ቴዲ አፍሮ ግን ፣ ነገስታቱን እና ባለሟሎቻቸውን ከሚያሞካሽበት ሰዓት እና ጊዜያቱ ላይ ትንሽ ቀንሶ ለአብዛኛው እና ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወገናዊነቱን የሚገልጽበት ጊዜ ቢኖረው ምን ይለዋል?
አዎ ፣ በቀደሙት ዘመናት የተሰሩ ጥቂት መልካም ታሪኮች ነበሩን። ሆኖም ግን ፣ ባለብዙ ብሄር ፣ ብሄረሰብ ፣ ሃይማኖቶች ፣ ቋንቋዎች ፣ ባህሎች እና የመሳሰሉ እሴቶች በእኩልነት የማይስተናገዱባት የነበረችው ኢትዮዽያ ለአብዛኛው ህዝብ የፍዳ እና የማይመች ህይወት መግፊያ ሆና መኖሯን ሳይሰማ የቀረ አይመስለኝም። ይሄንንም ስል ፣ በራሱ ሞያ አካባቢ የነበሩትን ብርቅዬ የኪነጥበብ ሰዎችን እና ታላላቅ አትሌቶችንም ህይወት ጨምሮ ፣ ከእጅ ወደ አፍ ኖሮ ደሃ ሆኖ መሞት በጣም የተለመደ እንደነበርም በማሰብ ነው።
የኪነጥበብ ሰው ሆኖ የናጠጠ ሃብታም መሆን (እንዲህ እንደዛሬው) የማይታሰብበት ዘመናት ነበሩን። ጥላሁን ገሰሰ የሚባል በርካታ ትውልድ ያደነቀው እና ያከበረው ድምጻዊ ወይም መንግስቱ ወርቁ የሚባል የኳስ ንጉስ/ጠቢብ ወይም አበበ ቢቂላ የሚባል በዓለም የገነነ ስም ይዞ የረባ ኑሮ አለመኖር የሚቻልባት ሃገር ነበረችን። አንደነገሩ የሆነ ድርቅ ተከሰተ ማለትም ፣ በሚሊዮን ካልሆነ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ህይወት እንደቅጠል የሚረግፉባቸው ዘመናትም ነበሩ ፣ የቴዲን ቀልብ ሰቅዘው የያዙት የቀደሙ መሪዎች ዘመናት።
እንዲሁ መሰረት በሌለው መንገድ እራስን/ሃገርን መካብ እና በከንቱ በመመጻደቅ እውነቱን መቀየር አይቻልም። ችግሩን ማመን እና ለመፍትሄመንቀሳቀሱ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል ፤ ባለፉት 25 ዓመታት ገደማ እንዳየንው።
ሰሞኑን ያወጣው ሙዚቃ ላይም እንዲሁ በዘልማድ የሚባል እና አንዳች እውነት የሌለውን አባባል ተጠቅሟል።
የኢትዮዽያ ባንዲራ እንዴት ሆኖ ሰማይ ላይ እንደታየ አልገባኝም። አንድ አንዶች ፣ ቀስተዳመናን አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ የኢትዮዽያ ባንዲራ ቀለም ነው ያለው በማለት የሚያወሩትን አፈ-ታሪክ ይዞ ከሆነ በጣም ተሳስቷል። ቀስተ-ደመና ሰባት ዓይነት ቀለማትን የያዘ እና በዚህ ዘመን ደግሞ ግብረሰዶማውያን እንደ መለያቸው የሚታወቁበት ነው። ለነገሩ ፣ እግዜርም ቀስተደመናን የፈጠረው ከኢትዮዽያ ባንዲራ ቀለም አይቶ ነው ማለትም ይቻል ይሆናል ፣ ምንም ቢባል “ለምን?” ብለው የማይጠይቁ ሰዎች በመኖራቸው።
ለማንኛዉም ፣ ከብዙ ወሬ/እንጉርጉሮ ጥቂት በተግባር የተገለጸ የሃገር ፍቅር ይበልጣል። ከበርካታ የህብረተሰብ ክፍል ጋር እልህ መጋባትም የሚያዋጣ አይመስለኝም እና ትንሽ ረጋ ቢል ይጠቅመዋል እላለሁ።
begashaw kebede