በገጠር የሚኖሩ 51 በመቶ ኢትዮጵያውያን ንፁህ ውኃ እንደማያገኙ ወተር ኤድ ‹‹ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ወርልድስ ወተር 2017›› በሚል ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ በገጠር የንፁህ ውኃ ተደራሽነት ችግር ባለባቸው ቀዳሚ አሥር አገሮችና በንፁህ ውኃ ችግር የሚሰቃየውን የኅብረተሰብ ክፍል በመቶኛና በቁጥር ለይቶ አስቀምጧል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ፣ በቁጥር ሲሰላ 40.9 ሚሊዮን የንፁህ ውኃ ችግር ያለባቸው የገጠር ነዋሪዎች መገኛ በመሆን ከህንድ፣ ከቻይናና ከናይጄሪያ ቀጥላ ከቀዳሚዎቹ ችግር ካለባቸው አገሮች በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በመቶኛ ሲሰላ ደግሞ በሪፖርቱ ከተካተቱት አገሮች በ15ኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች፡፡
በንፁህ ውኃ ተደራሽነት ረገድ ከመጨረሻዎቹ 10 አገሮች ተርታ የተሰለፈችው አገሪቱ ግን ትልቅ መሻሻልን እያሳየች መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ እ.ኤ.አ. 2000 በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የነበረው የንፁህ ውኃ ተደራሽነት 18.9 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ 48.6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል፡፡ ይህም ባለፉት 15 ዓመታት በገጠር የነበረው የንፁህ ውኃ ተደራሽነት በ29.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የሚያመለክት ነው፡፡
በዚህ መሠረትም አገሪቱ የገጠር የንፁህ ውኃ አቅርቦታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ካሻሻሉ 10 የዓለም አገሮች ውስጥ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ፓራጓይ፣ ማላዊ፣ ሌዎ ፒፕልስና ካምቦዲያ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለረሃብ የዳረገው ኤልኒኖ እስከሚመጣው ዓመት አጋማሽ ድረስ ከ5.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎችን ለረሃብ እንደሚዳርግም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ አገሪቱ በከፍተኛ መጠን ለአየር ጠባይ ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ 20 አገሮች መካከል ትመደባለች፡፡ የአየር ጠባይ ለውጥን ለመቋቋም ከሚቸገሩ 23 አገሮች መካከልም አንዷ መሆኗን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
81 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ በገጠር እንደሚኖርና መተዳደሪያው ግብርና መሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁንና ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ግብርና የተመሠረተው በዝናብ ላይ ነው፡፡ በዝናብ ላይ ለተመሠረተው የአገሪቱ ግብርና ደግሞ የአየር ጠባይ ለውጥ ትልቅ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ ግብርና መር ለሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ፈተና ሲሆን፣ የውኃ ተደራሽነትን ከፍ በማድረግ በዝናብ እጥረት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መቆጣጠር እንደሚቻል ይታመናል፡፡
ከውኃ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ለውጥ ማስመዝገብ ቢቻልም አሁንም በርካታ አገራት ከፍተኛ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር አለባቸው፡፡ ችግሩ በይበልጥ ጐልቶ የሚታየውም በአፍሪካ ነው፡፡
በአንጎላ ገጠራማ አካባቢዎች 71.8 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች ንፁህ ውኃ አያገኙም፡፡ ይህም አንጎላን ከፍተኛ የንፁህ ውኃ ችግር ካለባቸው የዓለም አገሮች ተርታ የመጀመሪያዋ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ኮንጐ 68.8 በመቶ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ 68.5 በመቶ በመሆን በተከታታይ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል፡፡