ዘጠኝ ሴቶችን አገባችኋለሁ በማለት ቅምጥ ካደረጋቸው በኋላ ሀብትና ንብረታቸውን ያጭበረበረው ወጣት በ10 አመት ጽኑ እስራት ተቀጥቷል።ግለሰቡ በደሴ ከተማ ምንም ሳይኖረው የስራ ተቋራጭ ነኝ በማለት በርካታ ሰዎችን ማጭበርበሩም ተጠቅሷል።
ሀብታሙ አረጎ የተባለው ተከሳሽ በደሴ ነዋሪ ቢሆንም ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ የለውም።ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በከተማዋ የተለያዩ ህንፃዎችን እንደሚያስገነባ እና ተሽከርካሪዎች እንዳሉት በመናገር ገንዘብ ሲቀበል መቆየቱን የደሴ ከተማ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ዋና ኢንስፔክተር አሳምን ሙላት ተናግረዋል።
ግለሰቡ ዘጠኝ ሴቶችን አግብቶ መገኘቱንም ነው የገለጹት።ከአንደኛዋ አገባሻለሁ ካላት ሴት ቤተሰቦቼ ከአዲስ አበባ ይመጣሉ በማለት እንደ ጂፓስ ያሉ እቃዎችን እንድታውሰው በመጠየቅ መዝረፉ ተጠቅሷል።
ሌላኛዋን ነጋዴም እንደሚያገባት በማግባባት ከሱቋ ዘይት እና ሌሎች የባልትና ውጤቶችን ወደ አዲሱ ጎጇችን ልውሰድልሽ በማለት እቃ ላዋሰችው ሴት ሰጥቷል።የስራ ተቋራጭ በመምሰል የተለያዩ የማጭበርበር ተግባራትን መፈፀሙ ተጠቁሟል።
በአጠቃላይ ከተለያዩ ግለሰቦች ከ188 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን አጭበርብሮ መውሰዱን ጥቆማ የደረሰው ነው የከተማዋ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያም ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፍለጋ ይጀምራል።ነገር ግን አድራሻውን እየቀያየረ የሚኖር በመሆኑ በቀላሉ ሊገኝ አልቻለም።
ፖሊስ ተጎጂዎን አስተባብሮ ያደረገው የማፈላለግ ስራም ፍሬ አፍርቶ በቁጥጥር ስር ውሏል። ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃልም ድርጊቱን መፈፀሙን አምኗል።
የደቡብ ወሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም በተከሳሹ ላይ ክስ የመሰረተ ሲሆን፥ ጥፋተኝነቱንም በማስረጃዎች አረጋግጧል።በዚህም ተከሳሹ በ10 አመት ፅኑ እስራት እና በ6 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል።ግለሰቡ ያጭበረበረው ከ100 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ እና የተለያዩ ንብረቶችም ለባለቤቶቹ እንዲመለስ መደረጉን የከተማዋ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ያስታወቀው። ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ