በመቶዎች የሚቆጠሩ የዝምተኛው ኮሜዲያን ቻርሊ ቻፕሊን አድናቂዎች 128ኛ የልደት ቀኑን ለ25 ዓመታት በኖረበት የቀድሞ ቤቱ ውስጥ ተገኝተው ለማክበር ተሰባስበዋል፡፡
ቻፕን ትራምፕ በሚባለው ዝምተኛ እና ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በሚታወቀው ቤት አልባው ተዋናይ ይታወቃል፡፡
በፊልሙ ውስጥ ዝምተኛው ትራምፕ በሚያደርጋቸው ድርጊቶች ብቻ የሰውን ቀልብ በመሳብ የሳቅ ምንጭም ሆኗል፡፡
በድንቅ ትወናው ዘመን ተሻጋሪ ሲሆን ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የኮሜዲ ፊልሞቹ ይታያሉ፡፡
ታዲያ አድናቂዎቹ በስዊዘርላንድ በሚገኘው የቻርሊ ቻፕሊን ቤት በመገኘት፥ ትራምፕ የተባለውን ገፀባህርይ ሲጫወት የለበሰውን አለባበስ ለብሰው የልደት ቀኑን ለማክበር በርካቶች ተሰባስበዋል፡፡
እነዚህ አድናቂዎቹ ከ660 በላይ ሲሆኑ በፊልሙ ውስጥ እንዳለው ትራምፕ ሁሉ ጺም አቆራረጣቸውን፣ ጥቁር ቆብ ጨምሮ ጥቁር በጥቁር መልበሳቸው፣ ከዘራ መያዛቸው፣ አካሄዳቸውን ሁሉ ለማስመሰል ጥረዋል፡፡
ቻፕሊን በፈረንጆች 1977 እስከሚሞት ድረስ በኖረበት እና አሁን ቻፕሊን የዓለም ሙዚየም በተባለው ግቢ ውስጥ የቻፕሊንን የትወና ገፀባህርይ (ትራምፕ) አለባበስ ለብሰው የተሰባሰቡት 662 ደጋፊዎቹ ባለ አምስት ቅርፅ ኮከብ ሰርተው ፎቶ ግራፍ ተነስተዋል፡፡
አዛውንቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች የተሰባሰቡበት ይህ ልዩ ሁነት የትራምፕን ገፀ ባህርይ አለባበስ ለብሰው የቻፕሊንን እና የሙዚየሙን የልደት ቀን ያሰቡ በርካታ ሰዎች በሚል በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ሊሰፍሩ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ትራምፕ የቻርሊ ቻፕሊን ቅፅል ስም ሲሆን በ1915 በተሰራው አጭር ፊልም ውስጥ ቻፕሊን በዋና ተዋናይነት የሰራው ገፀባህርይ ነው፡፡
ምንጭ፡-አሶሺየትድ ፕሬስ