ጎረቤቶች ሳይቀር ትተርከዋለች… ይኸው እኔም ዛሬ እርሷ ከቅዳጅ ጋዜጣዎች ስትፈልግ የኖረችውን ነገር ከዳጎሱ መጽሐፍት ባገኘው ብዬ እተጋለሁ… ቤቴ ከመጽሐፍ ውጭ ንብረት የላትም… ኪራይ ቤት በቀየርኩ ቁጥር ሃሞቴ የሚፈሰው ብዛታቸውን ሳስብ ነው… በልጅነት የከተበችኝ ሞኝነት በስተርጅና ሲያንገላታኝ አያችሁልኝ?…
የእናቴ በደል እንዲህ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም… ምድር ሁሉ ብራና ባሕር ሁሉ ቀለም ቢሆን እንኳ መዝለቁ የማይታሰብ ነው…
ህም…. እማማዬ…
ቡታጅራ ነኝ አሁን – ከማሚ ጋር… አብሬያት ስሆን ‘ይህች የገንዘብ ድሃ… የመንፈስ ግን ሃብታም ሴት ምን የረባ ነገር አውርሳኝ ይሆን?’ ብዬ ስጠይቅ እኒህ ለጊዜው በጽሑፍ መጡልኝ… ሌሎቹን ግን በቃላት ልላቸው አልተቻለኝም…
ደሜ – ዝምታዬ የሚጠልቀው ስላንቺ ሳስብ ነው… እወድሻለሁ!!!
“እንዝርት ያለ ቋንጣ – አይሽከረከርም
ቤት ያለ ምሰሶ – አይቆረቆርም
ይዋል ይደር እንጂ – ያሰብነው አይቀርም” … እያልሽ አይደል ያሳደግሽኝ?… አዎን ያሰብነው አይቀርም…
ክብር ለሴትነት – ፍቅር ሁሉ ለእናትነት!!!