እስካሁን በርካታ ወለል ካላቸው ህንጻዎች ላይ ወድቆ ህይወቱ ተረፈ የተባለ ሰው እንዳለ ተሰምቶ አይታወቅም ይሆናል።

ሶስት ወለል ካለው ህንፃ ላይ ከሚወድቁ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ብቻ በህይወት የመትረፍ እድል ያላቸው ሲሆን፥ 10 ወለል ካለው ህንፃ ላይ ወድቆ ግን እስካሁን በህይወት የተረፈ ሰው የለም።

የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ነዋሪው የመስታወት አፅጂ ግን ስራውን በመስራት ላይ እያለ ከ47ኛ ወለል ላይ ወደ መሬት ወድቆ ህይወት መትረፍ መቻሉ ተአምር ሆኗል።

አልሲደስ ሞኔሮ እና ታናሽ ወንድሙ ኤጋር ሞኔሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2007 ላይ 47 ወለል ያለውን ሰማይ ጠቀስ ሀንፃ መስታወት ማጽዳትን በጠዋት ነበር የጀመሩት።

MONERO_1.jpg

ሞኔሮ ይናገራል፥ “ህንጻውን ለማጽዳት እስከ 47ኛው ፎቅ ድረስ በአሳንሰር (ሊፍት)ነበር ተጠቅመን ወደላይ የወጣነው፤ የህንጻው ጣራ አካባቢ የነበረው ቅዝቃዜ በጣም ከፍተኛ ነበር” ይላል።

ወደህንጻው ላይ ከወጡ በኋላ ግን ያልጠበቁት አደጋ ያጋጥማቸዋል፤ የህንጻውን መስታወት ማጽዳት በመጂምሩበት ጊዜም ተንጠልጥለውበት የነበረው ገመድ ከተጣበቀት ቦታ በድንገት ይበጠሳል።

ሞኔሮ፥ “በመጀመሪያ በግራ በኩል ገመድ ነው የተበጠሰው፤ ወንድሜ የነበረት አቅጣጫ መለት ነው፤ በዚህ ጊዜም ወንድመሜ ወደቀ” ብሏል።

ኤጋር ሞኔሮ 472 ጫማ ከፍታ ካለው ህንጻ ላይም በጣም በፍጥነት እየተመዘገዘገ የወደቀ ሲሆን፥ መሬት በሚደርሰበት ጊዜም በግምት በአማካኝ በሰዓት 190 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ነበረው።

ከጥቂት ቆይታ በኋላም አልሲደስ ሞኔሮ በኩል ያለው ገመድም የተበጠሰ ሲሆን፥ እሱም ልክ እንደወንድሙ በፍጥነት እየተምዘገዘገ መሬት ላይ ይወድቃል።

በቦታው የደረሱ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞችም በጣም አሰቃቂ ነገር መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን፥ ቀድሞ የወደቀውን ኤጋር ሞኔሮን አካል በእንጨት አጥር ላይ ወድቆ ነበር ያገኙት።

አልሲደስ ሞኔሮን ግን መሬት ላይ በህይወት እንዳገኙት ይናገራሉ።

የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞችም በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ አልሲደስ ሞኔሮን ከወደቀበት አንስተዋል፤ በወቅቱ ትንሽዬ ስህተት ቢፈጠር አልሲደስ ይሞት ነበርም ተብሏል።

አልሲደስ ሞኔሮን በአቅራቢያው ወደ ነበረ ሆስፒታል በፍጥነት የወሰዱት ሲሆን፥ በጊዜውም ራሱን ስቶ በሰመመን ውስጥ ነበር።

በወቅቱም በአእምሮው፣ በጀርባ አከርካሪ አጥንቶቹ፣ በደረቱ እና በሆዱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ የነበረ ሲሆን፥ እጅ እና እግሩ ላይም የመሰበር አደጋ አጋጥሞታል።

የአልሲደስ ሞኔሮን ህይወት ለማታደግም በርካታ ቀዶ ጥገናዎች እንደተረገለት የሚናገሩት የጤና ባለሙያዎች፥ በአእምሮው ውስጥ ፍሳሽ በመብዛቱ ምክንያትም ካታተር ተገጥሞለት እንደነበረ እና 24 ዩኒት ደም እንደተሰጠውም ተናግረዋል።

የኒው ዮርክ ፕሬስባይቴሪያን ሆስፒታል ዶክተር ሀርበረት ፕራድስ፥ “በህክምና ዘርፍ ተአምርን ማየት ከፈለጋችዎ ሞኔሮን ማየት ብቻ ይበቃል” ብለዋል።
በርካታ ህክምናዎች የተደረጉለት አልሲደስ ሞኔሮ ከሶስት ወራት በኋላ ከሰመመን መንቃቱም ተነግሯል።

አልሲደስ ሞኔሮ ይናገራል፥ “በምንቃበት ጊዜ አእምሮዬ አካባቢ ብዥታ ነበር፤ ከነቃው በኋላም ወንድሜ እንደሞተ ለመገመት አላስቸገረኝም ምክንያቱም አጠገቤ ሚስቴ እና ልጄ ብቻ ነበሩ፤ በህይወት ቢኖር ኖሮ እሱም ከጎኔ ይሆን ነበር” ብሏል።

ወንድሜን ማጣትም ትልቅ ሀዘን ፈጥሮብኛል ሲልም ተናግሯል።

አሁን የ46 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ሞኔሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ1990ዎቹ ነበር ከወንድሙ ጋር ስራ ለመፈለግ ከኢኳዶር ወደ አሜሪካ የገባው።

አሁንም ቢሆን መስራት ከቻልኩኝ መስታወት ወደ ማፅዳቱ እመለሳለው፤ የከፍታ ፍራቻ የለብኝም ሲል የተናገረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን በጤና እክል ምክንያት ስራውን መስራት እንደማይችል ተነግሮታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ