በአፍሪካ በትቦ አማካኝነት የሚቀርን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ከማግኘት ይልቅ ሞባይል ስልክ መያዝ እንደሚቀል ጥናት አመልክቷል።ጥናቱ በአፍሪካ ከሚኖሩ ህዝቦች ውስጥ 63 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የቧንቧ ውሃን የሚያገኙ ሲሆን፥ 93 በመቶው የአፍሪካ ህዝብ ግን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ነው ይላል። አፍሮባሮሜትር በሚባል ተቋም የተሰራው ጥናት በ35 የአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደረገ ሲሆን፥ ቁጥራቸው 50 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎችም ፊት ለፊት ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።
በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሰዎች በቀላሉ በሞባይል ስልካቸው መነጋጋር ይችላሉ፤ ነገር ግን በዚያው ልክ መብራት አብርቶ መጠቀም እና ውሃን ከቧንቧ መቅዳት የማይታሰብ ነው ይላሉ የጥናት ቡድኑ መሪ ዋይኔ ሚቶላህ።
ከአስርት ዓመታት ወዲህ በአህጉሪቱ መሻሻሎች ቢታዩም፤ ለውጡ ግን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም የሚሉት ሚቶላህ፥ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ግን ከምንግዜውም በበለጠ እየጨመረ ነው ይላሉ።
አፍሮባሮሜትር ከ18 ሀገራት ያሰባሰበው መረጃ ላይ በመመስረት በሀገራቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ምን ያክል የመሰረተ ልማቶች መስፋፋት አለ የሚለውን ተመልክቷል።በዚህም በአፍሪካ ከፍተኛ እድገትን እያስመዘገበ የሚገኘው የሞባይል ስልክ አገልግሎት እና ተጠቃሚ ነው የሚለውን አስቀምጧል።
በ10 ዓመት ውስጥም የሞባይል ስልክ ተደራሽነት 23 በመቶ እድገት ሲያሳይ፤ መንገድ 16 በመቶ እንዲሁም የመጠጥ ምሃ እና ኤሌክትሪክሲቲ 14 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጥናቱ ሀገራት ቅድሚያ መስጠት ሲገባቸው ያልሰጧቸውን ነገሮች ለይቶ ያስቀመጠ ነው ይላሉ የጥናት ቡድኑ መሪ።መንግስታት ከዚህ በመነሳትም ዜጎቻቸው በቅድሚያ ምን አይነት መሰረተ ልማት ማግኘት አለባቸው የሚለውን ለመወሰን ያስችላቸዋል ብለዋል።ምንጭ፦ edition.cnn.com