ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ‘ትሬይነር ፕላስ’ ሙሉ አባል ሆነች።
አቪዬሽኑ እንዳስታወቀው ሀገሪቱ የ’ትሬይነር ፕላስ’ አባል መሆን በዘርፉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በመስጠት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝላታል ብሏል።
የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉና እያደጉ በመምጣት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተጨማሪም የአየር ትራፊክ መጠን እየጨመረ በመሄዱ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ማሰልጠን ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም ይነገራል።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በቀለ፥ ማዕከሉ ቀደም ሲል በተለያዩ የአቪዬሽን ሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።
“አሁን የሙሉ አባልነት ማረጋገጫ የተገኘበት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ‘ትሬይነር ፕላስ’ ሃገሪቷ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን መስጠት ያስችላታል” ብለዋል።
በዚህም የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል ነው ያነሱት።
አባልነቱ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአቪዬሽኑን የስልጠና ማዕከል አሰራር በመገምገም በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጠው አስተያየትና የግምገማ ውጤት መሰረት የተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የማዕከሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ያዘጋጁት ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ሰነድና መርሃ-ግብርም ደረጃውን ካስገኙ መስፈርቶች መካከል ተጠቅሰዋል።
የስልጠና ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ለ20 ጅቡቲያውያን ስልጠና እየሰጠ ሲሆን ባለፈው ዓመትም ለሶማሌ ላንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስልጠና መሥጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።