የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ሩጫ በመላ ሀገሪቱ ዛሬ ተካሂዷል።
የሩጫ ውድድሩ “ጊዜ የለንም እንሮጣለን! ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!” በሚል መሪ ቃል ነው ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ የተካሄደው።
በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በድምቀት በተካሄደው የሩጫ ውድድር ቁጥራቸው 650 ሺህ የሚጠጉና ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ዜጎች ተሳትፈውበታል፡፡
ውድድሩ በአዲስ አበባ ከተማም መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ የተካሄ ሲሆን፥ በውድድሩ ላይ ከ90 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል።
በመስቀል አደባባይ የተካሄደውን የሩጫ ውድድርም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስጀምረዋል።
ዶክተር ደብረጺዮን በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም፥ የግድቡ ግንበታ ያለሴቶች ተሳትፎ የትም ሊደርስ አይችልም ብለዋል።
የህዳሴ ግድብን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የህዝቡ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር ደብረጺዮን አስታውቀዋል።
ፎቶ፦ኢቢሲ
በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የ6 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ በወንዶች፣ በሴቶችና በአካል ጉዳተኞች ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች ከክብር እንግዶች የሜዳሊያ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።