ህጻናት በመጀመሪያዎቹ እድሜያቸው ወራት ላይ ከአባቶቻቸው ጋር የሚኖራቸው ቆይታ ለአእምሯቸው ጠቀሜታ እንዳለው አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።
በእንግሊዝ በሚገኙት የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ፣ ኪንግስ ኮሌጅ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በጋራ የሰሩት ጥናት እንደሚያመለክተው፥ በመጀመሪዎቹ ወራት አከባታቸው ጋር ረጀም ጊዜን የሚያሳልፉ እና የሚጫወቱ ህጻናት የአእምሯቸው የመገንዘብ አቅም ከአባታቸው ጋር ከማይጫወቱት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።
ጥናቱ 128 አባቶችን የተመለከተ ሲሆን፥ በጥናቱም የቤተሰቡን ገቢ፣ እድሜ፣ ቤተሰብ ከልጆቹ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ወላጆች ልጆቻቸውን ገና በ3 ወራቸው ያለ አሻንጉሊት ማጫወትን እንዲሁም በ2 ዓመታቸው መጽሃፍ ሲያነቡላቸው አይቷል።
በዚህም በአባት እና በልጅ መካከል ያለው የግንኙነት መጠን በልጆቹ አእምሮ ላይ በጎ ጎን እንዳለው መለየታቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።
ከልጆቻቸው ጋር ማሳለፍ እና መጫወትን በበጎ ጎን የሚለከቱ አባቶች የልጃቸው ሴትም ትሁን ወንድ አእምሯቸው ጥሩ የሚባል የመገንዘብ አቅም እንዲኖረው ያደርጋሉ ብለዋል።
በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ፕሮፌሰር ፓውል ራምቻንዲ፥ የህጻን ልጅ እና የአባት ግንኙነት ገና ከ3 ወር ቢጀምር እንኳ የአእምሯቸው ነገሮችን የመገንዘብ አቅም በሁለት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያሳያል ይላሉ።
የአባት እና የልጅ ግንኙነት በልጆቹ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።
በኪንግስ ኮሌጅ የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር ባሄሽታ ሴትና፥ በጥናቱ የተገኘው ውጤት አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ መልካም መሆኑን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
ምንጭ፦ www.upi.com