ምቹ ተፈጥሮ እያላት ምግብ የሚታደልባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት
· ቦትስዋና 90 በመቶ መሬቷ በረሃማ ነው፤ ግን ራሳቸውን ይቀልባሉ
· ደቡብ አፍሪካ በድርቅ ተጠቂ ብትሆንም የተትረፈረፈ ምርት አምራች ናት
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የምጣኔ ሃብት ምሁር)

ለምንድን ነው ድርቅ የሚያስከትለውን አደጋ መከላከል ያቃተን?
በመጀመሪያ ደረጃ መታየት ያለበት ሀገሪቱ ምን አይነት አቅም አላት የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት አላት ያለው ራሱ የግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ቢበዛ 14 በመቶውን ነው እየተጠቀምን ያለነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፤ ወንዞቻችን በየዓመቱ 122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ ይዘው ከሀገር ይወጣሉ፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ነው የምትባለው፡፡ በአራቱም አቅጣጫ ነው ውሃ ወደ ውጭ የምንልከው፡፡ ከዚህ በመነሳት እኛ በድርቅ ስንቸገር ብዙዎች ግራ እየገባቸው “እነዚህ ሰዎች ምን ሆነው ነው” ይላሉ። በእርግጥም አስገራሚ ነው፤ በድርቁ የሚጠቁት ቆላማ አካባቢዎች ናቸው፡፡ አንዱ የሶማሌ ክልል ነው፡፡ የሶማሌ ክልል ግን በአለም ላይ በሰፊው ሊታረሱ ከሚችሉ ረጅም ለም መሬት ተብለው ከሚታወቁት አንዱ ነው፡፡ ለም መሬቱ ብቻ አይደለም፤ ዋቢ ሸበሌን ጨምሮ በርካታ ወንዞች፣ ለጥ ባለው ለም መሬት ላይ ዝም ብለው ይፈሳሉ፡፡ የሰዎቹ አኗኗር ሁኔታ ሲታይ ደግሞ አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ተግዳሮት የሚሆነው፣ ማንም ሰው የማህበረሰቡን አኗኗር፣ ባህል … በግድ ለመቀየር መብቱ የለውም፡፡
በሌላ በኩል ድርቅ በተፈጠረ ቁጥር ለተረጂነት ይጋለጣሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ኤሊኖ ሲከሰት ከ8 መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥቶ ነው መንግስት እርዳታ ያቀረበው፡፡ ይሄ ገንዘብ ወደ ሌላ ልማት ቢውል ኖሮ ብዙ ስራ ይሰራል፡፡ እርግጥ ነው ከምንም በላይ የሰው ህይወት የማዳን ስራ ይቀድማል፤ ግን በዚህ መንገድ እስከ መቼ ነው የምንቀጥለው የሚለው ነው፤ ዋናው ጥያቄ፡፡
እኛ ከተወለድን ጀምሮ ኢትዮጵያ በድርቅ ስትመታና ስትቸገር ነው የምናየው፡፡ በ1977 ያ ሁሉ ድርቅ በተከሰተበት ጊዜ፣ 8 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ነበር በረሀብ የተጠቃው፡፡ ያኔ እርዳታ በማስተባበሩ ረገድ ትልቁ ተዋናይ ቀይ መስቀል ነበር፡፡ የዓለም ህዝብ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ እርዳታ ነበር የላከው፡፡ ዛሬም እንዲሁ እርዳታ እየጠየቅን ነው፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ መፍትሄ መፈለግ አለበት ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ስለ እንደዚህ አይነት ችግሮች ስንነጋገር፣ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት አቅማችን ምን ይመስላል … የሚለውንም በመገምገም መሆን አለበት፡፡
አንደኛ፤ የሚፈጠሩ አደጋዎች ተተንባይ እንደመሆናቸው፣ ምን ያህል የእርዳታ ክምችት አለን የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ የአደጋ ማስተባበር የምንለው ከዚህ በኋላ የሚከተልና የተከማቸውን እህልና እርዳታ፣ ጤንነቱን ጠብቆ ወደየአካባቢው የማድረስ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ሰዎች ከቀዬአቸው እንዳይሰደዱ፣ በየቦታው የእርዳታ ማቅረቢያ ካምፖች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ እርዳታውን በተገቢው ማድረስ ይቻላል፡፡
አደጋን ማስወገድ ስንል ደግሞ ከእነአካቴው መሰል ችግር እንዳይከሰት የሚሰራ ስራ ነው፡፡ እኛ ገና እዚህ ላይ አልደረስንም ማለት ነው፤ አሁን ከሚታየው ሁኔታ አንፃር፡፡ ለችግር የተዳረጉ ሰዎች በቀጣይ እንዳይደገምባቸው በደህና ጊዜ ሀብትና ጥሪት የሚያፈሩበት ሁኔታ መፍጠር፣ ከገበያ ገዝተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉበትን አቅም መፍጠር ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ እስካሁን የታሰቡ አይመስልም፡፡ ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዴት መሻገር እንችላለን ለሚለው አንዱ፣ እነዚህን ዘላቂ መፍትሄዎች ማሰብ መቻል ነው። ከዚህ በፊት የነበሩት፣ የፖሊሲ ችግሮች ጭምር ናቸው፡፡ “የእነሱን ህይወት የመቀየር ኃላፊነት የለብንም፤ እንዳሉ ከጠበቅናቸው በቂ ነው” የሚል ፖሊሲ ነበር፡፡ አሁን ግን የዚያ አይነት ፖሊሲ የለም። በአግባቡ መተግበርና መስራት ግን ያስፈልጋል፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ ሰፋፊ ሜካናይዝድ የግል እርሻዎች ተጀምረው ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ተዘግቶ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በፖሊሲ ደረጃ እያገገመ ያለ ነው፡፡ ለውጭ ዜጎች መሬት እየተሰጠ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ እርግጥ ወደ ውጪ ነው ኤክስፖርት እየተደረገ ያለው፤ ቢሆንም በገንዘቡ ሌላ ምግብ መግዛት እንችላለን፡፡
አሁንም ቢሆን ያልነካነው ሰፊ መሬት ጥቅም ላይ ሊውል ወደሚችልበት መንገድ መሄድ አለበት። ኢንቨስተሮች መጥተው፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዘልማድ አርብቶ አደርነት ወጥቶ የተሻለ አርብቶና አርሶ አደር የሚሆንበት መንገድ ቢፈጠር የተሻለ ነው፡፡ ውሃና የግጦሽ መሬት እየተከተለ የሚሄድ ሳይሆን አንድ ቦታ ተረጋግቶ፣ ከብቶቹን በጤንነት ተንከባክቦ ቢያረባ የት በደረሰ ነበር፡፡ በአካባቢው በተለይ በበርበራና በሞቃዲሾ በኩል በአመት ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የቁም እንስሳት በኮንትሮባንድ መልክ ከሃገር ይወጣሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ሃብት ያለው ህዝብ ነው፣ አሁን ተራበና ተቸገረ እየተባለ ያለው፡፡ ይሄንን በእቅድ ይዞ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ደግሞ የግል ዘርፉ ነው መስራት ያለበት፡፡ ለምሳሌ የዚምባብዌን ነጭ ገበሬዎች ሙጋቤ ሲያባርራቸው፣ ወደ ሞዛምቢክ ሄደው በዘጠኝ ወር  ነው የሞዛምቢክን የምግብ አቅርቦት በ3 እጥፍ የጨመሩት፡፡
ገበሬ ስንል ዝም ብሎ ልምድ የሌለው፣ አያስፈልግም ማለቴ ነው፡፡ ባንክ ስለሚያበድር ብቻ ሁሉም ገበሬ ነኝ ብሎ መሬት ወስዶ፣ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት ማባከን የለበትም፡፡ ጋምቤላ እየተሠራ ያለውን ስራ እናውቃለን፡፡ ከአፈሩና ከውሃው ጋር የሚጠጣሙ፣ ልምድ ያላቸው፣ ግብርና ከዘር ማንዘራቸው እየተላለፈ የመጣ፣ ስራውን የሚያውቁ ትልልቅ አቅም ያላቸው፣ ገብተው ሊሠሩ ይገባል፡፡ በድርቅ ተጠቅተዋል የተባሉት ቆላማ አካባቢዎች በስጋና በወተት ኢንቨስትመንት፣  ሰፊ አቅም አላቸው፡፡ በዚህ ላይ በትኩረት መሰራት አለመቻሉ፣ ዛሬም ከድርቅ አደጋ እንዳናመልጥ አድርጎናል፡፡ እነሱን ለመርዳት የወጣው 8 መቶ ሚሊዮን ዶላር እና ከውጭ የመጣው እርዳታ ለእንደዚህ አይነቱ ልማት ቢውል፣ እነዚህ ሰዎች ኩሩ ሆነው በኖሩ ነበር፡፡ እርዳታ ሲጠይቅ ማንነቱን አዋርዶ ለማኝ ሆኖ ነው። ለእነዚህ ዜጎች ይሄን አማራጭ ብንተገብርላቸው፣ ከዚህ ሰቀቀን በወጡ ነበር፡፡
እንዴት ነው አቅም መፍጠር የምንችለው?
ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የግል ዘርፉ ሰፊ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡ የግል ባለሀብቱ ደግሞ ካፒታል ያስፈልገዋል፡፡ ካፒታል ደግሞ አሁን ባሉን ባንኮች ተንቀሳቅሶ ሊሰራበት የሚያስችል አይደለም፡፡ በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ ከፈለግን፣ በግሎባላይዜሽን አስተሳሰብ ሁሉም እኩል ካፒታል ይፈልጋል፤ ስለዚህ እነዚህን ማስተናገድ የሚችል የባንክ አቅም ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ በድርቅ የምትጠቃ ብትሆንም የተትረፈረፈ ምርት አምራች ነች፡፡ ሀገሬውን የሚቀልቡት ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ የህዝቡን 3 በመቶ አይሆኑም፤ ሙሉ ደቡብ አፍሪካን የሚቀልቡ ገበሬዎች፡፡ ወተት እንኳ ሳይቀር እንደ ወንዝ ነው የሚያፈሱት፡፡ በቧንቧ መስመር ነው የሚያከፋፍሉት፡፡ እነዚህን ልምድ ያላቸው ገበሬዎች ወደ ሀገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ እናምጣ ብንል፣ ባንኮቻችን አቅም የላቸውም፡፡ ኢንቨስተሮች ወደዚች ሀገር ሲመጡ አንዱ የሚጠይቁት፤ “ምን ባንክ አለ?” የሚለውን ነው፡፡ ለዚህ ምላሽ የሚመጥን የባንክ አቅም አልፈጠርንም፡፡
ለምንድን ነው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች የማይለሙት?
ዋናው ችግራችን እንግዲህ ከታሪካችን ይነሳል። ሌሎች ሀገሮች እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባቡዌ፣ ቦትስዋና፣ ዛምቢያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ … ስንመለከት፣ የኛን ያህል መሬትና የውሃ ሀብት የሌላቸው ናቸው። ግን በቅኝ ግዛት ዘመን የዳበረው ባህል ለዛሬው ጠቅሟቸዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ሰፋፊ እርሻ የነበራቸው ገበሬዎች፣ የልጅ ልጆች ዛሬም ድረስ ግብርናውን ያከናውሉ፡፡ ለምሳሌ የኬንያን የዱር እንስሳት አስተዳደር ስንመለከት፣ ዛሬም በነጮቹ እጅ ነው ያለው፡፡ ኬንያ ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር ከዚህ ዘርፍ ታገኛለች፡፡ እነዚህ ሰዎች ይሄን ቀጥ አድርገው ይዘውላታል ማለት ነው፡፡ ግብፅም ብንሄድ ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች አሁንም ድረስ በእንግሊዞች ኩባንያ ስር ነው ያሉት፡፡ የግብፅ የጥጥ ምርት በአለም ገበያ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡
በኛ ሀገር ይሄ ባህልና ታሪክ የለም፡፡ በጃንሆይ ዘመነ መንግስት ሰፋፊ እርሻ ተጀምሮ ነበር፡፡ የበቆሎ፣ የቦሎቄ፣ የሰሊጥ፣ የጥጥ እርሻ በግለሰቦች ተጀምሮ፣ ጥሩ አቅጣጫ ይዞ እያለ ደርግ መጣና ወረሳቸው፡፡ ደርግም የመንግስት የእርሻ ልማት ብሎ ለመቀጠል ሞከረ፡፡ የደርግን ሰፊ ወታደር ሲቀልቡ የነበሩት እነዚህ የመንግስት እርሻዎች ናቸው፡፡ 17 ዓመት ሙሉ ደርግ ለቀለብ ምንም የውጭ እርዳታ አላገኘም፡፡ በ1977 ነው ለህዝቡ እርዳታ የመጣው እንጂ አብዛኛው ቀለብ የሚሰፈረው ከእነዚህ እርሻዎች ነበር፡፡
አሁን ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ አነስተኛ አምራቾች ላይ ነው ማተኮር ያለብን ተብሎ፣ የድህነት ቅነሳ መርሃ ግብሩ እስከወጣበት እ.ኤ.አ 2006 ድረስ ሰፋፊ እርሻ የሚባል ነገር ክልክል ነበር፡፡ የነበሩትን የደርግ እርሻዎች ወደ ግል ከማዞር በዘለለ፣ አዳዲስ እርሻዎች አልተጀመሩም ነበር፡፡ ቆይቶ ነው 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አለና፣ ኢንቨስተር እንፈልጋለን የተባለው፡፡ ኢንቨስተር ተፈልጎ በሚመጣበት ጊዜ ደግሞ አሁን በቅርቡ እንዳየነው፣ ለእርሻው ብለው ገንዘብ ወስደው ለሌላ ነገር አዋሉ ተብለው፣ ግማሹ ታሰረ ሲባል በየሚዲያው እየሰማን ነበር፡፡ የልማት ባንክም ለእርሻ የሚሰጠውን ብድር ሙሉ ለሙሉ አቁሞ ነበር፡፡ እንደኔ ዋናው የማናጅመንት ጉዳይ ነው፡፡ አሰራሩ ነው መፈተሽ ያለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ የህንድ ኩባንያ 3 መቶ ሺህ ሄክታር ወሰደ ተባለ፡፡ ከዚያ መቶ ሺህ ተባለ፡፡ ቀጥሎ ከመቶ ሺው 2 ሺህ ሄክታሩን ብቻ ነው ያለማው ተባለና እንደዚህ አይነት ውጥንቅጥ፣ በአስተዳደሩ ውስጥ ችግር እንዳለ የሚያመለክት ነው፡፡
አንድ ኦክላንድ ኢንስቲትዩት የሚባል አለ። በየቀኑ ነው መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች መሬት ሰጠ እያለ የሚወቅሰው፤ ግን ከ4 ሚሊዮን ሄክታሩ የተሰጠው 5መቶ ሺም አይሞላም፤ እሱም ምርታማ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ሀገሪቱ ላይ ችግር ሲፈጠር መፍትሄ ለማምጣት ጥረት አይደረግም። ልማታዊ መንግስት ስንል፣ አንዱ ራሱ መንግስት ነው፡፡ መንግስት – ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሀብት ያቀርባል። ሌላው የግል ዘርፍ ነው – ገንዘብ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ይዞ ይመጣል፡፡ ሶስተኛው ባለድርሻ ምሁሩ ነው፡፡ የተሻሉ የምርምር ውጤቶችን ያቀርባል፡፡ እነዚህን ነገሮ ስንመለከት፣ ይሄ እኛ ሀገር አለ ወይ? የሚለውን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። በነገራችን ላይ ይሄ ትልቅ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ልምድ መቅሰም አሊያም ከዚያ ኢንቨስተሮችን መጋበዝ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በግብርና ከተሳካላቸው አንዷ ቦትስዋና ነች፡፡ ቦትስዋና 90 በመቶ መሬቷ በረሃማ ነው፣ ግን ራሳቸውን ይቀልባሉ፡፡ አሁን ምቹ ተፈጥሮ እያላት ምግብ የሚታደልባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡
እንደኔ፣ ልክ የሀገር ዳር ድንበር ተደፈረ ብለን እንደምንነሳው፣ ይሄም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት አለበት፡፡ ከዚህ ችግር እስከ መጨረሻው መውጣት አለብን፡፡ መንግስት የየአካባቢውን ህዝብ ማስተማር አለበት፡፡ ጉድጓድ ሄዶ መቆፈርና እህል ማቅረብ፣ መቼውንም ቢሆን ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ መንግስት ራሱ ልምድ ካላቸው ሀገሮች፣ ኢንቨስተሮችን ማምጣት አለበት፡፡ ሲመጡም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ በሶማሌ ክልል የነበረው የሰላም መደፍረስ ብዙ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ ያ ገፅታ አሁንም አልደበዘዘም፤ ለዚህ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
መንግስት በሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስት ቢያደርግ … መፍትሄ ያመጣል?
የመንግሥት እርሻ ማቋቋም መንግስት ራሱ እንደሚናገረው፣ ካለው የሙስና መንሰራፋትና የመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚቻል አይመስልም፡፡ ስለዚህ ልምድና ስኬት ያስመዘገበ የግል ባለሀብት ገብቶ እንዲሰራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ቦትስዋና፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ ከመሳሰሉ ሀገራት የግል ባለሀብቶችን ማምጣት ሁሉ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰፊ ልምድ አላቸው፡፡ አርሶ አደሮቻችንም ወደዚህ ልምድ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በጃንሆይ ዘመን “ጭላሎ አግሪካልቸራል ዲቨሎፕመንት ዩኒቲ” የሚባል ነበረ፡፡ አርሲና ባሌን የስንዴና የገብስ ሀገር ያደረገ ስራ ነው፡፡ የስዊድን መንግስት 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጎ ያሳደገው እርሻ ነበር፡፡ ይሄ ስኬት ሲያስመዘግብ ደግሞ ወላይታ ላይ እንድገመው ተብሎ፤ “ወላቡ አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ዩኒቲ” ተብሎ ተጀመረ፡፡ ያንን ተሞክሮ እንኳ መልሰን ማምጣት አልቻልንም። ደርግ እንዳወደመው ነው አሁንም ያለው፡፡ ይሄ ልምድ መምጣት አለበት፡፡ መንግስት እንዲህ ዓይነት ስኬታማ አሰራሮች እንዲፈጠሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ እርሻውም እየተስፋፋ፣ ኢኮኖሚውም እያደገ ነው፤ ግን ከህዝብ ቁጥር ጋር አልተስማማም፡፡ ለዚህ የሚሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ የመንግስት ድርሻ ሀገር መጠበቅ፣ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ነው እንጂ ግብርና ውስጥ ይግባ የሚለው አያስኬድም፡፡ ለግል ባለሀብቱ እድሉ ሊመቻች ይገባል፡፡ በከብት ሀብት ከአፍሪካ 1ኛ ነን፤ ግን የደቡብ አፍሪካን ያህል እንኳ አልተጠቀምንበትም፡፡ ምርጥ የከብት ዝርያዎችን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ እርባታዎችን መፍጠር አለብን፡፡ የከብት ሀብት አስተዳደራችን መፈተሽ አለበት፡፡ የከብት ሀብት ቢኖረንም ምርታማ አይደሉም፡፡ ይሄም መታየት አለበት፡፡

———————–

· “ድርቅ በመጣ ቁጥር ጭንቅ ላይ ነን”
· “ለድርቅ አደጋ እርዳታ ጠባቂ የሆንነው በምንከተለው ፖሊሲ ነው”
· “ድርቅ ሲከሰት ድንገት እንደ በጋ ዝናብ ዓይነት አይደለም”
አቶ ሞሼ ሰሙ (ፖለቲከኛና የባንክ ባለሙያ

እስከ መቼ ነው ለድርቅ አደጋ እርዳታ ጠባቂ የምንሆነው?
ለድርቅ አደጋ እርዳታ ጠባቂ የመሆናችን ምክንያት አንደኛው፣ የምንከተለው የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ድርቅና ረሃብ የሚደርስባት ሀገር ነች፡፡ ይሄን ለመፍታት የሚያስችል መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫ መዘርጋትና በዚያ መሰረት ድርቁ ቢከሰት ያለ ምንም ምፅዋት ህዝቡ ከሀገሪቱ ሀብት ይሄን ችግር የሚፈታበት መንገድ፣ በግልፅ በፖሊሲ ማስቀመጥና ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲ በባህሪው አቅጣጫ ጠቋሚና መፍትሄ ሰጪ ነው እንጂ ችግር አመንጪ ሊሆን አይገባም፡፡ አንዳንድ ፖሊሲዎች ችግር አመንጪ ሲሆኑ ይታያሉ። ችግር የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ሳይሆን ከራስ የፖለቲካ ፍላጎት በመነሳት በመቀረፃቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በኮሚኒስት ሀገሮች ላይ የድርቅን ችግር ለመፍታት የተሄደበት መንገድ፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ከመተሳሰሩ ይልቅ ከፖለቲካ ፍልስፍና ይመነጫል፡፡ ያ የፖለቲካ ፍልስፍና ምናልባት በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ሊሰራ ይችላል እንጂ በሁሉም ሀገሮች ላይ ይሰራል ማለት አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ፍልስፍና የሚመነጭ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲቀየስ፣ ሰው በነፃነት ተንቀሳቅሶ እንዲሰራና ለችግሮች መፍትሄ እንዲያመጣ አያደርግም፡፡
ሌላው የፖሊሲ አቅጣጫ፣ ከግለሰቦች ፍላጎት ሊመነጭ ይችላል። ይህ ሲሆን ምናልባት ከህዝቡ፣ ከማህበሰረቡ ባህል፣ አኗኗር ወይም ከችግሮች መፍትሄዎች ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ አሁን የምናየው የሀገራችን የድርቅ ችግር ከእነዚህ አመክንዮዎች አይወጣም፡፡
እንደዚህ አይነት ድርቅ ሲከሰት ድንገት እንደ በጋ ዝናብ ዓይነት አይደለም፡፡ ጠቋሚ ምልክቶች አሉት፡፡ ጊዜ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አስቦ መስራት ይቻላል፡፡ ድርቆች ወደ ከፋ ጉዳትና ረሃብ እንዳይለወጡ የመከላከል እድሉ አለ፡፡ ሌላው እነዚህ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ድርቅ የሚደርስባቸው ከሆነ፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ከወጣው ፖሊሲ ጋር የማይጣጣም ነገር አላቸው ማለት ነው። ስለዚህ እነዚያ አካባቢዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚታወቀው ፖሊሲ ውስጥ ከሚታቀፉ … የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫ ልንቀርፅላቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ ያሉበትን መሬትና አሰፋፈር ያገናዘበ እንደ ማለት ነው፡፡ ምናልባት ከቦታው አንስቶ ወደ ሌላ ማስፈር ሊሆን ይችላል፡፡ ቦታው ለእርሻ ሳይሆን ለከብት እርባታ የሚመች ከሆነ፣ ድርቅ  የሚያጠቃው ወደዚያ እንዲለወጥ ማድረግ፣ ያ መሬት ድርቅ የሚያጠቃው ከሆነ፣ ከግብርና ውጪ የሆነ ስራ እንዲሰራ ማድረግም ሌላው የመፍትሄ አማራጭ ነው፡፡ ይሄ ልዩ የፖሊሲ አቅጣጫ ያስፈልገዋል፡፡ ሌላው እንዲህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ካለ፣ ሁልጊዜ ማህበረሰቡን ለበለጠ ጉዳት ያጋልጡታል፡፡ ትኩረት ሁሉ ወደ ተጎጂዎች ሳይሆን ወደ ፖለቲካ ትኩሳቱ ይሆናል፡፡ በመሀል ዜጎች ይጎዳሉ። መንግስትም ትኩረቱን በሙሉ ወደ ፖለቲካ ትኩሳቱ ስለሚያዞር፣ ተገቢውን ጥንቃቁና እንክብካቤ አያደርግም፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ሳይቀር ልንሰማ የምንገደደው ከውጪ ሀገር ሚዲያዎች ነው፡፡
አሁንም የድርቁን ችግር እየሰማን ያለነው ከውጭ ሚዲያዎች ነው፡፡ ትልቁ ነገር ለጉዳዩ ትኩረት ማጣት ነው፡፡ የፖሊሲ አውጭዎች ከፖለቲካ ፍልስፍና ወይም ከግለሰቦች እውቀት ብቻ ሲመነጩ ወይም አንድ የፖሊሲ አቅጣጫ ለበረሃውም፣ ለቆላውም፣ ለአደጋውም እኩል አቅጣጫ ተደርገው በስራ ላይ እንዲውል ሲደረግ፣ ዛሬ እንደምናየው የዘመናት የድርቅ ችግርን ለመቋቋምና ለመሻገር ይሳነናል፡፡ ፖሊሲዎች ከህብረተሰቡ አኗኗር፣ አሰፋፈር፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ተነስተው ነው መቀረፅ ያለባቸው፡፡
ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና የድርቅ ችግር እንዴት ነው መስተናገድ ያለባቸው?
ማንኛውም ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ችግሩን፣ የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄውን ለመፍታት የሚወሰደው ጊዜና ሰው በድርቅ ሲጠቃ ችግሩን ለመፍታት የሚወሰደው ጊዜ እኩል ሊሆን አይገባም። የፖለቲካው ችግር የሚያደርሰው ምስቅልቅልና ጉዳት በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ነው፡፡ ድርቁ የሰው ህይወትን የማዳን ጉዳይ ነው፡፡ ምግብ አግኝቶ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ለሁለቱ ሊሰጥ የሚገባው ትኩረት ለየቅል ነው። ከ1950 በኋላ አምባገነን መንግስታትም እንኳን ከድርቅና መሰል አደጋዎች ብዙዎቹ ወጥተዋል፡፡ ምናልባት እንደ ሀገር የማይቆጠሩት እንደ ሶማሊያ የመሳሰሉት ካልሆነ በስተቀር መንግስት ያላቸው ሀገሮች ከዚህ ችግር ወጥተዋል፡፡ ድርቅ በቃ ምንም ጉዳት የሌለው የአየር ፀባይ ለውጥ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ እኛ ግን ድርቅ በመጣ ቁጥር ዛሬም ጭንቅ ላይ ነን፡፡
ዛሬ ከ5.6 ሚ. በላይ ህዝብ እርዳታ ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ በቋሚነት በየዓመቱ የሚረዱ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አሉ፡፡ ይሄ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ጎታች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ማህበረሰቡ በአንድ በኩል ለምፅዋት እጁን ሲዘረጋ ያለበትን ምስቅልቅል ለመግለፅ ያስቸግራል፡፡ የሚከሰተውን ስነ ልቦናዊ ቀውስ መገመት ይቻላል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎችን በመተቸት የተሻሉ አቅጣጫዎችን ማሳየት አለባቸው፡፡ ደርቆች የሚከሰቱባቸው ቦታዎች ከሚዲያው ሩቅ ናቸው። አስከፊ ገፅታቸውን አናይም ግን አየናቸውም አላየናቸውም ይሄ ከሀገር ህልውና ጉዳይ የሚተናነስ አይደለም፡፡ ልክ የሀገር ድንበር ሲደፈር እንደምንዘምተው፣ ለእንደዚህ አይነት መሰረታዊ ችግሮችም የፖለቲካ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ፣ አብቶ መዝመት ያስፈልጋል፡፡ መንግስት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን እንዲመረምር ግፊት መፍጠርና የተሻሉትን አማራጮች ማምጣት አለባቸው፡፡
የሙያ ማህበራትና በዚህ ላይ እውቀት አለኝ የሚል አካል ሁሉ ትኩረቱን በጉዳዩ ላይ አድርጎ፣ አዳዲስ አቅጣጫዎን ማሳየት አለበት፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን አሁንም ከድርቅና እርዳታ ጋር ተያይዞ የሀገራችን ስም መነሳቱ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ የሰው ልጅ አሁን ስለ ምግብ ሳይሆን ስለሌላ ተጨማሪ ፍላጎቶቹ በሚያስብበት ወቅት እኛ በልቶ ስለማደር ዛሬም መነጋገራችን አሳፋሪ ነው፡፡ ዜጎቻችንን ለመቀለብ የሚያስችል ፖሊሲ አጥተን እንደ መዳከር አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፖለቲካ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ከፖሊሲ አቅጣጫም ሀሳብ ማቅረብ አለባቸው፡፡ የምርምር ተቋማት ይሄን ችግር የሚፈታ መፍትሄ ማመንጨት እንዴት ይሳናቸዋል?
ከአመት ከአመት ይሄ የድርቅ ሁኔታ በሀገራችን አይቋረጥም፡፡ ሶማሌ፣ ኤርትራ፣ ኮንጎ … እንደ መንግስት አልባ ሀገራት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነሱ ስማቸው ከድርቅ ጋር ተያይዞ ቢነሳ የሚደንቅ አይሆንም፤ የኛ ግን አስደናቂ ነው፡፡ አደግን እያልን እንዴት አደጋውን መሻገር አቃተን? ይሄ ሁሉም ሊያስበው የሚገባ ነው፡፡ ቅድሚያ ትኩረት እንዴት አይሰጠውም?
መንግስት የሚያስፈልገው እርዳታውን የሚሰበስብና ልመናውን የሚያስተባብር ተቋምና በልመና የሰለጠነ “ባለሙያ” አይደለም ይሄን ችግር ሊፈታ የሚችል የፖሊሲ አቅጣጫ የሚቀርፅና መፍትሄ የሚያመጣ አካል ነው የሚያስፈልገው፡፡ ችግሩ በዝናብ ጠባቂነት የማይፈታ ከሆነ፣ በመስኖ፤ በመስኖ የማይፈታ ከሆነ፣ በሰፋፊ መካናይዝድ እርሻ። በሱም የማይፈታ ከሆነ፣ ወደ ኢንዱስትሪ መዞርና የመሳሰሉትን የፖሊሲ አማራጮች የሚያመነጭ አካል መፍጠር አለበት፡፡
የድርቅ አደጋ አሜሪካኖች፣ ራሺያዎች፣ ሌላው አለምም ገጥሞታል፤ ግን እነሱ የተለያዩ ፖሊሲዎች በመዘርጋት፣ ተፈጥሮን ለራሳቸው በሚመች መልኩ ገርተውታል፡፡ ተፈጥሮን ማሸነፍ አይቻልም፤ ግን መግራት ይቻላል፡፡ እኛ ማድረግ ያቃተን ይሄንን ነው፡፡ መንግሥት፤ የሚለምን ተቋም ከማደረጃት ይልቅ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያመነጭ ተቋም መፍጠር አለበት፡፡
ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ፣ ያ ሁሉ ድርቅና ረሀብ እያለ ደርግ ለ10ኛ የአብዮት በአሉ ሲደግስ ነበር፤ አሁን ደግሞ ይሄ ችግር እያለ የድርጅቶች ልደት ይከበራል። ይሄን እንደ ቀላል ነገር ልናየው አይገባም፡፡ ለዚህ የሚወጣው ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ጉልበት ብዙ ነው፡፡ ለችግሩ ትኩረት አለመሰጠቱንም ያሳያል፡፡

—————-

· መንግሥት የሚለምን ተቋም ከማደራጀት፣ ፖሊሲ የሚያመነጭ ተቋም ይፍጠር
· ድርቅን ማስቆም አይቻልም፤ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ እንጂ · ኬንያ ላለፉት 6 ዓመታት ድርቅ ላይ ናት፤ ግን ስለምግብ                 እጥረት ሲወራ አልሰማንም
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ
(የቢዝነስ አማካሪና ስራ ፈጣሪ)

ባለፈው አመት የተከሰተው ድርቅ ሰፊ መጠን ያለው ቢሆንም ሃገሪቱ እዚህ ግባ በማይባል የውጭ እርዳታና በራሷ አቅም መቋቋም ችላለች፡፡ ይህ ጥሩ ሁኔታ ላይ መድረሳችንን ያመለክታል፡፡ የድርቅ አደጋው የራስ አቅምንም ማሳያ ነበር፡፡ ድሮ እንዲህ ያለውን ድርቅ የምንቋቋምበት ምንም አቅም አልነበረንም፡፡ በሌላ በኩል በእርዳታ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የኢትዮጵያ የድርቅ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በጣም ጥሩ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እነ ኬንያ በዚህ ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ እኛ ከልምድም ሊሆን ይችላል፤ ድርቁ ሊመጣ ሲል የሚሰጠው ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚያበረታታ ነው፡፡
ወሳኙ ቅድመ ማስጠንቀቂያው ነው፡፡ ሰዎችን ከጉዳት አካባቢ ለማራቅና አስቀድሞ መፍትሄ ለማበጀት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ሌላው አንዱ አካባቢ ድርቅ ቢኖር፣ ሌላው አካባቢ የተስተካከለ አየር ንብረት ስለሚኖር፣ ምርትን ከምርታማ አካባቢ ወደ ተጎጂዎች የማቅረብ አቅም እየተፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶማሌ ክልል ድርቅ ቢኖር፣ ኦሮሚያ ዝናብ ቢኖር፣ ተረፈምርት ወደ ተጎጂዎች የማድረስ አቅም እየተገነባ መሆኑ በበጎ የሚታይ ነው፡፡
ድርቅ ተፈጥሯዊ ነው፤ ማስቆም አይቻልም፤ ግን ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኬንያ ላለፉት 6 ዓመታት ድርቅ ላይ ናት፡፡ ግን ስለ ምግብ እጥረት ሲወራ አልሰማንም፡፡ ተቋቁመውታል፡፡ ለእኔ የባለፈው አመት የሃገራችን ልምድ ድንቅ ነው፡፡ 16 ቢሊዮን ብር በጅቶ እርዳታ ማቅረብ መቻሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለወደፊትም በዚህ ከቀጠልን ያለ ምንም እርዳታ ራሳችንን እንችላለን፡፡ እርዳታ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የትም ሃገር ይኖራል፡፡ ሃብታም የሚባሉት ሃገሮች  እንኳን ሳይቀሩ እርዳታ ይጠይቃሉ፡፡
ለወደፊት ደግሞ የግብርና አዘማኝ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታችንን ማሳደግ መቻል አለብን፡፡ ትልቁን ዋስትናችን እሱ ነው፡፡ ውሃ በማቆርና ምርጥ ዘሮችን በማምጣት ድርቅን መቋቋም መቻል አለብን፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ ባልሳሳት ባለፉ 15 ዓመታት ከሁለት  እስከ ሦስት እጥፍ ምርታማነቱ ጨምሯል፡፡ ይሄ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ እየገባን እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቢል ጌት ኢትዮጵያ የምግብ ኤክስፖርት አድራጊ ሃገር ትሆናለች ብሏል፡፡ እኔም ይሄን ነው የምጠብቀው፤ እርግጠኛ ነኝ ድርቅም ቢኖር፣ ኢትዮጵያ ምግብን ለውጪ ገበያ በሰፊው የምታቀርብ ሃገር ትሆናለች፡፡ መካናይዝድ እርሻዎችን እየተጠቀምን ከሄድን፣ ካለን መሬት አንፃር ተጠቃሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ከአፍሪካ አንደኛ ነች፡፡ ከኛ ቀጥሎ ደቡብ አፍሪካ ትከተላለች፡፡ ግን ከህዝብ ብዛታችን ጋር አልተመጣጠነም፤ አቅሙ ስላለን በሠፊው ማሳደግ እንችላለን፡፡ 74 ሚሊዮን ሄክታር የሚለማ መሬት አለን፤ እስካሁን 15 ሚሊዮን የሚሆነው ነው እየለማ ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄን አቅም መጠቀም አለብን፡፡ ኢትዮጵያን የምግብ ማማ ማድረግ የምንችለው፣ ይሄን ሃብት በቴክኖሎጂ ታግዘን ስንጠቀም ነው፡፡ ውሃችንን በአግባቡ ከተጠቀምን፣ ድርቅ የሚያስከትለውን አደጋ በራሳችን አቅም መቋቋም አያቅተንም፡፡