- 4,000 ስደተኞች ብቻ የጉዞ ሰነድ ወስደዋል
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በአገሪቱ በሕገወጥ መንገድ ኑሯቸውን የሚገፉ የውጭ ዜጎችን በተመለከተ ያወጣውን የምሕረት አዋጅ፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትጵያውያን እየተጠቀሙበት ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡ በተለይ በቅርቡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞችን በተመለከተ ያወጣውን አዋጅ አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ከመጋቢት 21 እስከ ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ያለምንም ቅጣትና መዋከብ፣ እንዲሁም የጣት አሻራ መስጠት ሳያፈልጋቸው በተቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ እንዲወጡ የአገሪቱ መንግሥት የምሕረት አዋጅ አውጥቷል፡፡
‹‹በሕገወጥ መንገድ ከሚኖሩ ስደተኞች ነፃ የሆነች ሳዑዲ ዓረቢያን ማየት›› የሚል ዓላማ ያለው አዲሱ አዋጅ፣ ስደተኞቹ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የኢምግሬሽን ጽሕፈት ቤቶች የመውጫ ቪዛ ወድያውኑ እንዲያገኙ፣ ያለምንም ቅጣት በራሳቸው ወጪ ገንዘብና ንብረታቸውን ይዘው በፈቃደኝነት አገሪቱን እንዲለቁ፣ እንዲሁም የጉዞ ሰነዶችን ከሚመለከታቸው አካላት እንዲገኙ የሚያደርግ ነው፡፡
በምሕረት አዋጁ መሠረት በተሰጠው የግዜ ገደብ ውስጥ አገሪቱን ለቀው የሚወጡ የውጭ ዜጎች እንደ በፊቱ የጣት አሻራ መስጠት የማይጠበቅባቸው ሲሆን፣ ይኼም በሕጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተመልሰው ለመሄድ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን የሚገልጹት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ እንደሚሉት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ የግብረ ኃይሉ የልዑካን ቡድንም ከመጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሳዑዲ ዓረቢያ የአራት ቀናት ቆይታ አድርጎ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየቱ ተገልጿል፡፡ አቶ መለስ እንዳሉት፣ የልዑካን ቡድኑ በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ዜጎች የምሕረት አዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስቧል፡፡ የመውጫ ቪዛ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት አማካይነት ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶች እንዲከፈቱም ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሪያድና በጅዳ ያሉት ኤምባሲዎቹን ጨምሮ በሌሎች የተከፈቱ ጽሕፈት ቤቶቹ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑንና በአካባቢው ከሚገኙ የኮሙዩኒቲ፣ የልማት ማኅበራትና ሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ሰፋ ያለ ምክክር ማድረጉን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው እንደሚገመት፣ እስካሁን አራት ሺሕ ስደተኞች ብቻ የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውንና 200 ያህሉ ብቻ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ቁጥር ወደ አገር ቤት መመለስ ከሚገባቸው አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው፤›› ያሉት አቶ መለስ፣ በአካባቢው በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎች የምሕረት አዋጁን በመጠቀም ያፈሩትን ንብረትና ገንዘብ ይዘው በሰላም ወደ አገራቸው እንዲገቡ የተሰጣቸው ዕድል እንዳያመልጣቸው በማለት፣ መንግሥት ከፍተኛ ሥጋት አድሮበታል ብለዋል፡፡
‹‹ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ከአሳሳቢነትም ወደ አስከፊ ችግር ሊሸጋገር ይችላል፤›› ሲሉ የሥጋቱን ከፍታ ጠቁመዋል፡፡
ጊዜ ገደቡ ሊያበቃ ከ70 የማይበልጡ ቀናት የቀረ መሆኑን፣ የተገመተውን ያህል ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ዜጎች በዕድሉ ተጠቃሚ አልሆኑም የሚለው ደግሞ አሳሳቢነቱን ከፍ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
አቶ መለስ እንደሚሉት፣ በአካባቢው የሚገኙ ደላሎች ሳዑዲ ዓረቢያ ያወጣችው አዋጅ ‹‹ተግባራዊ አይደረግም› በማለት እያስወሩ በመሆናቸው ስደተኛ ዜጎች እየተዘናጉ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ጉዳዩን በፅሞና መከታተልና ሕጉን በአግባቡ ማወቅ እንዳለባቸው ቃል አቀባዩ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ በ2013 ሳዑዲ ዓረቢያ ባወጣችው ተመሳሳይ አዋጅ መሠረት፣ በተለይ ኢትዮጵያውያኑ ተጠቃሚ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ያጋጠመው እንግልትና ስቃይ የሚታወስ ነው፡፡ ጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅም በተወሰደው ዕርምጃ በግዴታ ከ150 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ፣ 2.5 ሚሊዮን በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ባዶ እጃቸውን መባረራቸው አይዘነጋም፡፡
የምሕረት አዋጁን በማያስከብሩ ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ውሳኔዎች በሕጉ ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በፀጥታ ኃይሎች የቤት ለቤት አሰሳ ይካሄዳል፣ የሚያዙ በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል፣ ከስምንት ወራት በፊት የወጣው የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተግባራዊ ይደረግባቸዋል፡፡ እንዲሁም የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በሕገወጥ መንገድ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ከለላ የሰጠ ወይም የቀጠረ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ድርጅት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን አዋጁ ይደነግጋል፡፡