ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲሱን የኤርትአሌ እሳተ ገሞራ ፍንዳታና ዳሎልን ለመጎብኘት ወደ አፋር ክልል ባቀናንበት ወቅት ካስተዋልናቸው መካከል በክልሉ ለ12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል የሚደረገው መሰናዶ ይጠቀሳል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች በዓልን ከሐረሪ ክልል በተረከበው ቀጣዩ አዘጋጅ አፋር ክልል በዓሉን በማስታከክ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል የስታዲየም ግንባታ ይገኝበታል፡፡ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በርካታ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የመሳብ ፍላጎት መኖሩን የገለጹልን የአፋር ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ያዩ እንደተናገሩት፣ ስታዲየሙ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ ነው፡፡
አቶ መሐመድ ከስታዲየም ግንባታው ጎን ለጎን ለጎብኚዎች ምቹ ማረፊያ በማዘጋጀት እንዲሁም ክልሉን በማስዋብ ረገድ እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴም ይናገራሉ፡፡ ስለ ስፖርታዊ ክንውኖች ሲነሳ ቀዳሚ ቦታ ከሚሰጣቸው ስታዲየም አንዱ እንደመሆኑ ግንባታው በዘርፉ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በርካታ ተመልካቾችና አፍቃሪዎች ያሉት እግር ኳስ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሲሆን፣ ስለ ግንባታውና እግር ኳስ ሲወሳ በክልሉ ዘመናትን ያስቆጠሩ ባህላዊ ስፖርቶች (ጨዋታዎች) ተያይዘው ይታወሳሉ፡፡ ባህላዊ ጨዋታዎች ከስፖርታዊ ውድድርነታቸው ጎን ለጎን በማኅበረሰቡ መካከል ቅርርብ በመፍጠርም ይታወቃሉ፡፡ በአፋር ክልል ተወዳጅ የሆኑ በርካታ ባህላዊ ጨዋታዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእግር ኳስ ጋር መጠነኛ ተመሳሳይነት ያለው ኳዕሶ ተጠቃሽ ነው፡፡
‹‹የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች›› በተሰኘው ጥናት እንደተመለከተው፣ ከክልሉ በርካታ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል ኳዕሶ አንዱ ሲሆን፣ የወንዶች ኳስ ሽሚያና ቅብብል ጨዋታ ነው፡፡ ኳዕሶ በአፋርኛ ኳስ እንደማለት ሲሆን፣ ጨዋታው አካላዊ ጥንካሬ፣ በቴክኒክና ታክቲክ በልጦ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ ለጨዋታው የሚሆን ኳስ የለሰለሰ የፍየል ቆዳ በትንሹ በማድበልበል ይዘጋጃል፡፡ የኳዕሶ ውድድር የሚካሄደው ከተለያዩ መንደሮች ወይም ፊኢማ ከሚባሉ ባህላዊ የማኅበረሰብ አወቃቀር ቡድኖች በተውጣጡ ሁለት ቡድኖች መካከል ነው፡፡ በውድድሩ ለመካፈል የዕድሜ ገደብ ባይኖርም ጨዋታው የልጆችና የአዋቂዎች በመባል ይከፋፈላል፡፡ በጨዋታው የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር ገደብ ባይኖረውም የሁለቱም ቡድኖች ተጨዋቾች ብዛት እንዲመጣጠኑ ይደረጋል፡፡
በኳዕሶ ጨዋታ ተወዳዳሪ ቡድኖች ፊት ለፊት ከቆሙ በኋላ፣ ኳሷን አንድ ሰው አንጥሮ ጨዋታውን ይጀምራል፡፡ ኳሷን ያነጣረው ሰው ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ሲሮጥ እሱን ለመጣል በሚደረግ ትግል ጨዋታው ይቀጥላል፡፡ በጨዋታው ወቅት ተወዳዳሪዎቹ ከወገብ በላይ መልበስ አይችሉም፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል ኳስ በመቀባበል ማለትም በተቃራኒው ቡድን ኳስን ሳያስነጥቅ ብዙ መቆየት የቻለ ቡድን አሸናፊ ይሆናል፡፡ በአፋሮች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ እንደሆነ የሚነገርለት ኳዕሶ ሲካሄድ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ይነገራል፡፡ ጨዋታው ከመወደዱ የተነሳ ተጨዋቾች እስከሚደክማቸው ድረስ ቀኑን ሙሉ ሊዘልቅም ይችላል፡፡
ጨዋታው የተጀመረበት ወቅት በውል ባይታወቅም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው ጨዋታው፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጥበቅ ከሚረዱ ክንውኖች መካከል ይገኝበታል፡፡ ከጨዋታው በፊትና በኋላ በዳጉ መረጃ የመለዋወጥ ልማድ ያለ ሲሆን፣ ኳዕሶ በዓላት ሲከበሩና ሠርግ ለማድመቅም ተመራጭ ነው፡፡
ጨዋታው በብዛት የሚካሄደው በክረምት ሲሆን፣ የሚጫወቱት ቡድኖች በስምምነት ቀን ይቆርጣሉ፡፡ ቱፋል በመባል በሚታወቀው የቀን ቆረጣ ሥርዓት የተጫዋቾቹ ቡድኖች አምበሎች (ኢናይታ በመባል የሚታወቁ) ጨዋታው የሚካሄድበትን ወቅት በማሳወቅ ተጨዋቾች እንዲዘጋጁ ያደርጋሉ፡፡ ጨዋታው የሚካሄድበት ጊዜ ሰዎች ልዩ ልዩ ኃላፊነቶችን የሚያጠናቅቁበት የመኸር ወቅት በመሆኑ ጊላል ተብሎ ይጠራል፡፡ የኳዕሶ ጨዋታ ሲጠናቀቅ የቡድን ኢናይታ ወይም ከአገር ሽማግሌዎች አንዱ ኳሷን በመወርወር ይዘጉታል፡፡
እንደ ኳዕሶ በማኅበረሰቡ ተወዳጅነትን አትርፈው ዘመናት የተሻገሩ ባህላዊ ጨዋታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ባህላዊ ጨዋታዎች እንደየማኅበረሰቡ ባህልና አኗኗር የሚፈጠሩ ሲሆኑ፣ በየአገሩ የታሪክ መዛግብት አያሌ ባህላዊ ስፖርቶች ይገኛሉ፡፡ ጨዋታዎቹ ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ባሻገር ያላቸው ዕውቅና ቢያጠያይቅም ለኅብረተሰቡ ያላቸው ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
በአፋር ክልል የሚዘወተረው ሌላው ባህላዊ ጨዋታ ላሎይታ፣ ከኳዕሶ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ የሚለየው ተጫዋቾች የሚወዳደሩት ውኃ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ለጨዋታው የሚዘጋጅ መጠነኛ እንጨት ውኃ ውስጥ ይከተትና ተጨዋቾች የእንጨቱን አቅጣጫ ለማግኘት ይጣጣራሉ፡፡ እንጨቱን ያገኘ ተጨዋች በጥርሱ ይዞ እየዋኘ እንጨቱን ማድረስ ወደ ሚጠበቅበት ቦታ ሲወሰድ፣ ሌሎች ተጨዋቾች እንጨቱን ለማስጣል በመሞከር ይፎካከራሉ፡፡ ተጫዋቹ እንጨቱን ሳይቀማና ውኃ ውስጥ ሳይሰጥም መድረስ ያለበት ቦታ ከደረሰ አሸናፊነቱን ይቀዳጃል፡፡
በአፋር ዕውቅ ከሆኑ ጨዋታዎች መካከል ትግል አንዱ ሲሆን፣ ጨዋታው በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለመደ ነው፡፡ ትግል በዓመታዊው የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ውድድር ውስጥም ይካተታል፡፡ በዓመታዊ ውድድሩ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታ፣ ዳርትና ሌሎችም ጨዋታዎች ያሉ ሲሆን፣ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተጨዋቾች ይሳተፋሉ፡፡
አፋር አካባቢ ከእንጨት በተሠራ መጫወቻ ወይም መሬት ላይ ጉድጓድ በማዘጋጀት በጠጠር የሚካሄድና እንደ ገበጣ ያለ ደቡዳ የተባለ ጨዋታ አለ፡፡ ጨዋታው ከማዝናናት ጎን ለጎን የሒሳብ ስሌት ችሎታን በማዳበርም ይታወቃል፡፡ በአካባቢው በመጠኑ ከዳቡዳ ጋር የሚመሳሰል ባድእስ የሚባል ጨዋታ አለ፡፡ ጋባ ዳአ የሚባለውም ከደቡዳ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ሴቶችና ወንዶች በኅብረት ወይም በተጠናል የሚጫወቱት ሲሆን፣ ጠጠሮች ሰብስቦ አንዱን ጠጠር ወደ ላይ በመወርወርና በማንሳት ተጫዋቾች ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ይፎካከሩበታል፡፡
በክልሉ የድንጋይና የጦር ውርወራን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ የውርወራ ጨዋታዎች ያሉ ሲሆን፣ ማህዲ አምቦ (ጦር ውርወራ) ይጠቀሳል፡፡ ውድድሩ በጦር (መሃዳ በመባል በአፋርኛ የሚጠራው) ውርወራ ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የሚካሄደው ወደ ጫካ በመሄድ ወይም በአደን ወቅት ነው፡፡ በማህዲ አምቦ ጎበዝ የሆኑ ተጨዋቾች በማኅበረሰቡ ዘንድ ክብር ይሰጣቸዋል፡፡
ኩላ-ሀቤክ ይላ-ሀቤ የድብብቆሽ ጨዋታ ሲሆን፣ ትርጉሙ ‹‹የአንተን ከብት ልተወው ወይም የኔን ከብት ተው›› እንደማለት ነው፡፡ በጨዋታው ወንዶችና ሴቶች በቡድን ተከፋፍለው አንዱ ቡድን ከሌላው ከብት እንደደበቀ በማስመሰል ይካሄዳል፡፡ አንድ ቡድን በሦስት የተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ነገሮች ይደብቅና ሌላው ቡድን ይፈልጋል፡፡ ቡድኑ ከተደበቁት ነገሮች መካከል ባገኘው መጠን በዳኞች ነጥብ ተሰጥቶ አሸናፊው ይለያል፡፡
በሰዎች መካከል ከሚደረጉ ባህላዊ ጨዋታዎች ባሻገር በእንስሳት መካከል የሚደረጉ ውድድሮችም በአፋር የተለመዱ ናቸው፡፡ አላላ ከብቶች ለግጦሽ በሚሰማሩበት ወቅት የሚካሄድ ውድድር ነው፡፡ አርብቶ አደሮች ከከብቶቻቸው መካከል ጠንካራ ያሏቸውን በውድድሩ ያሳትፋሉ፡፡ ከከብቶቹ መካከል ፊት መሪ ላም ወይም በሬ የሚኖር ሲሆን፣ ከብቶቹ መንጋውን ከፊት ሆነው በፍጥነት እየተጓዙ ይመራሉ፡፡
ውድድሩ ምን ጊዜም የሚከናወነው ውኃና ሳር ባለበት አካባቢ ሲሆን፣ ውድድሩ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ሊወስድ ይችላል፡፡ አወዳዳሪዎች ከብቶቹ ፍጥነት እንዲጨምሩ፣ እንዲቆሙ ወይም ሌላ ክንውን እንዲያደርጉ ሲፈልጉ የተለያየ ድምፅ ያሰሟቸዋል፡፡ ከብቶቹ ድምጾቹን ስለሚለማመዷቸው ትዕዛዙን ተከትለው እንደሚንቀሳቀሱም ይነገራል፡፡ በስተመጨረሻ የውድድሩ ዳኞች በውድድሩ ማጠናቀቂያ ቦታ ሆነው ጠንካራውን ከብት ከደካማው በመለየት ብይን ይሰጣሉ፡፡ ውድድሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ በጉጉት ከሚጠበቁ ክንውኖች አንዱ ሲሆን፣ ከውድድሩ በፊት ያለው የፉክክር ስሜትና ድሉም ትልቅ ቦታ ይቸራቸዋል፡፡
ከዩ ባህላዊ የግመል ግልቢያ ውድድር ሲሆን፣ የተወዳዳሪው ግመል ቁመና፣ ብርታት፣ ጉብዝናና ጥንካሬን ማሳየት የውድድሩ ዋና ዓላማ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከዩ እንደ አላላ ሁሉ መኖና ውኃ በደንብ በሚገኝበት ወቅት ይከናወናል፡፡ ውድድሩ ከአምስት እስከ አሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ሊሸፍንም ይችላል፡፡ የተወዳዳሪዎች ብዛት በውድድሩ መሳተፍ ፈልገው እንደመጡት ሰዎች የሚወሰን ይሆናል፡፡
በክልሉ ማኅበረሰቡ የሚዝናናባቸው፣ ተወዳድሮ የሚያሸንፍባቸውና ብርቱውን የሚለይባቸው ሌሎችም ባህላዊ ጨዋታዎችም ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ እንደ ከዩ ያሉ ጨዋታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ እንደመጡ ጥናቱ ቢያሳይም፣ ማኅበረሰቡ አሁንም ጠብቆ ያቆያቸው ባህላዊ ጨዋታዎች መኖራቸውም ይገለጻል፡፡