ጉንፋን በአብዛኛው በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ ነው።ጉንፋን የተለመደ በሽታ እንደመሆኑ መጠን ምናልባትም በአመት ሁለት እና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ለዚህ በሽታ የመጋለጥ እድል መኖሩን ጥናቶች ያመለክታሉ።
ጉንፋንን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ማከም እና መከላከል ግን ይቻላል፤ ለዚህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ በሚዘጋጁ መፍትሄዎች መከላከል እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እነዚህ መከላከያ መንገዶች ደግሞ የጉሮሮ መከርከርና ማቃጠልን ጨምሮ፣ የአፍንጫ መዘጋት እና መታፈን፣ ሳል፣ የፊት እና በተለይም የአፍንጫ አካባቢ መቅላት እና ህመምን መከላከል ያስችላሉ።
መፍትሄ መጉመጥመጥ፦ አፍን ወደ ላይ ቀና አደርጎ ከጀርባ ወደ ኋላ ገለል በማለት ጥቂት ውሃ ወደ ጉሮሮ በማፍሰስ መጉመጥመጥ የጉሮሮ መከርከርና ማቃጠልን ለመከላከል ይረዳል።ለዚህ ደግሞ 1 የሻይ ማንኪያ ጨውን ለብ ባለ አንድ ኩባያ ውሃ በመቀላቀል ወደ ጉሮሮ ማንቆርቆር እና መጉመጥመጥ።ከዚህ ባለፈም 1 የሻይ ማንኪያ የሎሚ ውሃና ማርን አንድ ላይ በማድረግ ከውሃው ጋር ቀላቅሎ መጠቀም፤ ውሃው ግን ለብ ያለ እንጅ የሚያቃጥል መሆን የለበትም።
ፈሳሽ መውሰድ፦ ፈሳሽ ማብዛቱ ከሰውነት የወጣውን ፈሳሽ በመተካት ፈሳሽ እንዳያጥርና ድርቀት እንዳይፈጠር ያደርጋል።ከዚህ ባለፈም በጉንፋኑ ምክንያት በመጠን የሚበዛውን ንፍጥ በማቅጠን የአፍንጫ መዘጋትና መታፈንን ይቀንሳል።ለዚህም ውሃና ሌሎች ጭማቂዎችን በብዛት መጠጣት።
ሻይ በሎሚ እና በማር ቀላቅሎ መጠጣትም ይመከራል፤ ሻይን በሎሚ እና በማር መጠቀምዎ የአፍንጫ መደፈንና መታፈንን እና የጉሮሮ ህመምን ለማከም እንደሚረዳም ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሾርባ በተለይም የአትክልት ሾርባዎችን መውሰድም ይመከራል፥ በጉንፋኑ ምክንያት የሚፈጠረውን የአፍንጫ መዘጋት በመክፈት በአግባቡ ለመተንፈስ ስለሚረዳ።
እንደ ቡና እና አልኮል ያሉ መጠጦችን ደግሞ ያስወግዱ።
ሙቀት፦ ሞቅ ባለ ውሃ ገላን መታጠብ የአፍንጫ መደፈንን ያስወግዳል።ጉንፋን በታመሙ ጊዜ በሙቅ ውሃ መታጠብ አልያም ውሃን በማፍላት በጎድጓዳ ሳህን በማድረግ በፎጣ ነገር ተከናንቦ መታጠን።ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚህ ወቅት መድሃኒት ቤት የሚሸጡና ለጉንፋን ማከሚያ የሚረዱ ኢዩካሊፕተስ የሚባሉ ጠብታዎችን ውሃው ላይ በማድረግ መጠቀም።እንዲሁም የውሃውንና የጠብታውን ውህድ አፍንጫ ውስጥ ማድረግም መልካም ነው፤ ይህን ሲያደርጉ ግን አይንዎን መጨፈን ይኖርብዎታል።ከዚህ ባለፈም ሲናፈጡ አፍንጫን በአግባቡ መያዝና ከልክ በላይ አለመጫንም መልካም ነው።ከተናፈጡ በኋላ የማይበን ሶፍት በመጠቀም በስሱ በማስገባት ቀሪ ቆሻሻዎችን ማውጣትም ይልመዱ።
ማር፦ በጉንፋን የተያዘ አዋቂ ሰው ማርን ከሻይ ጋር ቀላቅሎ እንዲጠቀም ይመከራል።እድሜያቸው ከአንድ አመት በላይ ለሆኑ ህጻናት ደግሞ ከመኝታ በፊት በጥቂቱ መስጠት፤ በመኝታ ሰዓት እንዳይስሉ ይረዳቸዋልና።
መድሃኒት መጠቀም፦ ጨዋማ ጠብታዎች፤ መድሃኒት ቤት የሚገኙና ጉንፋንን ለማከም የሚረዱ ጨዋማ ጠብታዎችን መጠቀም በዚህ ወቅት ሊከሰት የሚችልን ሳይነስለማስቀረት ይረዳል።
ይህን በተለይም ለህጻናት ማድረጉ ተመራጭ ነው።
አሴታሚኖፌን፤ ይህ መድሃኒት በተለይም ህጻናት ጉንፋን በያዛቸው ወቅት ከፍተኛ ትኩሳትና የሰውነት መድከም ስለሚያጋጥማቸው ይህ እንዳይሆን ስለሚረዳቸው መጠቀሙ ይመከራል።
ይህ ግን በአብዛኛው ጨቅላ ህጻናት ለሚባሉት የሚሰጥ በመሆኑ ከዚያ ከፍ ላሉት ባለሙያ ያማክሩ።እነዚህን ቤት ውስጥ አዘጋጅተው በመጠቀምዎ በሽታው እስከሚለቅዎት ድረስ የተሻለ ጥንካሬን እንዲያገኙ ይረዳወታል።ጉንፋን ተይዘው ከ10 ቀናት በላይ ከቆየ እና ጠንከር ካለ ወደ ህክምና ተቋም በማምራት ባለሙያ ማማከርን ግን እንዳይረሱ።
ከዚህ ባለፈ ግን በየዕለቱ የራስንም ሆነ የመኖሪያዎን ንጽህና መጠበቅና አካባቢን ማጽዳት፣ ጉንፋን ከተያዙም እስከሚሻልዎት ወደ ሌላ ሰው እንዳይዛመት ጥንቃቄ ማድረግንም ልማድዎ ያድርጉ።ሲስሉም ሆነ ሲያስነጥሱ ዘወር ብለው አልያም በሶፍትና በመሃረብ ማድረግ እና ሶፍትና መሃረቡን ከአካባቢው ማስወገድ።ምንጭ፦ medicalnewstoday.com/