ጄኔራል ኦያይ ዴንግ አጃክ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባርን እ.ኤ.አ በ1982 ተቀላቀሉ፡፡ አገሪቱ ከዋናዋ ሱዳን ነፃ እስካወጣች ድረስ የግንባሩ ጦር ኃይል ዋና አዛዥ ነበሩ፡፡ አገሪቱ ነፃ ከወጣች በኋላ ከጦር ኃይሉ በመውጣት የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነትን በመያዝ ደቡብ ሱዳንን አገልግለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊና የአገሪቱ ኢንቨስትመንት ሚኒስትር መሆናቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ጄኔራል ኦያይ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጠርጥረው ለእስር ከተዳረጉት ሚኒስትሮች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ አሁን ጄኔራሉ በኢጋድ የሚመራው የሰላም ሒደት ተደራዳሪ ናቸው፡፡ ወቅታዊ የደቡብ ሱዳን ጉዳዮችን አስመልክቶ የማነ ናግሽ ጄኔራሉን አነጋግሯቸዋል፡፡ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. በ2013 በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል ተብለው ተጠርጥረው ለእስር ከተዳረጉት መካከል ነዎት፡፡ በወቅቱ ምን ነበር የተፈጠረውጄኔራል ኦያይ፡- በወቅቱ ቀውሱ ሲጀመር 13 ሚኒስትሮች ነበርን ለእስር የተዳረግነው፡፡ እኔ ላይ ክስ ተመሥርቶብኝ ነበር፡፡ ሳልቫ ኪር የመሠረቱብኝ ክስ በእሳቸው ላይ መፈንቅለ መንግሥት አቀነባብረሃል፣ ሙከራ አድርገሃል በሚል ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደ ፍርድ ቤት አቅርበውናል፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ግን ክሱ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ምክንያቱም ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘብንም፡፡ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንቱ ይህንን ዕርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳቸው ምን ነበር?ጄኔራል ኦያይ፡- በእርግጥ ልዩነቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ ብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች ነበሩብን፡፡ በተለይ ከሙስና ጋር በተያያዘ፣ የድርጅቱ የውስጥ ጉዳይ፣ የአስተዳደር ጉዳይ፣ እንዲሁም ከምርጫ ሒደት ጋር በተያያዘ ብዙ ስንጨቃጨቅ ነበር፡፡ የእኛ ሐሳብ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብለን ማውራት አለብን የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች የደቡብ ሱዳን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱም መጀመሪያ፣ ‹‹እሺ ቁጭ ብለን እናወራለን›› ብለው ነበር፡፡ በሒደት ግን እኛን ማሰር እንደ መፍትሔ ነበር የወሰዱት፡፡ በመሠረቱ ችግሩ የድርጅቱ የውስጥ ችግር ነው፡፡ ፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ስላልቻሉ እኛን በማሰር ችግሩን ለማስቀየስ ሞክረዋል፡፡ ብዙ ክሶች ነበር ያቀረቡብን፡፡ ገንዘብ ሠርቀዋል፣ ሙስና ፈጽመዋል፣ ወዘተ. . . በማለት ከሰሱን፡፡ እኛም ወደ ሚዲያ ሄደን ነገሩን ግልጽ አደረግነው፡፡ እኛ ያጠፋነው ካለ ለመመርመር ዝግጁ ነን፣ ለሎችም ምርመራ ይደረግባቸው ብለን መግለጫ ሰጠን፡፡በእርግጥ የአገሪቱ ገንዘብ ተሰርቋል፣ ብዙ ጥፋትም ተፈጽሟል፡፡ እኛ አልነበርንም ያጠፋነው፡፡ በገለልተኛ አካል እንዲታይ ነበር የጠየቅነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን ያደረጉት ምንድነው? በማጣራት ምትክ እኛን ይደግፋሉ ተብለው የተጠረጠሩት ወታደራዊ አዛዦች ትጥቅ እንዲፈቱ ነው ያደረጉት፡፡ እንዲሁም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ሪክ ማቻር ላይ አነጣጠሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ውጊያ ተቀሰቀሰ፡፡ ያንን ሁከት አሳበው እኛን ለማሰርና ለመግደል ነበር የፈለጉት፡፡ መግደል ስላልቻሉ ለእስር ዳረጉን፡፡ ከዚያም የውሸት ክስ ይዘው ቀረቡና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል አሉ፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ‹‹ምንም ዓይነት ማስረጃ አላገኘሁም›› ስላለ ልንፈታ ችለናል፡፡ሪፖርተር፡- ከዚያ በኋላ የነበረውን የድርድር ሒደት እንዴት አዩት? የእናንተ ድርሻስ ምን ነበር?ጄኔራል ኦያይ፡- በድርድሩ ውስጥ በአንድ በኩል የአገሪቱን መንግሥት እወክላለሁ የሚሉት ሳልቫ ኪር ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመራው ተቃማሚ ቡድን ነበር፡፡ በእስር የነበርን ደግሞ አንድ ቡድን ፈጥረናል፡፡ ሌላ አራተኛ ተደራዳሪ ቡድንም ነበር፡፡ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ከመነሻው ስለምንረዳው ተሳትፏችን ከፍተኛ ነበር፡፡ ቀውሱን ለመፍታት የበኩላችን ተወጥተናል፡፡ በእርግጥ ለእርቅ የቀረበው ሰነድ በአብዛኛው የእኛ አስተዋጽኦ ነበረበት፡፡ በአብዛኛው የምንስማማበት ነው፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አንስማማም፡፡ ድርድሩንም ቢሆን ተቀብለነዋል፡፡በኋላ ግን በአሜሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን የስምምነቱን ሰነዱ ለመፈረም ተጠርተን፣ ሁሉም አደራደሪ ኃይሎችና ተደራዳሪዎች ቀርበው የእኛን ፊርማ እየተጠባበቁ እያለ ችግር ተፈጠረ፡፡ ሁሉም ተደራዳሪ አካል ለመፈረም እንደተዘጋጀ ነበር መሪዎች የሚያውቁት፡፡ ሳልቫ ኪር ግን ድንገት ተነሱና ለመፈረም ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናገሩ፡፡ አንዳንድ የማይስማሙባቸው ጉዳዮች ሰነዱ ውስጥ እንዳሉና ተጨማሪ ድርድር ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናገሩ፡፡ ችግሩ የመጣው እዚህ ላይ ነበር፡፡ስምምነቱ ለበርካታ ጊዜያት ተደራድረን ያፀደቅነው ነበር፡፡ የሳልቫ ኪርም ተወካይ ተደራድሮ የተረቀቀ ነበር፡፡ በመጨረሻ ለመፈራረም ዝግጁ በሆንበት ሰዓት አልፈራረምም አሉ፡፡ አንተን የሚመች ብቻ ለመፈራረም ድርድር ማድረግም አያስፈልግም፡፡ ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን በመሪዎቹ ፊት አይሆንም አሉ፡፡ ጁባ ሂጄ ሕዝቤን ማማከር እፈልጋለሁ አሉ፡፡ ሁለት ሳምንት ተሰጣቸውና ይምከሩበት ተባለ፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ውጪ የተቀረን ተደራዳሪዎች ፈረምን፡፡ ጁባ ከሄዱ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲሁም፣ ለሌሎች የኢጋድ መሪዎች ስልክ በመደወል፣ በጁባ ለመፈረም ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ፡፡መሪዎቹ ወደ ጁባ ካመሩ በኋላ ባለአሥር ገጽ ሰነድ አዘጋጅተው የሐሳብ ልዩነታቸውን ይዘው ጠበቋቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በስምምነቱ የተካተቱ ሲሆኑ፣ ሰነዱ ላይ የኢጋድ የአገር መሪዎቹ እንዲፈርሙበት ጠየቁ፡፡ መሪዎቹ ደግሞ ይኼማ አይሆንም አሉ፡፡ ‹‹ወደ ጁባ የመጡት የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን ፊርማ ለማየትና ለመመስከር እንጂ ሌላ ስምምነት ለመፈረም እንዳልሆነ ገለጹላቸው፡፡ በሰነዱ ላይ ነጠላ ሰረዝ አንቀይርም አሉ፡፡ በግዴታ ፈረሙ፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ግን የሚገርም ንግግር አድርገዋል፡፡ ስምምነቱ መጽሐፍ ቅዱስና ቁርዓን ስላልሆነ ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት ሳይስማሙበት ነው፡፡ በእሳቸው አባባል በወቅቱ የፈረሙት በመሪዎቹ ጫና ተደርጎባቸው እንጂ አምነውበት አልነበረም፡፡ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንቱ ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ የኢጋድ መሪዎችን ለማሳመን ለምን አልሞከሩም? ያልተስማማባቸው ዋነኛ ጉዳዮችስ ምን ምን ነበሩ?ጄኔራል ኦያይ፡- ስለ ምርመራና ስለማጣራት ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ስለተሰጠ ሥልጣን፣ የጦር ኃይሉን ስለ ማዋሀድ፣ እንዲሁም የአስተዳደሩን ጉዳይ በተመለከተ የተቀመጠውን ነገር አልወደዱትም፡፡ በእሳቸው እምነት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ብዙ ሥልጣን ነው የተሰጣቸው፡፡ የኢጋድ መሪዎች የቦትስዋናን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ተጠቅመው ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ነበር ፍላጎታቸው፡፡ ከዘያ በኋላ የኢጋድ መሪዎቹ ስምምነት አስፈርመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ እዚያው ቆሞ ቀረ፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ በተፈረመ በሦስት ወራት ውስጥ በጁባ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ምንም ተግባራዊ የተደረገ አንቀጽ አልነበረም፡፡ የእርስ በርስ መገዳደሉ ቀጠለ፡፡ ዛሬም ድረስ ችግሩ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ሪፖርተር፡- ተኩስ የተጀመረው በጦር ኃይሉና በማቻር ጠባቂዎች መካከል እንደሆነ ነበር የተዘገበው፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?ጄኔራል ኦያይ፡- ተኩስ የተከፈተበት ምክንያትና ዓላማ ዛሬም ድረስ ግልጽ አይደለም፡፡ አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፡፡ በእኔ እምነት ውጊያው የተካሄደው በበላይ ትዕዛዝ ነበር፡፡ ሳልቫ ኪር ራሳቸው ያደረጉት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?ጄኔራል ኦያይ፡- ስምምነቱ ውድቅ ሆኗል፡፡ ዛሬ ስምምነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ውጊያ ከተከፈተ በኋላ ዶ/ር ሪክ ማቻርን ለመያዝ ሲፈልጉ ነበር፡፡ አላገኙዋቸውም፡፡ አምልጠው ወጥተዋል፡፡ አሁን በመላ አገሪቱ የእርስ በርስ ግጭት ነው ያለው፡፡ በተለይ ሳልቫ ኪር ከመጡበት ጎሳ የተደራጁ ሚሊሻዎች ሌሎች ጎሳዎችን እያሰቃዩና እየገደሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ያለው እያንዳንዱ ጎሳ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል የራሱ ሚሊሻ በማደራጀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡በአጠቃላይ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ እየተበታተነ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ ከአገር ወጥተዋል፡፡ ወደ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ኮንጎ እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ወደ ተራሮች ወጥተው የሚኖሩ ሲሆኑ፣ የላይኛው ናይል ሕዝቦች ደግሞ ነውያ በተባለ ረግረጋማ ቦታ እየኖሩ ነው፡፡ የተቀሩት በተመድ የስደተኞች ካምፕ ገብተው ይኖራሉ፡፡ በጁባ ብቻ ሁለት ትላልቅ ካምፖች አሉ፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙት አሥር ክልሎች መካከል አምስቱ በተመድ ወታደራዊ ጥበቃ የሚያገኙ ናቸው፡፡ የተቀሩት የአገሪቱ ሕዝቦች ተስፋ ቆርጠው ሁኔታዎችን የሚጠባበቁ ናቸው፡፡ ለተለያዩ ሰብዓዊ ጥቃቶች ማለትም ለእስር፣ ለአስገድዶ መደፈር፣ ለግድያና ለረሃብ የተጋለጡ ናቸው፡፡ለዚህም ነው ደቡብ ሱዳን በመሰለ ሀብታም አገርና ባለ ለም መሬት ሳልቫ ኪር ረሃብን ያወጁት፡፡ ድርቁ ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ሰው ሠራሽ ነው፡፡ ምክንያም ሕዝቡ በዚህ ሁኔታ ምን ማብቀልና ራሱን መመገብ ይችላል? አብዛኛው ሕዝብ በካምፕ ውስጥ ታጉሮ እየዋለ እንዴት ይሠራል? ወጣቶቹ ደግሞ በየፊናቸው በየራሳቸው ጎሳ እየተደራጁ፣ ራሳቸውን እያስታጠቁና እርስ በርሳቸው እየተላለቁ ነው የሚገኙት፡፡ሪፖርተር፡- አሁን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል [ባለፈው ሳምንት]፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በምን ጉዳይ እንዲመክሩ ይጠብቃሉ?ጄኔራል ኦያይ፡- ፕሬዚዳን ሳልቫ ኪር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግሥት ውሸት ለማውራት ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውን እውነት እንዲያውቁ ነው፡፡ ጠንከር ባለ መንገድ በስምምነቱ መሠረት የታወጀው ብሔራዊ ዕርቅ በገለልተኛ አካል እንዲከናወን ሳልቫ ኪር እንዲፈቅዱ ወይም ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ነው፡፡ ብሔራዊ ውይይቱ ግን በራሳቸው መሪነት ሊካሄድ አይችልም፡፡ ሌላ ገለልተኛ አካል ሊመራው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ኢጋድ፣ የአፍሪካ ኅብረት ወይም ደግሞ ተመድ ሊመሩት ይችላሉ፡፡ ሳልቫ ኪር ግን በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ውይይቱን ጠልፈውታል፡፡ ኮሚቴዎችና አዘጋጆች ሁሉ ወደነሱ የሚያደሉ ናቸው፡፡ሪፖርተር፡- የእርስ በእርስ ግጭቱ ብሔራዊ ጦሩ ውስም አለ?ጄኔራል ኦያይ፡- በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ጦር የሚባል የለም፡፡ የደቡብ ሱዳን ጦር ከአንድ ጎሳ የተውጣጣ ሲሆን እሱም የፕሬዚዳንቱ ጎሳ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ውስጥ ምንም የመከፋፈል ችግር የለም፡፡ ችግሩ ሌሎች ላይ ጥቃት እያደረሱ በመሆናቸው እያንዳንዱ ጎሳ ራሱን ለመከላከል መታጠቁ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሚሊሻ ሁሉም ነገር በእጁ ስለሆነ ጠንካራ ነው፡፡ ሌሎች ግን አቅም የላቸውም፡፡ በተለይ የዶ/ር ሪክ ማቻር ጦር ጠንካራና ላመነበት ዓላማ የቆመ ቢሆንም፣ የትጥቅና ስንቅ ችግር አለበት፡፡ሪፖርተር፡- አሁን ያስቀመጡት የብሔራዊ ዕርቅ ቅድመ ሁኔታ በፕሬዚዳንቱ ተቀባይነት ካላገኘ ወደፊት ምን ይሆናል?ጄኔራል ኦያይ፡- ምንም የሰላም ተስፋ አይኖርም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ካልወረዱ አልያም ስምምነቱ (ብሔራዊ እርቅ) ካልተተገበረ ምንም ተስፋ የለም፡፡ ምናልባትም የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ተባብረው ይህንን ለሰላም ያልተዘጋጀ አምባገነን ፕሬዚዳንት በጉልበት ከሥልጣን ለማውረድ ይችላሉ፡፡ ይኼ እንዳይሆን ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል በተመድ የተረቀቀው ማዕቀብ ተግባራዊ የሚሆን ይመስለዎታል?ጄኔራል ኦያይ፡- አይመስለኝም፡፡ ማዕቀብ ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሒደት ነው፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ሆኖ አይታየኝም፡፡ የኢጋድ መሪዎች ናቸው ጫና መፍጠር ያለባቸው፡፡ ከሥልጣን እንዲወርዱ ወይም ቅድመ ሁኔታውን እንዲቀበሉ ማድረግ አለባቸው፡፡ እስካሁን ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ወደ ጁባ ይላካል የተባለው የቀጣናው ተጠባባቂ ኃይል እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ሳልቫ ኪር ስላልፈለጉት ነው ይህ ያልሆነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ገለልተኛ ኃይል በሌለበት እንዴት ሆኖ ነው የብሔራዊ ዕርቅ መድረክ የሚዘጋጀው?ሪፖርተር፡- ኢጋድ ውስጥ ያሉ አደራዳሪ አገሮች ገለልተኛ ናቸው ብለው ያስባሉ? በደቡብ ሱዳን ላይስ የጋራ አቋም አላቸው ብለው ያምናሉ?ጄኔራል ኦያይ፡- የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን ላይ ምንም የጋራ አቋም የላቸውም፡፡ እያንዳንዱ አገር ከራሱ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ነው እየሠራ ያለው፡፡ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ሪፖርተር፡- በመጨረሻ ስለደቡብ ሱዳን ዕጣ ፈንታ የሚታየዎትን ቢነግሩን?ጄኔራል ኦያይ፡- በአሁን ወቅት በደቡብ ሱዳን ውስጥ የአንድ መንግሥት አልባ አገር መለኪያዎች በሙሉ እየታዩ ናቸው፡፡ እናም ያ ጨርሶ እውነት ከመሆኑ በፊት የቀጣናው አገሮች መሪዎች በተለይ ኢትዮጵያ በሳልቫ ኪር ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ነው ጥሪዬን የማቀርበው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ሰላም እንዳለ አስመስለው ያውሩ እንጂ በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ሳልቫ ኪር አንድም ለብሔራዊ ዕርቁ መርሆች ተገዥ እንዲሆኑ፣ አልያም በገዛ ራሳቸው ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡