ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት አሊያም ክብደት ያላቸው ሰዎች በቀላሉ ለ11 የካንሰር አይነቶች ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናት አመልክቷል።
ከመጠን ካለፈ ውፍረት ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱት ውስጥ፥ የጡት፣ የማህፀን፣ የኩላሊት፣ የጣፊያ እና የአንጀት ካንሰር ይገኙበታል።
ካንሰር በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ለሰው ልጆች ሞት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ እየያዘ ይገኛል።
ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት ወይም ውፍረት ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመልከተው በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ሰዎች ከልክ ላለፈ የሰውነት ክብደት ወይም ውፍረት የተጋለጡ ናቸው።
ይህ ደግሞ ከ10 ሰዎች አራቱ ከልክ ላለፈ የሰውነት ክብደት እንዲሁም ከ10 ሰዎች አንዱ ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋልጠዋል እንደማለት ነው።
ይህም ሰዎች በብዛት ለልብ ህመም፣ ለስኳር በሽታ፣ ለኩላሊት እና ለመገጣጠሚያ አካል የጤና እክል እንዲጋለጡ እደረገ መሆኑን ሪፖርቱ ያመልክታል።
ከዚህ በተጨማሪም የካንስረ ተጋላጭነት በስፋት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።
ጥናቱ በእንግሊዝ ለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የተካሄደ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ከመጠን በላይ ውፍረትን ወይም የሰውነት ክብደት ከ36 የተለያዩ የካንሰር አይነቶች ጋር ግንኙነት አለው በሚል የተሰሩ 204 ጥናቶችን በመዳሰስ ነው የተካሄደው።
በዚህም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ወይም የሰውነት ክብደት ለ11 የካንሰር አይነቶች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ማጣራታቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።
የካንሰር አይነቶቹም፥ የጡት፣ የማህፀን፣ የኩላሊት፣ የጣፊያ፣ የትልቁ እና ትንሹ አንጀት፣ የጉሮሮ፣ የአጥንት፣ የሆድ እና ሌሎች ናቸው።
የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶክተር ግራሃም ኮልዲዝ፥ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት በካንሰር ተጋላጭነት ላይ የሚኖረው ተፅእኖ እንደ ሰውነት ክፍል ሊለያይ ይችላል ብለዋል።
ዋናው ነገር ግን ከልክ ያለፈ ውፍረት አሊያም የሰውነት ክብደትን በተቻለን አቅም ሁሉ መከላከል ነው ሲሉም ይናገራሉ።
ከመጠን ላለፈ ውፍረት ከተጋለጣቹ በመጀመሪያ የሰውነታቹ ክብደት ከዚያ በላይ እንዳይጨምር መጠንቀቅ አለባችሁ ያሉት ዶክተር ግራሃም ኮልዲዝ፥ በተቻለን አቅም የሰውነታችንን ውፍረት ወይም ክብደት መቀነስ ደግሞ የካንሰር ተጋላጭነታችንን መቀንስ ነው ሲሉም ተናግረዋል።