ፌስቡክ ያልወደድነውን ነገር መጥላታችንን ለመግለጽ የሚረዳ “ዲስላይክ” ምልክት ላይ ሙከራ እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።
በፌስቡክ የወደድነውን ነገር ላይክ ቁልፍን በመጫን መውደዳችንን መግለፅ እንደምንችል ሁሉ ሙከራ እየተደረገበት ባለው “ዲስላይክ” ያየነውን ነገር አለመውደዳችንን ለመግለጽ ያስችላል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በርካቶች ፌስቡክ ይህንን የዲስላይክ ቁልፍ እንዲያቀርብ ቢጠይቁም ከኩባንያው በኩል ምላሽ ሳይሰጥበት ቆይቷል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ይህ ምልክት በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ላይ ጥላቻ እንዲበራከት ያደርጋል የሚል ነው።
አሁን ላይ ግን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረውን የዲስላይክ ምልክት በቅርቡ ማግኘታቸው አይቀርም የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።
የፌስቡክ ኩባንያ የዲስላይክ ምልክቱንም በፌስኑክ ሜሴንጀር ላይ እየሞከረ መሆኑም ነው የተሰማው።
በሜሴንጀር ላይ አዲስ እየተሞከረ ያለው አገልግሎት በርካታ ኢሞጂዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ የዲስላይክ ምልክት ወይም ወደ ታች የተዘቀዘቀ የአውራ ጣት ምልክት ተካቶበታል ነው የተባለው።
በሜሴንጀር ላይ እየተደረገ ያለው ሙከራ ሙሉ በሙሉ በሚጠናቀቅበት ጊዜም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የፌስቡክ ኩባንያም በሜሴንጀር ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የተለያዩ ኢሞጂዎችን እያካተተ መሆኑን አስታውቋል።