በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በቢሊየን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ካላቸው የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ውስጥ ፌስቡክ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል።
ታዲያ ይህ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን እያገኘ እና ለተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች እና የንግድ ስራዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ፌስቡክ የመረጃ ጠላፊዎች ሰለባ መሆኑ ለበርካቶች የራስ ምታት ሆኗል።
የፌስቡክ አድራሻችን የመጠለፍ ጥቃት በመረጃ ጠላፊዎች ብቻ ሳይሆን ለኛ በጎ አመለካካት ቤላለቸው ሰዎች፣ በቀድሞ የፍቅር ጓደኞቻችን አሊያም በስራ ገበታችን ላይ ከኛ ጋር ተቀናቃኝ በሆኑ ሰዎች ሊደርስ ይችላል።
ታዲያ የፌስቡክ አድራሻችን በቀላሉ በጠላፊዎች እጅ እንዳይገባ መጀመሪያ ላይ ማድረግ ያለብን ነገር ጠንካራ የሆነ የይለፍ ቃል ማዘጋጀት ነው።
ለዚህም ይረዳን ዘንድ የይለፍ ቃላችን በሌሎች በቀላሉ ሊደረስበት በማይችሉ የፊደላት፣ የቁጥሮች እና ሌሎች የምልክቶች (ካራክተሮች) ስብጥር ቢሆን ይመረጣል።
እንዲሁም የፌስቡክ አድራሻን በቫይረሶች አማካኝነት ሊጠለፍ ስለሚችል እነዚህን ቫይረሶች የሚከላከሉ ሶፍትዌሮችን በሲስተማችን ላይ በመጫን መጠቀምም መልካም ነው።
የፌስቡክ አድራሻችን መጠለፉን ለማወቅ…
የፌስቡክ አድራሻችን ጠላፊዎች እጅ መግባቱን በቀላሉ ለመለየት መጀመሪያ “Settings,” የሚለውን መክፈት በመቀጠልም “Security” የሚለውን በመክፈት ከሚመጡልን አማጮች ውስጥ ፌስቡካችን ክፍት የሆነበትን ስፍራ የሚያሳየንን “Where you’re logged in” የሚለውን መክፈት ይጠበቅብናል።
በዚህ ጊዜም ፌስቡካችን የት ቦታ ላይ በምን አይነት የኤሌክትሮኒክስ መገልገያ እንደተከፈተ በዝርዝር ያመጣልናል።
ከሚመጣልን ዝርዝር ውስጥ ከዚህ ቀደም ተጠቅመንበት የማናውቀው ቦታ ላይ የፌስቡክ አድራሻችን ተከፍቶ ካገኘን ይህ የፌስቡክ አድራሻን መጠለፉን ያመለክታል ነው የተባለው።
በዚህ ጊዜም “Where you’re logged in” ከሚለው ስር የሚገኘውን “End activity” የሚለውን በመጫን የፌስቡክ አድራሻችንን ከቀማኛዎች መታደግ እንችላለን።
“End activity” አድራሻችንን ከዘጋን በኋላ ግን በቀዳሚነት ማድረግ ያለብን ነገር የይለፍ ቃላችንን መቀየር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።
ከዚህ በተጨማሪም የፌስቡክ አድራሻን መጠለፉን ምልክት ከሚሆኑን ውስጥ ፌስቡክ ላይ ያስቀመጥናቸው መረጃዎቻችን መቀያየር፣ ለማናውቃቸው ሰዎች የተላኩ የጓደኝነት ጥያቄዎች እንዲሁም የተላኩ መልእክቶች ይገኙበታል።
እንዲሁም እኛ ያልጫናቸው ምስሎችም ይሁን ሌሎች ጽሁፎች በፌስቡክ ገጻችን ላይ መለጠፍም ፌስቡካችን ስለመጠለፉ ምልክት ነው ተብሏል።
የመጀመሪያ ነገር የፌስቡክ የይለፍ ቃላችንን መቀየር ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ፌስቡክ ያስቀመጠልንን የደህንነት አማራጭ መጠቀም ነው።
ለዚህም ይረዳን ዘንድ የፌስቡክ “Help Page” ውስጥ በመግባት “I think my account was hacked or someone is using it without my permission” የሚለውን በመክፈት “secure it” የሚለውን መጫን ይኖርብናል።
በዚህ ጊዜም ፌስቡክ አድራሻችን የት የት ቦታ ላይ ተከፍቶ እንዳለ የሚያሳየን ሲሆን፥ የሚመጣልንን ቅደም ተከተል በመከተልም የፌስቡክ አድራሻችንን ደህንነት መጠበቅ እንችላለን።