በአዲስ አበባ ከተማ የፍሳሽ መስመር ፍትሻ እና የማስከፈት አገልግሎት ለማግኘት ሰድስት ወራትን መጠበቅ ግዴታ ሆኗል።
ጄት ማስተር በተሽከርካሪ በመታገዝ እስከ 35 ሜትር የተዘጋ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመርን ፈትሾ መክፈት የሚያስችል መሳሪያ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ ላለፉት በርካታ አመታት ሁለት የጄት ማስተር የተባለ መፈተሻ ብቻ ይዛ የከተማውን ህዝብ ስታገለግል ቆይታለች።
በአሁኑ ወቅትም አንዱ ተበላሽቶ አንዱ ብቻ ነው አገልግሎት እየሰጠ ያለው።
በዚህ ምክንያት የፍሳሻ ማስወገድ እና ፍትሻ የሚፈለጉ ተገልጋዮች ብዙ ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸውን የሚናገሩ ሲሆን፥ ችግሩ በአፋጣኝ እንዲፈታላቸውም ይጠይቃሉ።
በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የፍሳሽ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ባህረ በላይ፥ በከተማው አገልግሎት የሚሰጥ ጄት ማስተር ተብሎ የሚጠራው የፍሳሽ መስመር መፈተሻ መሳሪያ ችግር መኖሩ በጥናት መረጋገጡን ይናገራሉ።
ሆኖም ግን መሳሪያውን ለመግዛት በየጊዜው በሚወጣ የግዢ ጨረታ መጓተት ምክንያት በተጨማሪ መሳሪያ በመታገዘ ፈጣን አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜም መፈተሻው አንድ ብቻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለበርካታ ወራት ክፍያ ፈጽመው ወረፋ የሚጠባበቁ ደንበኞች እየበዙ መሄዳቸው እውነት መሆኑንም አቶ ባህረ ያብራራሉ።
ችገሩ መኖሩን ያረጋገጡት አቶ ባህረ፥ በአፋጣኘ አገልግሎቱ ለሚያስፈልጋቸው የህበረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ይሰጣል ሲሉም ተናግረዋል።
ሃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ አፋጣኘ የተባለው አገልግሎትን ለማግኘት አንድ ወር መጠበቅ ግዴታ ነው።
በአሁን ወቀት ችግሩ በከተማ ደረጃ ከመስፋቱ ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ ተጨማሪ የተዘጋ መስመር መፈተሻና መክፈቻ መሳሪያው ግዢ ለመፈጸም መዘጋጀቱ ተነግሯል።
ለመሳሪያ ግዢም በአሁን ወቅት ጨረታ ሂደት ተከናውኖ ቴክኒካል ምዘና እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
አዲስ የሚገዛው የመፈተሻ መሳሪያ ቀደም ብሎ ከነበረው 35 ሜትር በተሻለ እስከ 150 ሜትር መፈተሽ እንደሚችልም አቶ ባህረ አስታውቀዋል።
ጄት ማስተር ተብሎ የሚጠራው የፍሳሽ መስመር መፈተሻ መሳሪያ በተያዘው አመት ተገዝቶ በቀጣይ ዓመት ከመስከረም ወር ጀምሮ አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።