የአዳምና የሔዋንን ዝነኛ ታሪክ፣ እንደገና አነበብኩት። እንዲህ አጭር ነው እንዴ? አንድ ገፅ፣… ቢበዛ ደግሞ ሁለት ገፅ ቢሆን ነው። ግን፣ እንደ እጥረቱ ሳይሆን፣ እንደ ዝናው፣ ከባድ መልዕክትን ያቀፈ፣ ሳያንዛዛ ትልቅ ቁምነገርን የሚያስጨብጥ ልዩ ትረካ ቢሆንስ? ለዚያውም፣ አይን ከፋች ቁምነገር!
ትረካው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ፣ የአዳምና የሔዋን ነገረ ስራ፣ ግር ያሰኛል። “ነፍስ ያወቁ” ሕፃናት ይመስላሉ። ማሰብ የለ፤ መስራት የለ፣ ፍቅር የለ…። መብላትና መጠጣት ብቻ! ከዚያም በየፊናቸው መተኛት! እርቃናቸውን ነው የሚውሉት። ግን ምንም! እርስ በርስ በአድናቆት የመተያየትና በፍቅር የመሳሳብ ቅንጣት ምልክት የለም። እንኳን በእውናቸው በሕልማቸውም አይመጣላቸውም። በማግስቱ ከእንቅልፍ ሲነቁም፣ ያው እንደ ትናንቱ መብላት ነው። ለምለሙ የእርሻ ማሳ ውስጥ፣ ሁሉም ነገር ሙሉ፣ ሁሉም ነገር ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃቸዋል። እየጨለፉ መጠጣት፤ ፍሬ እየሸመጠጡ መብላት! እንዲበሉ ተነግሯቸዋል። እነሱም፣ የተፈቀደላቸውን ብቻ ያደርጋሉ። የተነገራቸውን ሁሉ ያምናሉ። የታዘዙትን ደግሞ ቢሞቱ አይጥሱም። የተከለከሉትንም ጫፉን ‘እንዲች’ አይነኩም። ወላጅን የማያስቸግሩ፣ ሞግዚትን እረፍት የማይነሱ ሕፃናት ይመስላሉ – አዳምና ሔዋን። ይመስላሉ ከማለት ይልቅ፤ ይመስሉ ነበር ብንል ይሻላል። መቼም፣ በወላጅ እንክብካቤ ሁሉም ነገር ተሟልቶ የተትረፈረፈበት ገነት ውስጥ፣ ዘላለም በሕፃንነት መኖር አይቻልም። ቢቻልስ፣ ማን እሺ ብሎ ይቀመጣል?!
በእርግጥ፣ ያለ ሃሳብ መኖር፣ ያለ ስራ መብላት ለጊዜው ተስማሚ፣ ላይ ላዩን አስደሳች ይመስላል እንጂ፤ ብዙም አያዛልቅም። ጣጣውም አያፈናፍንም። እድሜ ልክ የወላጅ ጥገኛ፣ ወይም የመንግስት ጥገኛ ተደጓሚ ከመሆን ጋርም ይመሳሰላል። በኑሮህ ጥገኛ እስከሆንክ ድረስ፣ የተነገረህን ተረት ማመን እንጂ ሌላ ነገር መጠየቅና ማሰብ፣ የታዘዝከውን ብቻ ማድረግ እንጂ፣ ሌላ ነገር መፈለግና መመኘት፣ መሞከርና ራስህን መምራት አይቻልም – ካልተፈቀደልህ በቀር። ደግሞም፣ አይፈቀድልህም። ትዕዛዝና ክልከላ አይቀሬ ነው።
እንደ ሕፃን ብዙ ነገር ሳያውቁ በምድረ ገነት ያለ ሃሳብ እየበሉ የሚኖሩት አዳምና ሔዋንም፣ ክልከላና ትዕዛዝ ነበረባቸው። በውቧ ገነት እምብርት፣ በለምለሙ የእርሻ ማሳ ውስጥ፣ ከአትክልቶቹ መሃል የበቀለችውን ዛፍ እንዳይነኩ ታዘዋል፤ ፍሬዋን እንዳይበሉ ተከልክለዋል።
ድርሽ እንዳትሉ ተብለው ቢታዘዙም፣ ንክች እንዳታደርጉ ተብለው ቢታዘዙም፣ ዘላለም ከዛፏ እንደራቁ መኖር፣ ፍሬዋን እያዩ እንዳላዩ መሆን አልቻሉም። በሔዋን መሪነት፣ ማኸለኛዋን ዛፍ ነካክተው፣ ፍሬዋን ተቃመሱ። ይሄኔ፣ ዓይናቸው በራ። እውኑ ዓለም፣ እንደ አዲስ በግላጭ ፍንትው ብሎ ታያቸው፤ ከእውነታ ጋር ተዋወቁ። ይህም ብቻ አይደለም። “ጥሩና መጥፎን”፣ “መልካምና ክፉን” መለየት… (ማለትም፣ ማመዛዘንና መምረጥ) ጀመሩ።
ድንቅ ነው። ግን ከችግር አላመለጡም። ከዚያች የእውቀት የጥበብ ዛፍ ላይ፣… የእውነትን ፍሬ ሸምጥጠው፣ የመልካምነትን ፍሬ ቆርጠው እንዳይበሉ ተከልክለዋል።
ምን አይነት ፍሬ ቢሆን ነው? ፍሬውን መብላት የተከለከሉትስ ለምንድነው? እኒሁና፣ ሁለቱ ጉደኛ ጥያቄዎች! እንዲህ አይነት ሁለት ጥያቄዎች በሰው ዘንድ የተፈጠሩ ጊዜ፣… ሰው አእምሮውን መጠቀም የጀመረ ጊዜ፣… “ምን?… ለምን?” እያለ መጠየቅና ማሰላሰል የጀመረ ጊዜ… አብዮት ይጠነሰሳል። ጉድ ይፍለቀለቃል።
“ምን?” ወይም “ምንድነው?” ብሎ ሲጠይቅ፣ እውኑን አለም ለማስተዋልና ለማወቅ፣ እውነትንና ሐሰትን ለመለየት፣ አዲስ ብርሃን ይለኩሳል።
“ለምን?” ወይም “ለምንድነው?” ብሎ ሲጠይቅ ደግሞ፣ ጥቅምና ጉዳትን አመዛዝኖ ለመምረጥና ለመወሰን፣ ለክቶና መትሮ አቅጣጫውን ተልሞ ለመጓዝ አዲስ መንገድ ይጠርጋል።
የሁለቱ ጥያቄዎች መዘዝ ቀላል አይደለም። ሰው፣ በራሱ አእምሮ ለመመራት ሲነሳ ነፃነትን ለመጨበጥ ይንጠራራል። ራሱን በራሱ ለመግዛትም ሲል ሃላፊነትን ለመውሰድ፣ ትከሻውን ያደላድላል። ያኔ፣… ነፃነትን ወደሚያጎናፅፍና ሃላፊነትን ወደሚጠይቅ ጎዳና ዘው ብሎ ይገባል።
የዚህ ጎዳና ፈር-ቀዳጅና የመጀመሪያ ተጓዥ፣ ሔዋን ናት። በሔዋን ዘንድ፣… “ምን?”፣… “ለምን?” የሚሉ ጥያቄዎች የተቀሰቀሱበት መነሻ ሰበብ፣ ሊለያይ ይችላል። ጥያቄዎቹ የመነጩት ከሔዋን ሕሊና ቢሆን፣ ወይም ደግሞ ጥያቄዎቹ የተጫሩት በእባብ ቆስቋሽነት ቢሆን፣ አልያም በዛፉ ውበትና ልምላሜ፣ በፍሬው መዓዛና ቅላት ሳቢያ ቢሆን… ልዩነት የለውም። ዋናው ነገር፣ ከተቆሰቆሰችና ከተማረከች በኋላ፣ እንደ ወትሮው አይኗን ጨፍና በዝምታ አለማለፍዋ ነው። ማየትና መመራመር፣ ጥያቄዎችን እያሰላሰሉ ማገናዘብና ማመዛዘን? … ይህንንማ አላደርግም፣ “ያልለመደብኝን! ያልታዘዝኩትን!”… ብላ መተው ትችል ነበር። “ምን?” በሚል ጥያቄ እውነትንና ሃሰትን ለመለየት መሞከር፣ ቀላል ስራ አይደለም። በነፃነት አእምሮዋን ለመጠቀምና ራሷን ችላ እውነታን ለመመርመር፣… ሃላፊነትን እየጨበጠች ነው። “ለምን?” በሚል ጥያቄ አማካኝነት፣ የነገሮችን ጥቅምና ጉዳትን ማመዛዘን፣ አመዛዝናም የሚበጃትን መምረጥና መወሰንም፣ ከባድ ሥራ ነው። በራስ የመመራት ነፃነትን ብቻ ሳይሆን፣ ራስን የመቻል ሃላፊነትን ያሸክማል። ሔዋን፣ ይህንን አልሸሸችም።
እባቡ መጣና ሔዋንን አናገራት። “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” አላት።
እውን እንዳትበሉ ተከልክላችኋል?
ሔዋን፣ ቀጥተኛ መልስ ሰጠች። … “በምድረ-ገነት ካለው የዛፍ ፍሬ ሁሉ እንበላለን። ነገር ግን በምድረ-ገነት መካከል ካለው ዛፍ ግን፣ ፍሬ እንዳንበላና እንዳንነካ እግዚአብሔር ከልክሎናል። ‘እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፤ አትንኩትም’ ብሎናል” አለች።
ምን አይነት ፍሬ ቢሆን ነው? አትብሉ? ጨርሶ አትንኩ?!
“አትሞቱም” በማለት እባብ መለሰ። የዛፍዋንና የፍሬዋን ምንነት ለመግለፅ ሞከረ። ለምን እንዳይበሉ እንደተከለከሉም ተናገረ። “ከዛፏ ፍሬ የበላችሁ ጊዜ፣ ዓይኖቻችሁ እንደሚከፈቱ፣ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንደምትሆኑ፣ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” አለ።
መንቃትና መባነን?… አዋቂና ብልህ መሆን?
ሔዋን፣ የእባብን ንግግር በጭፍን ለመከተል አልተጣደፈችም፤ ፍሬውን ለመሸምጠጥ አልቸኮለችም። ይልቅስ፣ ዛፉን አስተዋለች፤ ፍሬውንም መረመረች። “የዛፉ ፍሬ፣ ጥሩ ምግብ እንደ ሆነ፣ ለዓይንም እንደሚያምር፣ ጥበብ ለመጨበጥም ተመራጭ እንደሆነ ተመለከተች” ይላል ትረካው። እንዲህ፣ የፍሬውን ምንነት አገናዝባ እውነታውን ካረጋገጠች በኋላ፣… ጠቃሚነቱን፣ መልካምነቱንና ማራኪነቱንም አመዛዝና ከተማመነች በኋላ ነው፤ ወደ ምርጫና ውሳኔ ያመራችው። “ከፍሬው ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ”።
በእርግጥም ሔዋን አልተሳሳተችም። ሔዋንና አዳም፣ ያኔውኑ ወደ አዲስ ጎዳና ዘው ብለው ሲገቡ አስቡት። በራሳቸው እውቀትና ውሳኔ ተመርተው፣ ፍሬውን ቀምሰው ሲያጣጥሙ፣ ራሳቸውንና ድንቅ ሰውነታቸውን፣ አለምንና አካባቢያቸውን እንደ አዲስ አወቁ።
“የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ። ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑም አወቁ። የበለስ ቅጠሎችን ሰፍተው፣ ግልድም አደረጉ”። … የመጀመሪያው ልብስ ተሰራ ማለት ነው።
ድሮ ድሮ፣ እራቁታቸውን መሆናቸውን ለማየትም ሆነ ለማሰብ አይችሉም ነበር። ቢያዩ እንኳ ግድ አይሰጣቸውም። ያው እንደ ሌሎቹ እንሰሳት ማለት ነው? እንደ ሌሎች እንስሳት አይደሉም። እንደ ሕፃን ነበሩ ቢባል ይሻላል። የወላጆችን ንግግርና ትዕዛዝ በጭፍን እየተቀበሉ፣ በወላጅ እንክብካቤና መሪነት፣ ያለ ሃሳብ ሲበሉና ሲተኙ የነበሩ ሕፃናት፣… በጉርምስና እድሜ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ ከወላጅ ቁጥጥር ውጭ ሲያፈነግጡና ትዕዛዝ ሲጥሱ፤ ወይም በነፃነትና በራሳቸው ምርጫ ሲጓዙ ይታያችሁ።
በነፃነትና በራስ ምርጫ መራመድ? ይሁን። ግን፣ በማን ቤት? በማን እርሻ? በማን ንብረት ላይ ነው፣ እንደፈቀዳቸው የሚሆኑት? “በገዛ ቤቴ!” ብሎ የሚቆጣ ወላጅ አይታያችሁም። በልጆች የተቆጡ ብዙ ፈረንጆችም፣ “My House, My Rules” ይላሉ። ልጆች፣ የራሳቸው ባልሆነ ቤትና እርሻ ውስጥ፣ እንደፈቃዳቸው የልባቸውን ከፈፀሙ በኋላ፣ ነገሩን ሸፋፍኖ ለመደበቅ ወይም ማመካኛ ለመደርደር የሞክራሉ።
እግዚአብሔር፣ የአዳምን ስም እየጠራ፣ “የት ነህ?” ብሎ ጠየቀ።
አዳምም፣ “ድምፅህን ሰማሁና፣ ዕራቁቴን ስለሆንኩ ፈርቼ ተከለልኩ” ብሎ መለሰ።
“ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህ እንዴ?” አለ እግዚአብሔር።
ለካ፣ እነ አዳም ዕራቁት መሆናቸውን አያውቁም ነበር። እውቀትም፣ ደንታም አልነበራቸውም። የተረትና የብዥታ ዓለም ውስጥ፣ የድንዛዜ ወይም ሃሳብ የለሽ የቡረቃ ኑሮ ውስጥ ነው የነበሩት።
ያንን የእውቀትና የጥበብ ፍሬ ከገመጡ በኋላ ግን፣ ባነኑ!! ዓለሚቱ ድንገት የበራች ያህል፣ ከእንቅልፍ ድንገት የነቁ ያህል፣ ዙሪያ ገባው ሁሉ ደምቆ ተገለጠላቸው። የአዲስ ጎዳና አዲስ ጉዞ ይሉሃል ይሄ ነው።
እውነትንና ሐሰትን ለመለየት የሚያስችል የእውቀትን ፍሬ የበሉ ጊዜ፣… አካባቢያቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም አዩ። ጥሩና መጥፎን ለመለየት የሚያስችል የመልካምነትን ፍሬ ያጣጣሙ እለት፣… መሻሻልን፣ ኑሮ ማሳመርንና ማጣጣምን መረጡ። ወስነውም እንደ አቅሚቲ ለመስራት ተነሱ።
የእውቀትን ፍሬ በልተው ሲያበቁ፣ አይናቸው ተከፍቶ እውነታን መመልከታቸውና መገንዘባቸው፣ ለከንቱ አይደለም። እውነታውን ካዩ በኋላ፣ እንደ ወትሮው እንደ እንሰሳ ወይም እንደ ሕፃን ሆነው ለመቀጠል አልሞከሩም። ያዩትን ነገር በቸልታ አላለፉትም። አመዛዘኑት፣… አዎ፤ ዕራቁት መሆን፣ ጣፋጭ የሚሆንበት ጊዜና ሁኔታ አለ። ዘወትር ከቀን እስከ ማታ ዕራቁት መንገላወድ ግን፣… ጠቃሚ፣ ጥሩ፣ መልካም አይደለም። መልበስን መረጡ። መልበስን ተመኙ። ግን ምኞት ብቻ አይደለም። ለጊዜው፣ የአቅማቸውን ያህል፣ ቅጠል ደርበውና ሰፍተው ለበሱ። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ የመጀመሪያው ፈር-ቀዳጅ የፈጠራ ስኬት፣ ይሄው የልብስ ስራ ሳይሆን አይቀርም።
የእነ ሔዋን ዓለም፣ ተለውጧል።
መለስ ብለን ስናስበው፤… እውነትም፣ ሔዋን ከመነሻው አልተሳሳተችም። በምድረ ገነት መሃል ያለችው ዛፍ ታምራለች። በልምላሜዋ ከምትማርክ ውብ ዛፍ ላይ፣ ተንዠርግገው የሚታዩት ፍሬዎችም፣ ዕፁብ ድንቅ ናቸው። እውነትን ከሐሰት የመለየት ብቃትን የሚያጎናፅፉ፣ “የእውነት – የእውቀት ፍሬዎች” ናቸው።
ጥሩነቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? ጥቅምና ጉዳትን ለማመዛዘን፣ ጥሩና መጥፎን ለመለየት፣ መልካምን ከክፉ ለመምረጥ… አዲስ ችሎታ አዲስ ብቃት አግኝተዋል – እነ ሔዋን። የዛፏ ውብ ፍሬዎች፣… የተግባር መመዘኛ፣ የኑሮ ጣዕም መለኪያ፣ “የመልካምነት ፍሬ”… “የስነምግባር ፍሬ”… ናቸው ማለት እንችላለን።
አዳምና ሔዋን፣ ከእንግዲህ ሕፃናት አይደሉም። እውነትና ሐሰትን፣ ታሪክና ተረት መለየት የሚችሉ አዋቂዎች ሆነዋል። እንደ ድሮ፣ ከወላጅ የሰሙትን ተረት፣ በጥሬው አምነው የሚውጡ አይደሉም። ይህም ብቻ አይደለም። መልካምና ክፉን፣ ስነምግባርና ትዕዛዝን መለየት የሚችሉ ብልሆች ሆነዋል። እንደ ድሮ፣ የወላጅ ትዕዛዝን በጭፍን ተቀብለው፣ “ለምን?” ብለው ሳይጠይቁ የሚታዘዙበት የሕፃንነት እድሜ አልፏል። በሌላ አነጋገር፤ “ለአቅመ ሔዋን”… “ለአቅመ አዳም” ደርሰዋል!
አዎ፣ “ምን?”፣ “ለምን?” በሚሉ ጥያቄዎች ግራ ቀኝ እየተመለከቱ፣ ስለ ፍሬው ምንነትና ፋይዳ፣ እውቀትና ብልሃትን እየገበዩ፣… በአዲስ ብርሃንና በአዲስ መንገድ ጉዞ ጀምረዋል።
እናም፣ ሔዋን አልተሳሳተችም ማለት ነው።
እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “ይሄውና፣ ሰዉ መልካምንና ክፉን በማወቅ በኩል፣ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል”። በወንድ ፆታ የተፃፈ ነገር፣ ለሴት ፆታም ይሰራል እንል የለ? እንዲያውም፣ ሔዋን ከአዳም ቀድማለች፤… እውነትንና ሐሰትን፣ መልካምንና ክፉን በመለየት በኩል፣… የማወቅ ብቃትንና የመምረጥ ብልሃትን በመጎናፀፍ በኩል፣… እንደ አምላክ ሆናለች። “ከእኛ እንደ አንዷ ሆናለች” እንደማለት ነው።
ከዚህ በኋላ ምን ቀረ?
እውነትን በማወቅ፣ መልካምነትን በመምረጥ በኩል፣… እንደ አምላክ ሆነዋል።
በሌላ በኩልስ? ምን የቀረ ነገር አለ?
እለት ተእለት በብሩህ አእምሮ እውነትን እየለዩ የማወቅ፣ እለት ተእለት በቀናው መንገድ መልካምን እየሰሩ የማሳካት ብቃት ተጎናፅፈዋል። የእውነት ብርሃንን መላበስ፣ እንዲሁም ወደ መልካም መንገድ ጎራ ማለት… ድንቅ ስኬቶች ቢሆኑም፣ ብቻቸውን በቂ አይደሉም። እያሰለሱ መላበስና ጎራ ማለት፣ በየአጋጣሚው መጎናፀፍና መጎብኘት፣… ለሰው በቂ አይደለም።
ብሩህ እውነት እና መልካም መንገድ፣… የአጋጣሚ ወይም የዘፈቀደ ክስተት፣… የአዘቦት ወይም የክት ልብስ ሆነው መቅረት የለባቸውም። የእውነት ብርሃንና የመልካምነት መንገድ፣… ከእያንዳንዷ የሰው ሃሳብና ከእለት ተእለት ኑሮ ጋር መዋሃድ ሲችሉ ነው፤ ከምር… ክቡር ሕያውነትን መቀዳጀት የሚቻለው። ከሰብእናቸውና ከኑሯቸው ጋር መዋሃድ አለባቸው። ያኔ የመጎናፀፍና የመጎብኘት ጉዳይ ከመሆን አልፎ፣… ይዋሃዳቸዋል። “የሰዎች የሁልጊዜ ሁለመና” ይሆንላቸዋል – ክቡር ማንነትና ቅዱስ ሕይወት።
ከሰብእናቸው የማይነጠል፣.. የሁልጊዜ ማንነትን፣ የማይናወጥ እኔነትን ይቀዳጃሉ። የእለት ተእለት ሥራና ስኬታቸውም፣ ብልጭ ድርግም ከማለት ተሻግሮ፣ ከቅፅበት እስር ተላቆ፣ በጊዜ ውስጥ እያሰቡ ጊዜ የማይሽረው እውቀትን፣… በጊዜ ውስጥ እየሰሩ፣ ጊዜ የማይገድበው ስኬትን፣… በጊዜ ውስጥ እየኖሩ፣ ጊዜ የማያሳጥረው ታሪክን ይቀዳጃሉ። የዘላለም ሕይወት ባለቤት ይሆናሉ – ለእውነት ቆመው ባለእውቀት፣ ባለጥበብ፣ ባለሙያ፣… በመልካም ፀንተው ባለስኬት፣ ባለፀጋ፣ ባለታሪክ፣… የጀግንነት (ቅዱስ) ማንነትን ገንብተው ባለክብር፣ ባለእኔነት፣ ባለእርካታ… ይሆናሉ። በጥቅሉ፣ ባለግርማ ሞገስ “በዓል” ይሆናሉ። ባለእኔነት፣….. ባለሕይወት ይሆናሉ።
ለዝንተአለም ድንቅ ኑሯቸውን የሚመሰክር፣ ምንጊዜም ከታሪካቸው የማይሰረዝ፣ ዘላለማዊ የስኬት ቅርስና የጀግንነት ማህተምን በእውን ይቀዳጃሉ። እውነትን የመለየትና እውቀትን ከመጨበጥ አልፈው፣ ለእውነት የመቆም ቅንነትንና የእውቀት ፍቅርን ይፈጥራሉ። ከሁለመናቸው የማይገፈፍ፣ የሁልጊዜ ህይወታቸው ይሆናል። ክቡር ዘላለማዊ የእውነትና የእውቀት ፍቅር፣ ክቡር ዘላለማዊ የጀግንነት ታሪክና የስኬት ቅርስ፣… ክቡር ዘላለማዊ ማንነት፣ ማለትም የእኔነት ሞገስና እርካታ፣ ክቡር ዘላለማዊ ሕይወትን መቀዳጀት!
ሔዋንና አዳም፣ ገና እዚህ አልደረሱም። ገና ይቀራቸዋል።
መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ቅልብጭ አድርጎ ኢየሱስ ሲያስተምር፣… እውነትም፣ መንገድም፣ ሕይወትም እኔ ነኝ ብሎ የለ?
ሔዋንና አዳም፣ አይናቸው ተከፍቶ የእውነትን ብርሃን አይተዋል – የእውነትን ፍሬ በልተዋልና። ቀናውንም መንገድ ይዘዋል – የመልካምነትን ፍሬ አጣጥመዋልና። የቀራቸው ነገር፣ ብርሃናማውን እውነት እንዲሁም ቀናውን መንገድ፣ ከማንነታቸው ጋር አዋህደው፣ ዘላለማዊ እኔነትንና ዘላለማዊ ሕይወትን መቀዳጀት ነው። ወደዚህ ያቀኑ ይሆን?
እግዚአብሔር እንዲህ አለ – “ይሄውና፣ ሰዉ መልካምንና ክፉን በማወቅ በኩል፣ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል። አሁንም እጁን ሰንዝሮ ከሕይወት ዛፍ መውሰድና መብላት፣ ለዘላለምም ሕያው መሆን ይችላል” (God said, “See, the man has become like one of us, knowing good and evil. And now, he might reach out his hand and take also from the tree of life, and eat, and live forever”)።
እነ ሔዋን፣ ከምድረ ገነት መዲና፣ ከውቧ የእውቀትና የጥበብ ዛፍ፣ ጣፋጭ የእውነትና የመልካምነት ፍሬ ወስደው በልተዋል። እንደለመዱት፣ አሁንም እጃቸውን ወደ ሌላ ዛፍ ቢሰነዝሩስ? የግርማ ሞገስ ባለቤት ከሆነችውና ከዕፁብ ድንቋ የሕይወት ዛፍ ላይ፣ የዘላለማዊነት ሕያው ፍሬ ወስደው ሊበሉ ይችላሉ።
የሰው ነገር! አንዴ ከባነነ ተጋድሞ አያንቀላፋ! አንዴ ከተነሳበት አርፎ አይቀመጥ! እንደ አእምሮው እጁም አያርፍም! እናም፣ እግዚአብሔር፣ ወሰነ። ሰውን ከዔደን ገነት አስወጣው። ለምን? “ለዘላለም ሕያው ለመሆን ሲል፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋና ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ”! ለምን? “የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ! የሥራ ፍሬውን ይበላ ዘንድ!” ተብሎ ተፅፏል። ይሄ ነው ውሳኔው። ከቤቴ ውጣ! የራስህን ጎጆ ሥራ!
እንግዲህ፣ ሔዋኔ… በራሷ አእምሮ መተማመን፤ በራሷ ምርጫ መመራት፤ የግል ማንነት ባለቤት (የእኔነት እመቤትና ጌታ መሆን) ከፈለገች፤… ይሁንላት። ይቅናት። አዳሜም ከፈለገ ይሁንለት፤ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት። የራሱን ሃሳብ በራሱ እየዳኘ፣ የኑሮው መሪና የሕይወቱ ጌታ ይሁን። ይቅናው። ነገር ግን፣ የራስ ባልሆነ ቤት፣ የራስ ባልሆነ ምድረ ገነት፣ የራስ ባልሆነ ንብረት ላይ አይደለም፣… መሪ እና ጌታ መሆን! በራሱ እውቀትና በራሱ ጥረት፣… መሬትን ማረስና ኑሮውን ማልማት፤ የግል ማንነቱን መገንባትና የራሱን ምድረ ገነት መፍጠር አለበት። “በኑሮ ዘመንህ ሁሉ በጥረትህ ከእርስዋ ትበላለህ” ተብሎ ተወስኗል… ከገዛ ራሱ የእርሻ ማሳ፣ ከገዛ ራሱ የስራ ፍሬ!
እግዚአብሔር ይህንን ውሳኔ ሲናገር፤… አዳም ቅንጣት አቤቱታም ሆነ ማመካኛ አላቀረበም። ሔዋንን አልወቀሰም፤ ለአምላክም ምልጃ አላሰማም። “የድሮ ቀረብኝ” ብሎ የሚያላዝን ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። በቅሬታ የኋሊት እየቃኘና እየቆዘመ ይባዝናል ብላችሁ ከገመታችሁም፣ ነገሩን ስታችሁታል። የማላዘንና የመቆዘም ምልክት፣ ወይም ሔዋንን የመውቀስ ምልክት፣… በአዳም ላይ አይታይም። በተቃራኒው፣ የወደፊቱን አዲስ ሕይወት ለመጀመር የጓጓ ይመስላል። ከምድረ ገነት እየወጣ መሆኑን ስለረሳ አይደለም። የዚህ ሁሉ መነሻ፣ ሔዋን መሆኗንም ሊዘነጋ አይችልም። ነገር ግን፣ ቅሬታና ወቀሳ የለም።
በተቃራኒው ወደ ጉጉትና ወደ አድናቆት ዞሯል። ገና አሁን ማንነቱን ያወቀ፣ ገና አሁን ሕያውነትን የቀመሰ፣ ወደፊትም ሕይወትን በደንብ ለማጣጣም ያለመ ይመስላል። ለዚህ ሁሉ መነሻ ለሆነችለት፣ ለውዷ ሚስቱም አዲስ ስም አወጣላት። ሔዋን ብሎ የሰየማት ያኔ ነው። “የሕያዋን ሁሉ እናት” በሚል ማዕረግ፣ ለሷ ያለውን አድናቆት፣ ክብር እና ፍቅር ሲገልፅ፣ “ልጆች ትወልጂያለሽ” ለማለት ፈልጎ አይመስልም። “የሕያውነት እናት” ለማለት ፈልጎ እንጂ። አልወለደችውም፤ ግን ሕያውነትን ያቀመሰችው እሷ ናት።
ከዚያ በፊት የነበረው ሕይወትማ፣ ከእንሰሳት ኑሮ ብዙም አይለይም። ወይም ዘላለም ጨቅላ ሕፃን ሆኖ እንደ መኖር ነው።
ራሱን እንደማያውቅ ሕፃን፣ የቅፅበት የቅፅበቷን ብቻ እያየና የተነገረውን እየሰማ፣ የእለት የእለቷን የታዘዘውን እየተከተለና የቀረበለትን እየበላ መቀጠል፣ ምሉዕ ሕይወት አይደለም። ከሌሎች መማር ጥሩ ቢሆንም፣ ራስን ችሎ የራስን አእምሮ ተጠቅሞ እውነትን የመለየትና እውቀትን የመጨበጥ ብቃት በመገንባት ነው፤ የምር ሰው መሆን የሚቻለው። ይሄ ነው፣ ብርሃናማው የእውነት ፍሬ። ወፍ-ዘራሽ ዛፍ ላይ እየተንጠላጠሉና ፍሬ እየሸመጠጡ መብላት፣ ከጦጣ ከዝንጀሮ ኑሮ ብዙም አይለይም።
ያለ ቅንጣት ጥረት ምግብና መጠጥ የሚገኝባት ምድረ ገነት ውስጥ፣ ሲበሉ ውለው ሲጠጡ እያመሹ ቀን መቁጠርና እድሜን መግፋት፣ ‘ኮማ’ ውስጥ ገብቶ ከድንዛዜ መንቃት እንዳቃተው ሕመምተኛ የመሆን ያህል ነው። እንዲያውም፣ ሕመምተኛው፣ የመንቃት እድል ሊኖረው ይችላል። ‘ኮማ’ ውስጥ በድንዛዜ ቀን መቁጠር ወይም ምድረ ገነት ውስጥ ፍሬ መሸምጠጥና መሰልቀጥ፣ ምሉዕ ሕይወት አይደለም – ለሰው። ይልቅስ፣ ፍሬ የተንዠረገገበት ምድረ ገነትን በጥረት መፍጠር፣… “ይሄ’ኮ የኔ ስኬት ነው”፣ ውብ የስራ ፍሬውን ማጣጣም የቻለ ሰው ነው፣ የምር ሰው መሆን የሚችለው። በራሱ የሚመራ፣ በራሱ የሚተማመንና ራሱን የሚያከብር ሰብእና፣ ማንነት፣ እኔነት ነው ይሄ። ይሄ ነው፤ ብርሃናማውን እውነትና ቀናውን መንገድ አዋህዶ የራሱ ያደረገ፣ ክቡር ሕይወትና ሕያው እኔነት።
ለካ፣ የእውነትን ብርሃን መመልከት፣ ጥሩና መጥፎን ለይተው በመልካሙ መንገድ መጓዝ የጀመሩት፣ “በአቋራጭ”፣ “የእውነትን ፍሬ፣ የመልካምነትን ፍሬ ስለበሉ” አይደለም። ከዚያ በፊት ነው ከእንቅልፍ የባነኑት፤ ከድንዛዜ የነቁት። “ምን?”፣ “ለምን?” ብለው መጠየቅ የጀመሩ ጊዜ ነው፤ በብርሃናማው እውነት፣ በመልካሙ መንገድ፣ አዲስ የሕይወት ጉዞ የጀመሩት። በአቋራጭ፣ በአንዳች ተዓምር፣ እውነትን የሚገልጥ፣ እውቀትን የሚሞላ፣ በመልካምነት የሚመራ፣ ስኬትን የሚያሸክም፣ ሕያውነትን የሚሰጥ ትንግርተኛ ዛፍና ፍሬ አያስፈልጋቸውም።
ታዲያ፣ አዳም፣ ከምድረ ገነት ሲወጣ፣ አርሰህ ብላ፣ ሰርተህ ኑር፣ በራስህ እውቀትና በራስ ጥረት ሕይወትህን ምራ የሚሉ መርሆች፣ ቅሬታ ባይፈጥሩበት ይገርማል? በተቃራኒው፤ ገና ሕያውነትን ማጣጣም ቢጀምር አይገርምም። ለዚህ ድንቅ ሕያውነት መነሻ ሆናለት፣… እጅጉን በፍቅር፣ በክብርና በአድናቆት፣ “የሕያውነት እናት!” ብሎ ቢያወድሳትም አይገርምም።